Connect with us

የሽምግልናው ጉዳይ

የሽምግልናው ጉዳይ

ፓለቲካ

የሽምግልናው ጉዳይ

የሽምግልናው ጉዳይ | (አዲሱ አረጋ ~ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር)

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለዉን አለመግባባት ለመፍታት 52 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን በመያዝ በራሳቸዉ ተነሳሽነት ወደ መቐለ መጓዛቸዉ የማህበራዊ ሚዲያዉ አጀንዳ ሆኗል፡፡

በርግጥ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በራሳቸዉ ተነሳሽነት ያለዉን አለመግባባት ለመፍታት የጀመሩት ጥረት አክብሮት ሊቸረዉ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ሆኖም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በቀናነት የጀመሩትን ጥረት ለራስ የፖለቲካ ቡድን የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ብሎም ብልጽግና ፓርቲን ለማጥቃት በማሰብ አንዱን ሽምግልና ላኪ ሌላዉን ሽምግልና ተቀባይ አድርጎ በማቅረብ መዝመትና ዲጂታል ወያኔዎችን እና ቅልብተኞቻቸዉን አሰማርተዉ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ሀገራችን ያለችበትን ፖለቲካዊ ችግር ከመፍታት አኳያ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደር ባለፈ ምንም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡ የሽማግሌዎቹ በጎ ጥረት ላይም ዉሃ መቸለስ ይሆናል፡፡

ሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ ዕርቅን በተመለከተ ብልጽግና ፓርቲ ግልጽ አቋም አለዉ፡፡ ይህች ሀገር የሀገረ መንግስት ግንባታዋ ምስቅቅል ታሪክ ጀምሮ አሁንም ተሰርታ ያላለቀች ሀገር እንደመሆኗ በርካታ ፖለቲካዊ ቁርሾዎች፣ ቁስሎች እና አለመግባባቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የዚህችን ሀገር ፖለቲካዊ ቁስሎች ከቁርሾ እና ከቂም በቀል ይልቅ በፍቅር እና በይቅርታ መታከም እንዳለባቸዉ፣ በብሄራዊ መግባባት ባልተፈጠረባቸዉ ጉዳዮች ደግሞ በተለይም በሀገራችን የፖለቲካ ሊህቃን መካከል ተዋስኦ መር ድርድሮች እየተደረገባቸዉ መግባባት ያልተደረሰባቸዉ ጉዳዮች በመግባባት እየተቋጩ እንዲሄዱ ብልጽግና በጽኑ ያምናል፡፡ ከዕምነት ባለፈም በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንጻር ሰፊ እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከዚህ በፊት የነበሩ ቁርሾዎች እና የፖለቲካ ጠባሳዎች እንዲሽሩ ለማድረግ ይህን ጉዳይ የሚመራ ገለልተኛ ተቋም (የእርቀ ሰላም ኮሚሽን) አቋቁሞ ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡ ብሄራዊ መግባባት ባልተደረሰባቸዉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ዉይይቶች ተጀምረዋል፡፡

እነዚህን መልካም ጅምሮች ከግብ ለማድረስ ብሎም ፖለቲካችን ያለፈዉን ቁስል በማከክ ብቻ ህልዉናቸዉን የማስቀጠል አባዜ የተጠናወታቸዉ ብልጣ ብልጥ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሲሳይ እንዳይሆን ለማድረግ ከብሔራዊ መግባባት እና ዕረቀ ሰላምን ከማዉረድ አኳያ ካለፍንበት ሀገራዊ ተሞክሮ መማር የግድ ይሆናል፡፡ ከደርግ ስርዓት መዉደቅ ማግስት በ1983 ዓ/ም የሽግግር መንግስት ወቅት ለሀገራዊ ዕርቅ የቀረበ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ያሳተፈ ሂደት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ሁላችንም እንደምናስታዉሰዉ ሂደቱ የተሳካ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ በደርግ ወስጥ የነበሩ ፖለቲከኞችን እና በደርግ ጊዜ የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊትን “የደርግ ወታደር” ብሎ በመፈረጅ ሙሉ በሙሉ ማግለሉ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ሁለተኛዉ ምክንያት በሽግግሩ ወቅት በጊዜ ሂደት ኦነግ፣ የሲዳማ ነጻነት ንቅናቄ እና ሌሎችም ኃይሎች እየተገፉ እንዲወጡ መገደዳቸዉ ነዉ፡፡ ሶስተኛዉ ምክንያት በወቅቱ እንደ አሸን ፈልተዉ የነበሩ ነጻ ጋዜጦች (እንደ አሁኑ ማህበራዊ ሚዲያ )፣ እና ሲያቆጠቁጡ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ሲነዙት የነበረዉ አፍራሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ እንዲሁም ሂደቱን የሚመራ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋም አለመኖር በዚያን ወቅት ብሄራዊ መግባባትን እና ሀገራዊ እርቅን ከመፍጠር አኳያ የነበረዉ መልካም አጋጣሚ እንዲመክን አድርጎታል፡፡

በሽግግር ሂደቱ ከነበረዉ ታሪክ የምንወስደዉ ትምህርት ሀገራዊ ዕርቅንም ሆነ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁሉንም ያገባኛል የሚል ቡድን በሆደ ሰፊነት ማሳተፍ የግድ መመሆኑን ነዉ፡፡ ከዚያም ባለለፈ “የበሬ ወለደን” አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ቡድኖችን አደብ ማስገዛት፣ ዕርቀ ሰላም ሂደቱን የሚመራ ገለልተኛ ተቋም መመስረት እና ማጠናከር ማንኛዉም የዕረቀ ሰላም ጉዳይ በተናጠል እና በራሳቸዉ በጎ ፈቃድ በቀናነት ተነሳስተዉ በሚነቀሳቀሱ ቡድኖች ሳይሆን የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ በሚቋቋመዉ ገልለተኛ ተቋም ብቻ እንዲመራ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ብልጽግና በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሌላኛዉ ትምህርት ልንወስድበት የሚገባዉ የታሪክ ምዕራፍ በ1999 ዓ/ም ሀገራዊ የሽምግልና ኮሚቴ በወቅቱ ከምርጫ 1997 ጋር ተያይዞ በእስር ሲማቅቁ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎቸን ለማስፈታት ብሎም ብሄራዊ መግባባት እና ሀገራዊ እርቅ እንዲመጣ ያደረገዉ ጥረት ነዉ፡፡ በርግጥ በወቅቱ በራሱ የነበረዉ ሀገራዊ የሽምግልና ኮሚቴ በእስር ሲማቅቁ የነበሩትን የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ በማድረግ ስኬትን አስመዝግቧል፡፡ ነገር ግን እስረኞች የተፈቱበት ሂደትና ከተፈቱ በኋላ የነበረዉ የህወሃት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ራሷን አሸናፊና ከእስር የተፈቱትን ተሸናፊ፣ ሕወሓትንን ይቅርታ አድራጊ ፣ በእስር የነበሩ ፖለቲከኞችን ይቅርታ ጠያቂ አድርጋ ማቅረቧ የዜሮ ድምር የፐለቲካ ጨዋታ የተጠናወተዉ በመሆኑ ብዙም ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ ከእስር የተፈቱት ፖለቲከኞችም ውጭ ሀገራት መውጣታቸውና የተወሰኑት የትጥቅ ትግል ለመጀመር መወሰናቸው ከገባንበት አዙሪት እንዳንወጣ አድርጎናል፡፡ ሕወሃት ሆነ የሀገራችን የፖለቲካ ተዋናዮች ከ1999ኙ ታሪካችን መማር ያለብን ዋናዉ ቁምነገር ሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ ዕርቅን በማምጣት የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን አንዱን አሸናፊ፣ ሌላኛዉን ተሸናፊ፣ አንዱን ሽምግልና ላኪ ሌላኛዉን ሽምግልና ተቀባይ፣ አንዱን ይቅርታ አድራጊ ሌላኛዉን ይቅርታ ተቀባይ አድርጎ በማቅረብ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጨዋታ መሞከሩ አንድም ስንዝር ወደፊት እንደማያራምደን ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ቁስሎችንና ቁርሾዎቻቸንን በማከም ወደሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ ዕርቅ ለመምጣት በተቋቋመዉ ገልለተኛ ተቋም እና በፖለቲካ ሊህቃን መካከል የሚደረግ ተዋስዖ መር ድርድር መጠናከር አለበት፡፡ ከዚህ ዉጭ በዘልማዳዊ አካሄድ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጨዋታ እና ዕለታዊ የፖለቲካ ትርፍን ማዕከል ባደረገ የፖለቲካ ጮሌነት ለመራመድ የምናስብ ከሆነ መሰረታዊ ችግሮቻችንን በመፍታት ወደ ዘመናዊ እና የሰለጠነ ፖለቲካ ለመራመድ ሊያዳግተን ይችላል፡፡

ለማጠቃለል፣ ሀገራዊ መግባባት እና ሀገራዊ ዕርቅን በማምጣት የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን ብልጽግና ጠንክሮ መስራቱን ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ በቀናነት ያለዉን አለመግባባት ለመፍታት የጀመሩት ጥረት ሊያስመሰግናቸዉ ይገባል፡፡ ሆኖም እነዚህን መልካም አሳቢ ሰዎች ጥረት አንዱ ወደ ሌላዉ ቡድን ሽምግልና እንደላካቸዉ አስመስሎ ፕሮፓጋንዳ መርጨት ከእዉነታ የራቀ ከመሆኑም በላይ ካፈጀዉ የፖለቲካ አስተሳሰብ አለመላቃችንን ያሳያል፡፡ ከችግራችን ለመላቀቅ የሚደረጉ ዉይይቶችም ሆኑ ድርድሮች ከምንም በላይ ካለንበት ችግር ለመላቀቅ ቅንነትን፣ ህገ መንግስትን፣ ህግን እና መርሆዎችን ያማከሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ቸር እንሰንብት!

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top