ከ54 እስከ 76 ዓመታት የቆዩበትንና በንግድ ሥራ የሚተዳደሩበትን ድርጅቶቻቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የገለጹ ሦስት ድርጅቶች በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ መልሶ ማልማትና የከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤትና በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ላይ የሁከት ይወገድልን ክስ አቀረቡ፡፡
ተቋማቱ ክስ የቀረበባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባይ እያሠራው ካለው፣ ‹‹አዲስ አበባን እናስውብ›› ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከአምፊ ቴአትር (ሰይጣን ቤት) ወደ ላይ የሚገኙትን ንብረትነታቸው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሆኑት 17 መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ፋርማ አክሲዮን ማኅበር፣ አንበሳ መድኃኒት ቤት አክሲዮን ማኅበርና ኒኦን አዲስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይገኙበታል፡፡
ለፕሮጀክቱ ሲባል እነዚህ ድርጅቶች ማለትም ፋርማ አክሲዮን ማኅበር፣ አንበሳ መድኃኒት ቤትና ኒኦን አዲስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአስቸኳይ መነሳት እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው፣ ድርጅቶቹ ወደ ፍርድ ቤት አምርተዋል፡፡
ድርጅቶቹ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረቡት የሁከት ይወገድልን ክስ እንደገለጹት፣ ፋርማ አክሲዮን ማኅበርና አንበሳ መድኃኒት ቤት ከ70 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የኖሩ ድርጅቶች ከመሆናቸው በላይ 64 ቋሚ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የመድኃኒት ክምችትና የተንቀሳቃሽ ዕቃዎችም ክምችት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
ኒኦን አዲስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ፣ ከ54 ዓመታት በላይ የቆየ ድርጅት መሆኑንና 36 ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉበት አስታውቋል፡፡
እንደ ድርጅቶቹ ክስ ምንም እንኳን ለልማት ሲባል ድርጅታቸውን ለቀው መውጣት ቢኖርባቸውም፣ በአዋጅ ቁጥር 1161/2012 ድንጋጌ መሠረት መሆን አለበት፡፡ ይህም ለልማት ተነሽ መሆናቸው ተነግሯቸው በቂ ጊዜ ሊሰጣቸውና ተገቢው የካሳ ክፍያ ሊፈጸምላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ተከሳሶች ግን በተግባር ላይ የዋለውንና ከወጣ አንድ ዓመት ያልሞላውን አዋጅ በመተላለፍ በአስቸኳይ ለቃችሁ እንድትወጡ ማለታቸው ተገቢ ስላልሆነ፣ እንዲሁም ሕግን የተላለፈ ሁከት በመሆኑ እንዲታገድላቸው ጠይቀዋል፡፡
ምንም እንኳን ሥራ ባይኖርም ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ በመሆኑ በአጠቃላይ ለ100 ሠራተኞች ሠርተው ከሚያገኟት ደመወዝ እየከፈሉ መሆናቸውን በክሱ አስረድተዋል፡፡ የድርጅታቸውን ሥራ የሚያስቀጥሉበት የሥራ ቦታ ሳያገኙ እንዲለቁ ማስገደድ፣ የድርጅቶቹን ባለቤቶችና ሠራተኞች ከእነ ቤተሰቦቻቸው መበተን በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
የድርጅቶቹን ክስ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች እስከ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ መልሳቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የግራ ቀኙን ክስ ለመስማት ለሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡(ሪፖርተር – ታምሩ ጽጌ)