Connect with us

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ጉዳይ ላይ እጃችንን አናስገባም

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጃችንን አናስገባም -  ደቡብ ሱዳን
Photo: Facebook

ፓለቲካ

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ጉዳይ ላይ እጃችንን አናስገባም

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ ላይ እጃችንን አናስገባም –  ደቡብ ሱዳን

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ሞርጋን ጋር ተወያዩ።
አምባሳደር ጄምስ ሞርጋን በውይይቱ ወቅት ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ በማንኛውም ጉዳይ ላይ እጇን እንደማታስገባ ገልጸዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቀውና ደቡብ ሱዳን በግዛቷ ለግብጽ መንግስት የወታደራዊ ካምፕ ግንባታ የሚያገለግል ቦታ ለመስጠት ከግብጽ ጋር ተስማምታለች በሚል የተናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው በማለት ገልጸዋል።

ይህን አስመልክቶ መንግስታቸው መግለጫ ማውጣቱን እና መግለጫውም ጁባ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን፥ ኤምባሲያቸውም በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሚዲያዎችን በመጋበዝ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን አንስተዋል።

ደቡብ ሱዳን እንደ ሃገር ራሷን እንድትችል እና የበለጸገች እንዲሁም የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ያረጋገጠች ሃገር እንድትሆን የኢትዮጵያ ድጋፍ የጎላ መሆኑንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ህዝቦች በሁለት ሃገር ውስጥ የሚኖሩ እና በርካታ ነገሮችን የሚጋሩ አንድ ህዝቦች ናቸውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በመጠቀም የመልማት መብቷን ደቡብ ሱዳን በጽኑ ትደግፋለች፤ ፍላጎቷንም ታከብራለች ብለዋል አምባሳደር ጄምስ።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በቀጠናው የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ጉልህ ሚና የሚጫወት እና ለደቡብ ሱዳንም ተነሳሽነትን የሚፈጥር ፕሮጀክት ስለሆነ በደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግስት በኩልም ሙሉ ድጋፍ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት የሁሉንም ሃገር ጥቅም ባማከለና የህዝቦቹን ፍላጎት ባጣጣመ መልኩ በውይይት መፈታት እንዳለበት ደቡብ ሱደን በጽኑ ታምናለችም ብለዋል አምባሳደር ጀምስ በንግግራቸው።

አምባሳደር ጄምስ ኢትዮጵያ በትናንትናው እለት ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ላደረገችው የኮቪድ19 ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወዳጆቿን በውል እንደምትረዳ ጠቅሰው፥ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀውን ወሬ ትክክል ነው ብላ እንዳልወሰደችው አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋ ትሰጣለችም ነው ያሉት።

በናይል ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሁሉም የላይኞቹ ተፋሰስ ሃገራት በእኩልነት የመጠቀም መብት ስላላቸው ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን የምትቃወምበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌላትም ኢትዮጵያ በውል ትገነዘባለች ብለዋል አቶ ገዱ።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ወንድሞቿ ጋር በጋራና በትብብር የመልማት በመርህ ላይ የተመሰረተና ለዘመናት የዘለቀ አቋሟን በማጠናከር ከደቡብ ሱዳን ጋር በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ትሰራለችም ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን የተረጋጋችና የህዝበቿን ጥቅም ያረጋገጠች ሃገር እንድትሆን ኢትዮጵያ የዘወትር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Continue Reading
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top