የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረት በህዳሴ ግድቡ በአደራዳሪነት ለመግባት ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታወቀ
የግብፅ መንግሥት የእነዚህን ወገኖች ሚና ለመቀበል ዳተኝነት አሳይቷል
በአሜሪካና በዓለም ባንክ የታዛቢ/አደራዳሪነት ሚና በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል በታላቁ በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተቋርጦ ሦስቱ አገሮች ዳግም ወደ ሦስትዮሽ ድርድር ውይይት ለመመለስ ፍላጎት ካሳዩ በኋላ፣ የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረት አደራዳሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ታወቀ።
በአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን የያዙት የኅብረቱ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ስማኤል ቼሩጊ ናቸው። ኮሚሽነር ቼሩጌ ባለፈው ሳምንት ከአውሮፓ ኅብረት ምክትል ኮሚሽነርና የኅብረቱ የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሮሌ ጋር በህዳሴ ግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች ለማድረግ ስላሰቡት ድርድር፣ እንዲሁም ሁለቱ አኅጉሮች ስለሚኖራቸው ሚና በስልክ መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቼሩጊ በድርድሩ ጉዳይ፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናና በሊቢያ ቀውስ ላይ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርና የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ መልዕከተኛ ሚካኤል ቦግዳኖቭ ጋር፣ ባለፈው ሳምንት በስልክ መወያየታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ኮሚሽነር ቼሩጊ ከአውሮፓ ኅብረት አቻቸው ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ገጻቸው ያረጋገጡ ሲሆን፣ ውይይታቸውም ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላም መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።
ይኼንኑ የባለሥልጣናቱን የስልክ ውይይት አስመልክቶ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ሦስቱ አገሮች የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያላቸውን ልዩነቶች ለመፍታት ዳግም ወደ ውይይት ለመመለስ ፍላጎት ማሳየታቸውን በበጎ ገጽታው አንስተው እንደተነጋገሩበት መግለጫው ያስረዳል።
‹‹ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን አለመግባባት መፍታት የቀጣናውን አጠቃላይ ሰላምና መረጋጋት የሚመለከት ነው፤›› የሚለው የአውሮፓ ኮሚሽን መግለጫ፣ ይኼንን መንፈስ መሠረት በማድረግም የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ቦሮሌና የአፍሪካ ኅብረቱ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ቼሩጊ እንደተወያዩ በመግለጫው ተመልክቷል።
ከዚህ የስልክ ውይይት ቀደም ብሎ በነበረው ሳምንትም የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ከሦስቱ አገሮች ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩና ከመካረር ይልቅ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ማበረታታቸውን፣ ለኮሚሽነር ቼሩጊ ማስረዳታቸውን መግለጫው ያመለክታል።
በሦስቱ አገሮች መካከል ያለው ልዩነት ከዚህ በላይ መካረር እንደሌለበትና በፍጥነት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ ሊፈለግ እንደሚገባ መወያየታቸውን፣ በዚህ ረገድ ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉትን ውይይት የአውሮፓ ኅብረት ለመደገፍና የኅብረቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን በማካፈል እንዲያግዙ ከተፈለገም ኅብረቱ ዝግጁ መሆኑን እንደገለጹ መግለጫው ያስረዳል።
ኮሚሽነር ቼሩጊ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በህዳሴ ግድቡ የሦስቱን አገሮች አለመግባባትንና በሊቢያ ጉዳይ ላይ መክረዋል።
በውይይታቸውም ሦስቱ አገሮች ልዩነታቸውን ለመፍታት የሚያደርጉትን አዲስ ጥረት የአፍሪካ ኅብረት ለማገዝ መንቀሳቀስ መጀመሩን ኮሚሽነር ቼሩጊ የገለጹላቸው ሲሆን፣ በተመሳሳይም በሱዳንና በሊቢያ የሚስተዋለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ሰፊ ተሳትፎ መጀመሩን ስለማስረዳታቸው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛም፣ ‹‹ለአፍሪካ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚል መርህ የአፍሪካ ኅብረት የጀመረውን አዲስ ጥረት የሩሲያ መንግሥት እንደሚደግፍ ማረጋገጣቸውን መግለጫው ያመለክታል።
በሱዳን መንግሥት አነሳሽነት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ዳግም ወደ ሦስትዮሽ ውይይት ለመመለስ በቅርቡ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በተናጠል ያስታወቁ መሆኑ ይታወሳል። የሦስትዮሽ ውይይቱን ለመጀመርም የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የውይይት ሥነ ሥርዓቱን ተመካክረው እንዲያሰናዱ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ዳግም ወደ ውይይት የሚመለሱት በአሜሪካ ሲያደርጉ ለነበረው ውይይት የተቀመጠውን መስመር በመከተልና በዚሁ ውይይት ስምምነት ከተደረሰባቸው ጭብጦች በመነሳት ይሁን፣ አይሁን በሚለው ላይ አሁንም ከመግባባት አልደረሱም።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት አደራዳሪነት ሚና እንዳበቃና ከዚህ በኋላ አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባት እንደሌለባት አቋም የያዘች ሲሆን፣ ግብፅ ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት ሚና እንዲቀጥል ፍላጎት አላት።
ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥትን በመወከል የአደራዳሪነት ሚና ሲጫወት በነበረው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ላይ እምነት ካጣች፣ ይህ ተቋም ተቀይሮ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲተካ የሚል አማራጭ እያቀረበች መሆኑ ተሰምቷል።
ኢትዮጵያ ይኼንንም አማራጭ ለመቀበል ፍላጎት የሌላት ሲሆን፣ የልዩነት ጉዳዮቹ የቴክኒክ በመሆናቸው ሦስቱ አገሮች ለብቻቸው ባቋቋሙት ብሔራዊ የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በኩል በሚደረግ ወይይት ልዩነቶቹ ሊፈቱ ይችላሉ የሚል አቋም ታራምዳለች።
ይህንንም አቋሟን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በግብፅ በኩል ለቀረበባት ክስ በቅርቡ በሰጠችው ምላሽ በይፋ ገልጻለች። ነገር ግን የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት አስፈላጊ ከሆነ የአፍሪካ ኅብረት ወይም ሁሉም የሚስማሙበት አንድ የአፍሪካ አገር፣ እንዲሁም የዓባይ ወንዝ ተጋሪ አገሮች ባሉበት ሊካሄድ እንደሚችል ለተመድ በጻፈችው ደብዳቤ አስታውቃለች።
የግብፅ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት እንዲያደራድር የቀረበውን ሐሳብ እንደማይቀበል መግለጹን የሪፖርተር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ግብፅ የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት ላለመቀበል ስትል ከምታነሳቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በአዲስ አበባ መሆኑና ኅብረቱም የኢትዮጵያ ተፅዕኖ አለበት የሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የሚመጣ ውጤት የግብፅን ጥቅም የሚጎዳ ቢሆንና ግብፅ ውጤቱን ላለመቀበል ብትወስን የኅብረቱ አባል ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች በሙሉ እንደሚያቃርናት፣ ይህም አጠቃላይ የዲፕሎማሲ ኪሳራ እንደሚያደርስባት በመሥጋት የኅብረቱን የአደራዳሪነት ሚና ላለመቀበል አቋም መያዟን ምንጩ ያስረዳሉ።
የኅብረቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በተናጠል የአፍሪካ ኅብረት በአደራዳሪነት እንዲገባ ለግብፅ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ የግብፅ መንግሥት ሳይቀበለው መቅረቱን ጠቁመዋል።
ሌላኛው አማራጭ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረት በጋራ ሆነው እንዲያደራድሩ፣ በሁለቱ አኅጉራዊ ኅብረቶች በኩል ጥያቄ እየቀረበ ነው። የግብፅ መንግሥት ይኼንንም ለመቀበል ዳተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በህዳሴ ግድቡ ላይ ከተሰማሩት ኩባንያዎች መካከል ዋነኞቹ የጀርመን፣ የፈረንሣይና የጣሊያን በመሆናቸው ኅብረቱ በገለልተኝነት ለማደረደር አይችልም የሚል ደካማ መከራከሪያ በግብፅ ባለሥልጣናት በኩል እየተራመደ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ግብፅ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀጥረው የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እያከናወኑ የሚገኙትን እነዚህ ኩባንያዎች ግንባታውን አቋርጠው እንዲወጡ ለአገሮቹ ባለሥልጣናት ውትወታ አድርጋ፣ ኩባንያዎቹ የግል እንደሆኑና ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከተመሠረቱበት አገር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው የሚገልጽ ምላሽ አግኝታ ሳለ፣ አገሮቹ የተወከሉበት የአውሮፓ ኅብረትን ገለልተኝነት በኩባንያዎቹ ምክንያት መጠርጠር ድርድሩን ለማደናቀፍ ወይም በራሷ ፍላጎት ብቻ እንዲመራ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ምንጩ አስረድተዋል።
ይህ ቢሆንም የግብፅ መንግሥት የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረቶች በጋራ የአደራዳሪነት ሚና እንዲይዙ የቀረበውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አለማድረጉን የጠቆሙት ምንጩ፣ ሐሳቡን በከፊል እንደምትቀበለው ነገር ግን ከሁለቱ ኅብረቶች በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥትም እንዲሳተፍ ጥያቄ እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማቀድም ኢትዮጵያ የተቃወመችው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴርና የዓለም ባንክን ተሳትፎ በመሆኑ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲወከል ቢደረግ የሚል ጥያቄ ማንሳቷን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ተሳትፎ ላይ ግልጽ የሆነ አቋሟን ደጋግማ ያስታወቀችና ይኼንንም ፅኑ አቋሟን በቅርቡ ለተመድ እንደገለጸች ያስታወሱት ምንጩ፣ ቀጣዩ ድርድር አሜሪካ የምትሳተፍበት ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።
(ምንጭ:- ሪፖርተር ~ ዮሐንስ አንበርብር)