Connect with us

ሕግ አስከባሪ ሆነው ሳለ የወሮበሎች ሰለባ የሆኑ ኮሚሽነሮችና አመራሮች

ሕግ አስከባሪ ሆነው ሳለ የወሮበሎች ሰለባ የሆኑ ኮሚሽነሮችና አመራሮች
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ሕግ አስከባሪ ሆነው ሳለ የወሮበሎች ሰለባ የሆኑ ኮሚሽነሮችና አመራሮች

ሕግ አስከባሪ ሆነው ሳለ የወሮበሎች ሰለባ ሆነው የሚገኙ ኮሚሽነሮችና አመራሮች
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

እኛ ኢትዮጵያውያን የሰማዩ እንዳለ ሆኖ ለምድራዊ ሕግጋት የምንገዝ ሕዝቦች ነበርን፡፡ ወንጀል ለመሥራት ስንነሳሳም ሆነ ወንጀል ፈጽመን ለማምለጥ ስንሞክር የሕግ አካል ይቅርና ማንኛውም ሰው ‹‹በሕግ አምላክ›› ብሎ የሚያስቆመን ሰዎች ነበርን፡፡

በመሆኑም ‹‹ኮሚኒቲ ፒሊሲንግ›› የሚል ታፔላ የተለጠፈባቸው ቢሮዎች በየአካባቢው ሳይከፈቱ በፊት ሕብረተሰቡ የራሱን ሕግጋት እያወጣ እንደ ፖሊስ ሲመረምር፣ እንደ ዳኛ ሲፍርድ ዘመናትን አሳልፏል፡፡

የጸጥታና የሕግ አካላት በየቀበሌው ከተመደቡ በኋላም እያንዳንዱን ፋይል ብንመለከት የአካባቢው ፖሊስ አሳሪ እንጂ መርማሪ አልነበረም፡፡ በአካባቢው አንድ ወንጀል ሲፈጸም ‹‹እውስ እያወሰ›› ወንጀለኞችን ከለየ በኋላ ለፖሊስ አሳልፎ ሲሰጥ የነበረው ሕብረተሰቡ እራሱ ነበር፡፡ ለዚያም ነው ፖሊስና እርምጃውን ስንከታተል ከእያንዳንዱ ስኬታማ ምርመራ ጀርባ ‹‹ከሕብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሰረት›› የሚል አረፍተ ነገር የማይጠፋው…

ሌላውን ትተን አዲስ አበባን እንኳን ብንመለከት ማንኛውም ሰው ወደ ሌብነት ሲገባ በሕይወቱ ላይ መፍረድና እንደ አትሌት ሩጫ መለማመድ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ግለሰብ ኪስ ከመግባት በፊት በዙሪያው ካለው ሕዝብ የማምለጥ ብቃትና ስትያዝ የሚደርስልህ ፖሊስ መኖሩን ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹ሌባ›› የሚል ቃል እንደተሰማ የሚያሯሩጥህም ሆነ የሚቀጠቅጥህ ድፍን የከተማዋ ሕዝብ ይሆናል፡፡

አሁንሳ?
አሁንማ በጠራራ ጸሐይ ሕዝቡንም ጥበቃውንም ከምንም ሳይቆጥሩ ባንክ የሚዘርፉ ወጣቶች ተፈጥረዋል፡፡ የሚጠብቁትን ባንክ የሚዘርፉ ዘበኞችም ተበራክተዋል፡፡

በዚህ ሰሞን እንኳን የሰማናቸውን የወንጀል ዜናዎችን ብንመለከት…. አንድ ሕፃን አግታ 300 ሺህ ብር ለመቀበል ስትሞክር የተያዘች ሴት፣ ላፕቶፕና ሞባይሏን ለመዝረፍ ሲል አንዲት የህክምና ተማሪ በስለት ወግቶ የገደለ ወጣት፣ ‹‹ከተፈቀደልህ የተሳፋሪ ቁጥር በላይ ለምን ትጭናለህ?›› ያሉትን የቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በጥይት የገደለ የባጃጅ አሽከርካሪ፣ ከአሥር የመንግሥት ሰራተኞችን መሃከል አራቱን ገድለው ሶስቱን ያቆሰሉ የኦነግ ታጣቂዎች፣ ጉጅ ዞን ውስጥ የተገደሉ 12 ልዩ ኃይሎች፣ ቦሌ አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤት በእኩለ ሌሊት ገብተው በጦር መሳሪያ በማስፈራራትና ባለቤቱን በኤሌክትሪክ ሾክ እራሱን እንዲስት በማድረግ በርካታ ንብረት ዘርፈው በመኪና ያመለጡ ሌቦች፣ በሕገ ወጥ አዳኞች የተገደሉ ስምንት ዝሆኖች፣ በፎርጅድ ወረቀት ለኮሮና ተጠቂዎች ብር ሲሰበስቡ የተገኙ አጭበርባሪዎች…………

የሚገርመው ታዲያ ለሕግም ሆነ ለሕሊናው የማይገዛ ፍጡር በየቦታው መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ሕግ አስከባሪዎቻችንንም የዚሁ ሰለባ መሆናቸው ነው፡፡ አካባቢያቸውን ሊጠብቁ ሲገባ እራሳቸውን መጠበቅ ተስኗቸው በማንም ወሮቦላ ጥይት በየቦታው ዘንበል ብለው የሚገኙ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና አመራሮች ቁጥርም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፡፡ ሕገ-ወጦቹ በአደረጃጀትም ሆነ በሎጂስቲክ እየተጠናከሩ መጥተው ከግለሰቦች ባለፈ የጸጥታ አስከባሪዎችንም ሰለባዎቻቸው ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

ይሄን ብለን ከውጤቱ ወደ ምክንያቱ ስንመጣ የወንጀል ድርጊቱን ያስፋፋው አንድም የመንግሥት አቅም መላላት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኑሮ ውድነት ይመስለኛል፡፡ ማለትም የመንግሥት መዳከም አገር ውስጥ ሆነው የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ድርጅቶችን፣ ጸጥታ አደፍራሽ ሃይሎችን፣ ብሎም እስከ አመራርና ኮሚሽነር ድረስ የሚገድሉ ማፊያዎችን ሲፈጥር የኑሮ ውድነቱ ደግሞ በየአካባቢው የተደራጁ ዘራፊዎችን ቀፍቅፏል፡፡

ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ሥራ የሌለው ወጣት እራሱን ለመመገብ ይቅርና ለመጀዘብም ብዙ ብር ያስፈልገዋል፡፡ ከዓመታት በፊት እንደ ቀልድ የሚገባባቸውና የሚጀዘብባቸው የሱስ አይነቶች ዛሬ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ ሆነዋል፡፡

ፓኮው አራት ብር የነበረ ሲጋራ ዛሬ ሰባ ብር ሆኗል፡፡ በሁለት ብር ሲቃም የነበረ ጫት ከ50- 100 ብር የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በዚያን ጊዜ ሱስ የጀመረ ወጣት የሱስ ማገገሚያ ተቋም ከፍተው እስካላስገቡት ድረስ መቃሚያ ቤት ለመግባት ሥራ መሥራት ካልሆነም ደግሞ ማጅራት መምታት ይጠበቅበታል፡፡ የሱስ ዋጋ መወደዱ ወደ ሱስ ላልገቡት ወጣቶች በጎ ቢሆንም ትናንት ከቤተሰብና ከሰፈር ሰው በሚቀፍለው ገንዘብ ሱሰኛ የሆነ ወጣት ዛሬ ላይ ሱሱን ለማሟላት የሰፈሩን ሰው የሚዘርፍና ሕይወት የሚቀጥፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ስለሆነም እየተስፋፋ ያለውን ወንጀል ለመቀነስ በመንግሥት በኩል ለሥራ ፈላጊው ወጣት የሥራ እድል ማመቻቸት፣ ለሱሰኛው የማገገሚያ ማዕከል መክፈት ይጠብቅበታል፡፡ ከሆነ ድርጅት የተውጣጡ ታጣቂዎች ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ተከታትሎ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ አገር ውስጥ ሆነው የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎችን ሙሉ ለሙሉ ማክሰም፣ እንዲሁም በየጊዜው እያመረተ የሚያስመርቀው የጸጥታ ሃይል በመንግሥት ደሞዝ ለሕገ-ወጦች የሚታዘዝ እየሆነ ነውና በቂ ትኩረት ሰጥቶ ባግባቡ መገምገም ይኖርበታል፡፡ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ በሚል ሥም በየአካባቢው የተመደቡ ፖሊሶችም ከወንጀል በኋላ ማመልከቻ የሚቀበሉ ሳይሆኑ ከኮሚኒቲው ጋር ተግባብተው፣ አካባቢያቸውን አውቀው፣ ብሎም ጤነኛና ወንጀለኛውን ለይተው የሚንቀሳቀሱ መሆን ስላለባቸው እንደ አዲስ ሊፈትሻቸውና ሊያጠናክራቸው ይገባል፡፡

ካልሆነ ግን በመንግሥት ጥበቃ እምነት የማይሰማው ሕዝብ ሊያጋልጣቸው የሚፈልገውን ታጣቂዎች ሳይወድ በግዱ የሚደብቃቸውና የሚታዘዛቸው ይሆናል፡፡ ከጥበቃው በላይ ወንጀለኛው በበረታበት ምድር ላይ የሚኖር ማህበረሰብም እራሱን ከጥቃት ለመጠበቅ ለሕገ-ወጦች መሽቆጥቆጥ ግድ ይለዋል፡፡ በመሆኑም ሕብረተሰቡ እንደ ወትሮው ወንጀለኞችን የሚጋፈጥና ለሕግ አሳልፎ የሚሰጥ ይሆን ዘንዳ መንግስት ሕገ-ወጥነት የተስፋፋባቸውን የሥጋት ቀጠናዎች በመለየት ደጀን መሆን ይጠበቅበታል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top