Connect with us

የግብጽ ወደ ድርድር መመለስ ለመስማማት ወይስ?

የግብጽ ወደ ድርድር መመለስ ለመስማማት ወይስ?
Egypt’s President Abdel Fattah El Sisi on Wednesday has inspected construction work in some road and bridge projects in eastern Cairo – Press photo

ፓለቲካ

የግብጽ ወደ ድርድር መመለስ ለመስማማት ወይስ?

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ዳግም ለመቀጠል ግብጽ መስማማቷን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የሦስትዮሽ ድርድሩ በተጀመረበት ሂደት እንዳይከናወን የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመፍጠር በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫና ለማሳደር ስትጥር የከረመችው ግብጽ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ለመቀጠል መስማማቷን ይህንንም ይፋ ማድረጓ በብዙዎች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል። ግብጽ በቀጣይ ጊዜያት በሚደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች ለመሳተፍ ፈቃደኝነቷን የገለፀችው ከስምምነት ለመድረስ ወይስ እንደተለመደው ለሌላ ተግዳሮት ጊዜ ለመግዛት የሚል ጥያቄ ብዙዎች እያነሱ ነው።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስትቲዩት የፖሊሲ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ግርማ ተሾመ እንደሚሉት፤ ግብጽ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ እንዳትጠቀም ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በቅርቡ በዓለም ባንክና በአሜሪካ አደራዳሪነት የተካሄደው ድርድርም የዚሁ የግብጽ ሴራ አካል ነው። የዓለም ባንክና አሜሪካ በታዛቢነት ገብተው በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ፊርማ ለማስፈረም መሞከራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ በመጨረሻ ላይ የዓለም ባንክና የአሜሪካ አደራዳሪነትን አልቀበልም፣ ሉዓላዊነቴን አስከብራለሁ ብላ ጠንካራ አቋም በመያዟ ግብጽ አስባ የነበረው ነገር አልተሳካም። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚያ በኋላም አቋሙን በግልጽ በማሳወቁ ግብጾች የሄዱበት መንገድ እንደማያዋጣቸው ተረድተዋል።

ግብጾች ወደ ድርድሩ ለመመለስ የፈለጉበት በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ በአንድ በኩል እውነተኛ ድርድር በማካሄድ ከስምምነት ለመድረስ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን በዚህ ክረምት ጀምራለሁ ማለቷ ከምሯ እንደሆነ በመገንዘባቸውና ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ የያዘችውን ጠንካራ አቋም በመገንዘባቸው የውሃ ሙሌት ድርድር ሳይካሄድ እንዲጀመር ስለማይፈልጉ ወደ ድርድርና ውይይት መድረኩ ተመልሰው ለመደራደርና ከስምምነት ለመድረስ በማሰብ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ግብጾች ወደ ድርድሩ እንመለሳለን ያሉት እውነተኛ ድርድር አካሂደው ወደ ስምምነት ለመድረስ ነው የሚለው እጅግ አጠራጣሪ እንደሆነም ይናገራሉ ። እንደ ዶክተር ግርማ ማብራሪያ ሁለተኛው ቢሆን ግብጽ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ እንደነበረው ድርድር እስኪያልቅ በሚል ስበብ በቅርብ ርቀት ሆነው የግድቡን ግንባታና የውሃ ሙሌት ጊዜ ለማራዘም ሊሆን ይችላል። ግብጾች የግድቡን ግንባታ ለማዘግየት የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ኖረዋል። ድርድሮች በግብጾች ነው ሲደናቀፍ የነበረው። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮች ለግብጾች ጊዜ መግዣ ሆነዋል። ስለግድቡ መረጃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለአብሮነት ካላት ጽኑ ፋላጎት የተነሳ በተደረጉ ድርድሮች ከሚጠበቅባት በላይ መንገድ ሄዳ ለግብጾች ማድረግ ከሚገባት በላይ አድርጋለች የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ አሁንም ግብጾች በተመሳሳይ ድርድር በሚል የሆነ ጥቅም እናገኛለን የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በወለጋ ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ደሳለኝ ቶሌራ የዶክተር ግርማን ሀሳብ ይጋራሉ። ግብጾች ወደ ድርድሩ የተመለሱት አንድም ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጋር እውነተኛ ድርድር ለማካሄድ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ድርድር እናካሂዳለን በሚል ስበብ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ለመፍጠር ሊሆን ይችላል ይላሉ። ግብጾች ተመልሰው የመጡት ለእውነተኛ ድርድር ከሆነ እጅግ የሚያስደስት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥትም በደስታ የሚቀበለው መሆኑን ያነሳሉ።

እንደ ዶክተር ደሳለኝ ማብራሪያ ግብጾች ወደ ድርድሩ ለመመለስ የወሰኑበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ጊዜ ለመግዛት ይሆናል። ግብጾች ግድቡን ለማስቆም ብሎም የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። አገራትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከጎናቸው ለማሰለፍ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም ወደ ድርድሩ ለመመለስ የፈለጉት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የግድቡን ግንባታ እና የውሃ ሙሌቱን ለማስቆም የሚያደርጉት ጥረት እስኪሳካላቸው ድረስ ጊዜ ለመግዛት ሊሆን ይችላል።

በዓለም ላይ ብዙ አገራት ከጀርባ ሌላ ተግባር እየፈፀሙ ውይይት፣ ድርድር፣ እንዲሁም ስምምነቶችን ጊዜ ለመግዛት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነገር መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ደሳለኝ፤ ግብጽም ወደ ድርድሩ የተመለሰችው ለዚህ ሊሆን ይችላል ይላሉ። ኢትዮጵያን በድርድር ስበብ እያዘናጉ ሃያላን አገራትንና ተቋማትን በመጠቀም የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የምታደርገውን ጥረት ልትቀጥል እንደምትችል ይገምታሉ ። ሃያላን አገራትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመጠቀም ጫና ለማሳደር ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን አገር ውስጥ ያለውን ልዩነቶችን በመጠቀም አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ለማስገባትም ሊሰሩ ይችላሉ።

የፖሊሲ ጉዳዮች ተመራማሪው ዶክተር ግርማ ተሾመ እንደሚሉት ደግሞ፤ ድርድር ዳግም መጀመሩ መልካም ቢሆንም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባት። “ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብዙ ሄዳ ግብጾች ለመቀበል ሞክራለች”። ኢትዮጵያ ከሚመከረው በላይ ወደ ግብጽ ሄዳለች። ግብጾች ግን ከዛሬ ብዙ ዓመታት በፊት ይዘውት የነበረውን አቋማቸውን ዛሬም ይዘዋል። ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ግብጽ መጠጋት አይጠበቅባትም፤ አይመከርምም።

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የግድቡን ግንባታ ማፋጠን ላይ ማተኮር አለባት የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ የግድቡን ግንባታ ማፋጠንና የውሃ ሙሌቱን መጀመር ዋናው ጉዳይ ነው ይላሉ። የግድቡ መፋጠን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥቅም አለው። የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የመደራደሪያ አቅምም እየጎለበተ እንደሚሄድ አንስተዋል።

እንደ ዶክተር ግርማ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች ላይ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ ጠንካራ አቋም መያዝ አለባት። ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም ስትይዝ ግብጾች ጊዜ ለመግዛት የሚያደርጉትን ታክቲክ ያቆማሉ። ሌሎቹን በውሸት የሚደልሉበትንም ያቆማሉ። በቅርቡ በአሜሪካ መንግሥት ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ስምምነት ለማስፈረም ጥረት ሲደረግ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም የሚደነቅ ነበር። ኢትዮጵያ ያንን አቋም መያዟ ግብጾች ቶሎ ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ አስገድዷቸዋል። በቀጣይም መሰል አቋም መያዝ አለባት።

“ግብጾች ውሃው ክፍፍል ላይ ኢትዮጵያ ቃል እንድትገባላቸው እና እንድትፈርምላቸው ይፈልጋሉ።” የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ በዚህ ላይ ኢትዮጵያ መጠንቀቅ አለባት ይላሉ። ቀጣይ ትውልድን የሚጎዳ ድርድርም ስምምነትም ከማካሄድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ድርድሩ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ብቻ መሆን አለበት። ውሃ በስንት ጊዜ ይሞላል፣ ውሃ አለቃቀቅና ውሃ ይዘት ላይ ነው መሆን አለበት ይላሉ።

ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ አቋም እንድትይዝ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ ኢትዮጵያ ግድቡ ማንንም ለመጉዳት አይደለም። ለጋራ ተጠቃሚነት ነው። ውሃው የኔ ስለሆነ ብቻዬን ልጠቀም አላለችም።

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ሱዳንና ግብጽን የሚጠቅም ነው። የጋራ ተጠቃሚነት ሀሳብ ደግሞ ሁሌም አሸናፊ ነው። ኢትዮጵያ የያዘችው የጋራ ተጠቃሚነት አቋም ኢትዮጵያ ጠንካራ እንድትሆን የሚያደርግ አስተሳሰብ እንደሆነ አመልክተዋል ። የግድቡ መገባደድ በራሱ ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም እንድትይዝ ሌላኛው አስቻይ ሁኔታ ነው የሚሉት ዶክተር ግርማ ፤ ከአሁን በኋላ ግድቡ በምንም ሁኔታ ለድርድር በሚቀርብ ደረጃ ላይ አይደለም ይላሉ። የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው ዶክተር ደሳለኝ ቶሌራ በበኩላቸው፤ ግብጽ ወደ ድርድር ተመለሰች ማለት እርቅ ወረደ ማለት አይደለም። በአገራቱ መካከል ያለው የጥቅም ግጭት ተፈታ ማለት አይደለም። ለሺ ዘመናት ግብጾች በዓባይ ወንዝ ላይ የያዙት አቋም ተቀይሯል ማለት አይደለም። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በግብጽ ሁኔታ መዘናጋት የለበትም፤ ግብጽን ተስፋ አድርጎ አንድም ደቂቃ ማረፍ እንደማያስፈልግ አመልክተዋል ።

የግድቡን ግንባታ ከማፋጠን ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው የሚሉት ዶክተር ደሳለኝ፤ በተለይም አፍሪካዊያንን ከጎን የማሰለፍ እና ስለ ወንዙ እና ስለ ግድቡ የተዛበ አመለካከት ላላቸው አገራት እና ተቋማት እውነተኛውን መረጃ መስጠት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ይመክራሉ ።

እንደ ዶክተር ደሳለኝ ማብራሪያ፤ ግብጽ ወደ ድርድሩ ተመለሰች አልተመለች ከሚለው ይልቅ ኢትዮጵያ የቤት ሥራዎቿን በመሥራት ላይ ማተኮር አለባት። አገር ውስጥ ያሉ ልዩነቶች ለግድቡ ግንባታ አደጋ እንዳይሆኑ መንግሥት ከፓርቲዎች ጋር በቅርበት መሥራቱን መቀጠል አለበት። መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማወያየት በግድቡ ዙሪያ የጋራ አቋም መያዝም ወሳኝ ነው።

አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2012

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top