ህግና ስርዓት
ዘረኝነት እና አፀፋ-ዘረኝነት!
ዘረኝነት እና አፀፋ-ዘረኝነት!
RACISM AND COUNTER-RACISM!
(አሰፋ ኃይሉ)
“በሕይወቴ እንደ ሰው የሚያስቡ አህዮች አጋጥመውኝ ባያውቁም፣ እንደ አህያ የሚያስቡ ሰዎች ግን ብዙ አሉ!”
— ቤንጃሚን ፍራንክሊን
ዛሬ ደግሞ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ይሄ ሰው – በአደባባይ ጎዳና ላይ – በአራት የህግ አስከባሪ ጋንግስተሮች እንዲህ ተረግጦ፣ ሽንቱንና ለሃጩን በመሐል አስፋልት እስኪያዝረከርክ እንዲህ ክብሩ ተዋርዶ – በአደባባይ ሞተ፡፡ ወይም ተገደለ፡፡ በሜኒያፕለስ፡፡ ሚኔሶታ፡፡ አሜሪካ፡፡ ሰዎች ግን ምን ሆነናል? ትናንትናም አውሬ፡፡ ዛሬም አውሬ፡፡ ነገንስ ምን እንሆን ይሆን? አንድዬ ይወቅልን፡፡
በአሜሪካ የፖሊሶች የአደባባይ ግፍ የታወቀ የዕለት ጉርስ ከሆነ እጅግ ሰነባበተ፡፡ ብዙ መጻሕፍት ተጽፈውበታል፡፡ ብዙ ፊልሞች ተሰርተውበታል፡፡ ብዙ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደውበታል፡፡ በየዕለቱ ብዙ ሺህ አሜሪካውያን የፖሊስን አውሬ ተግባራት እየተከታተሉ በሚዲያ ለሕዝብ በማጋራት ላይ ተጠምደዋል፡፡ ነገር ግን ፍንክች የለም፡፡ ያው ነው፡፡
በተለይ የአሜሪካ ፖሊሶችን የጭካኔ ተግባር ይበልጥ አውሬያዊ የሚያደርገው በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ላለፉት 4 ክፍለዘመናት – በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁሮች – የፖሊሶች አውሬያዊ ድርጊት ሰለባዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ በብዙ ዓለማት ታሪክ ውስጥ ብዙ ዓይነት ሕዝቦች ባሮች ሆነው የተቆጠሩበት አሳዛኝ የገፈት ታሪኮች ቢኖሩም – ባርነት የሚባለው ክፉ ቀንበር ግን – በተለይ ጥቁሮችን እንደ ሰው ዘር በጥቁረታቸው ለይቶ ክፉኛ ሰለባው አድርጓቸው ኖሯል፡፡ ይሄ የማይካድ የታሪክ ሃቅ ነው፡፡
ቤልጂያኖች ኮንጎን ሲገዙ የጥቁር ባሮችን እጅ ቆርጦ ለአለቃው ሪፖርት ያላደረገን የቤልጂያን ፖሊስ ይቀጡ ነበረ፡፡ በኔዘርላንድ ጥቁር ባሮች ከዝንጀሮዎችና ከቺምፓንዚዎች ጋር የዱር እንስሳት መኖሪያ ውስጥ ገብተው ይጎበኙ ነበር፡፡ በአሜሪካ ጥቁሮች ለህክምና ምርምር ተግባር ውለዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የነበሩ የእንግሊዝ ዝርያ ያላቸው ነጮች በዘረጉት የአፓርታይድ ሥርዓት ጥቁሮችን በተራቡ ውሾች በአደባባይ አስበልተዋል፡፡ የሚገርመው የአሜሪካም ነጮች በ60ዎቹ የአሜሪካውያን ጥቁሮች የመብት ትግል እንቅስቃሴ ዘመን – ጥቁሮችን በሠለጠኑ ውሾች ማስነከስ የሚደሰቱበት ተግባር ሆኖ ታይቷል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ በአሜሪካ ጥቁሮች የማይገቡባቸው ክለቦችና የትምህርት ተቋማት ነበሩ፡፡ ማርቲን ሉተር በሕይወት በነበረ ወቅት አንድ የሆቴል ባለቤት ጥቁሮች እንዳይገቡብኝ ብሎ በከለከለው የሆቴሉ መዋኛ ጥቁር ሴቶች ሲገቡበት – እየሮጠ ሄዶ አደገኛ የሰልፈሪክ አሲድ ኬሚካል ሴቶቹ ባሉበት የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሲያንዠቀዥቀው የሚታይበት ምስል በመላው ዓለም በዘግናኝነቱ ታውቆ እስካሁን – የዘረኝነትን መልክ ለማየት ለሚፈልጉ ሁሉ እውነቱን ሳይደብቅ እየተናገረ – ለታሪክ አለ፡፡ በቅርቡ እንኳ ቻይኖች ለዓለም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በሥጦታነት ማበርከታቸውን ተከትሎ – በቻይና የሚገኙ ጥቁሮች አሰቃቂ ድብደባን፣ መገለልን፣ መታጎርን አስተናግደዋል፡፡
ጥቁሮች የታሪክ ባሮች ብቻ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ጥቁርነት መደፈርን፣ ጥቁርነት መረገጥን፣ መበደልን፣ መገደልን የሚያስከትል ነገር ከሆነ ሰነበተ፡፡ በአሁኑ ‹‹ሠለጠነ፣ በለፀገ፣ አደገ.. ወዘተ›› በሚባለውም ዓለም የጥቁሮች ባርነት ሊያበቃ አልቻለም፡፡ የጥንቶቹ ወደ አሜሪካ የተጋዙ የአሜሪካ ጥቁሮች እስካሁንም ለ400 ዓመታት ነፃ ያልወጡ ባሮች ተደርገው መቆጠራቸው አልቀረም፡፡ ባለፈው የትራምፕ ምርጫ ውድድር ላይ – ‹‹ዝንጀሮዎች የወሰዱብንን ዋይት ሃውስን ለዋይቶች እናስመልሳለን›› የሚል የምርጫ ቅስቀሳ – ‹‹ፕላኔት ኦፍ ዘ ኤፕስ›› ከተሰኘ ዝንጀሮዎች ዋይት ሃውስን ሲወርሩ ከሚታዩበት የሆሊውድ ፊልም ጋር እየተነጻጸረ በሚዲያ ሲናኝ ተመልክተናል፡፡
አሜሪካን ለትክክለኛ ባለቤቶቿ እናስመልሳለን – ማለት ‹‹ዓይን ያወጣ – ጥቁሮች የዚህች ሀገር ባለቤት ልትሆኑ አትችሉም›› የሚል ቅስቀሳ ግን በሠለጠነ ዓለም ላይ ሲሰማ … የምር ግን… ምን ማለት ነው? (ፊንፊኔን ለትክክለኛ ባለቤቶቿ ከማስመለስስ ይለያል? – አንዳች ያስመልስህ አቦ! ምኑን አምጥቶ ይቀላቅልብኛል በገብርዔል?!) እነዚያ ዘረኝነቶች የወለዷቸው ቅስቀሳዎችና ንግግሮች… ካውንተር ዘረኝነቶችና ተዛማጅ ዘረኝነቶች ሲታከሉባቸው ደግሞ አስባቸው – ሀገር እና ዓለም ምን ወደሚመስል የጥላቻ መንደርነት እየተቀየረች እንደምትመጣ፡፡ ቢለካ ቢቆጠር – ብዙ አለ ነገር፡፡ ካውንተር ዘረኝነትን – ኋላ ላይ እንመለስበት፡፡
‹‹50 ይርስ ኦፍ ፖሊስ ብሩታሊቲ ኢን ዘ ዩኤስ›› በሚል አንድ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ከ300 በላይ በአሜሪካ ፖሊሶች በንፁሃን ጥቁሮች ላይ የተፈፀሙ ግድያዎች፣ ድብደባዎች፣ ቶርቸሮች፣ እና በርካታ ግፎች በፎቶ ሁሉ ተደግፈው ተሰድረው እናገኛለን፡፡ ያ ሁሉ ሲሆን – ያ ሁሉ ገሃድ ሲወጣ – እንደ ሠለጠነ ሀገርና ማኅበረሰብ ሥርዓታቸውን ማሻሻል የሚጠበቅ የጨዋ ወግ ነው፡፡ ብዙዎች እየተንገፈገፉ እንደሚሉት ግን – ከጊዜ ወደ ጊዜ – የአሜሪካ ፖሊስ በጥቁሮች ላይ የሚፈጽው የዘረኝነት ተግባር – መጠኑ እየሰፋ፣ ጠላቻው እየገፋ፣ ጭካኔውም እየከፋ እንጂ – ከቶውኑም ሲቀንስ አልታየም፡፡
በተለይ ሆነ ብለው የነጭና የጥቁሮችን የዘር ልዩነቶች እንደ ፖለቲካ ስትራቴጂና እንደ ፖለቲካ ድጋፍ ወይም የድጋፍ ጎራ መፍጠሪያ ስልት አድርገው በሚጠቀሙት እንደእነ ዶናልድ ትራምፕ የመሰሉ መሪዎችና ፖለቲከኞች ወደ መንግሥት ሥልጣን መውጣት – ወትሮም የነበረውን ችግር ይበልጥ አባብሶታል – ነው የሚሉት ብዙ የመብት አቀንቃኞች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ‹‹የብላክ ላይቭስ ማተር›› የተሰኙት የአሜሪካ ጥቁሮችን መብት ተከታታይ ‹‹ዎች ግሩፕስ›› ወይም የጥቁር መብት ንቃት ንቅናቄዎች – በመላው አሜሪካ በየዕለቱ የሚከሰተውን የፖሊስ የዘረኝነት ተግባር እየተከታተሉ ያወጣሉ፡፡
እና በቃ… እነሱ የሚያወጡትን እውነት ቀን በቀን መከታተሉ ራሱ – ህሊናህን ያመዋል፡፡ በበኩሌ ብዙ ተከታትዬ፣ ተከታትዬ – በመጨረሻ ‹‹በቃኝ!›› ብዬ ተሰናብቼያቸዋለሁ፡፡ ከመናደድ – እና በአንተም ውስጥ ‹‹ካውንተር ሬሲዝም›› የሚባለውን ጥላቻ ከማሳደር ውጪ ምን ትርፍ አለው? ብዬ፡፡ ትርፍ የለውም፡፡ በእርግጥ ማየቴም፣ ማቆሜም ትርፍ የለውም፡፡ ግን ለምን ቆሽቴን አሳርራለሁ በገዛ እጄ – ብዬ እርግፍ!!
(ቢሆንም ግን አመል አያስችልህምና አልፎ አልፎ ማየት አይቀርም – እና አንዳንዴ ሳይ – በሠለጠነ ዓለም ያልሰለጠነው የአሜሪካ ፖሊስ – የህግ አስከባሪ ዩኒፎርም ለብሶ የሚፈጽማቸው – ጥላቻና ዘረኝነት የሞላባቸው የዕለት ዕለት ድርጊቶች – ልቤን ያሳምሙታል፡፡ ጤነኛ ህሊናን ያጨቀያሉ፡፡ የማታውቀውን ዓይነት የቁጭት ስሜት ይፈጥርብሃል! ሳትወድ በግድ፡፡ ሳትወድ በግድ – የዚያችን ሀገር በብዙዎች የሚወደስ የፍትህ ሥርዓት – እንድትፀየፍ ያደርግሃል፡፡)
ሁሉ የሰው ልጅ እኩልነት በተመሰከረባት ዓለም መኖር – የሰው ልጆች ተረት ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የሰው ልጅ የአዕምሮ ግንዛቤ በጊዜ ሂደት ይቀየራል የሚለው በብዙ ሰብዓዊያን ልብ ውስጥ አድሮ የነበረ ምኞት በብዙ ተሞክሮዎች ሲታይ ከሽፏል፡፡ ምኞቱ በተደጋጋሚ እንደጉም ሲተን ተስተውሏል፡፡ ብዙ ሰዎችን የሚቀናቸው – ከህሊናቸው ይልቅ – ቀልባቸው (ኢንስቲንክታቸው) ሆኗል፡፡ በሆነ የምወደው (ግን ደግሞ ዘረኛው) የእንግሊዝኛ የሀገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዶን ዊሊያምስ እንዳለው – አሁንም በዓለም – ጥቁር ጥቁር ነው፣ ነጭም ነጭ ነው፡፡ ብላክ ኢዝ ብላክ፣ ዋይት ኢዝ ዋይት፡፡ በተግባር የታየው ሃቅ ይሄ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡
አንድም ሥልጣኔ ዘረኝነትን እንዳላስቀረና እንደማያስቀር፡፡ ሁለትም ሠለጠኑ የተባሉት በቁስ የበለፀጉ ሀገራት ህዝቦች ብልፅግናቻ የቁስ እንጂ የህሊና ብልጽግና እንዳልተጠጋቸው ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ሥልጣኔያቸው የአዕምሮ ሥልጣኔ ቢሆን ኖሮ – መሠልጠን መሠይጠንን ያስቀር ነበር፡፡ ነገርግን እንዲያ አልሆነም፡፡ በሠለጠነው ዓለም ጥቁርነት የቆዳ ቀለም ከመሆን ውጪ ምንም ትርጉም አይኖረውም ብለው የተመኙ ሁሉ – ምኞታቸውን አፈር በልቶታል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በቅርብ የማውቀው አንድ ቅን አሳቢ (ግን ጮሌ!) የአዲሳባ ወዳጄ – ትውልደ እስራኤላዊ (ፈላሻ) ነኝ ብሎ – በትክክልም ሳይሆን አይቀርም – እስራኤል ሀገር ገባ፡፡ እና ከሶስት ወይ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ‹‹ናሽናል ሰርቪስ›› የሚባለውን ሰጥቶ – ብዙ ስኬታማ ህይወትን በእስራኤል አሳልፎ – የእስራኤል ፓስፖርትና ብዙ መሳጭ ታሪኮችን ይዞ – መጣ ወደ አዲሳባ፡፡ እና አፈላልጎ አገኘኝ፡፡ በአንዱ ጨዋታ ሲያወራልኝ ታዲያ – በእስራኤል – ልክ ከኢትዮጵያ እንደሄዱት ሁሉ – ከተለያዩ ሀገራትም የሄዱ ትውልደ እስራኤላውያንም ይኖራሉ፡፡ ብዙዎቹ አዲስ መጪዎች ተመሳሳይ ሰፈር ነው እንዲከትሙ የሚደረጉትም አለኝ፡፡
እና አንድ ቀን በአንድ መንደር ተጎራብተው በሚኖሩ ሁለት በዕድሜ በጎለመሱ ሴቶች መካከል ፀብ ተነሳ አለኝ፡፡ ከፖላንድ የመጣችው ትውልደ እስራኤላዊ – ከኢትዮጵያ ከመጣች ገጠር-ቀመስ ትውልደ እስራኤላዊ ጋር ነበረ አምባጓሮው፡፡ እና ገላጋይ ሆኖ መሐላቸው ገባ፡፡ ያውቅበታል ድሮም ማግባባት ሰውን፡፡ እና ግን የሆነውን ሲነግረኝ ጉድ አልኩ፡፡ ጠቡን ካበረደ በኋላ አንድ ትከሻዋን በወዳጅነት በእጁ ያዝ አድርጎ ወደ ቤቷ እያስገባት – የፖሊሿ ፈላሻ – ምን ትላታለች አለ የእኛዋን ፈላሻ?፡-
‹‹ይቺ ጥቁር ባሪያ! ደሞ ሰው ነኝ ብላ ከኔ ጋር
አፍ ትከፋፈታለች?! ከእሷ የበለጠ ይቺን (እያለች
የታቀፈቻትን ውሻዋን በአምስት ጣቶቿ እየደነቆለች)
ከእሷ ይቺ ውሻ ትሻላለች! ከእሷ የበለጠ ለዚች ውሻ
ትልቅ ክብር እንዳለኝ አላወቀችም!.. ይቺ ባርያ..!!››
እያለች ታወርደዋለች አለ የዘረኝነቱን መዓት፡፡ እና ምን ቢሆን ጥሩ ነው መጨረሻው? “አላስችል ስላለኝ.. እኔም ተደርቤ.. ሰድቤያት ተለያየን!” አለኝ፡፡ በሳቅ ነው የሞትኩት፡፡ ደግሞም አዘንኩ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን እንዲያ ያለውን የሞራል ጫና እያብኩ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት – በሀገረ እስራኤል – ኢትዮጵያውያን ለቀይ መስቀል የለገሱትን ደም መንግሥት ደፍቶት በመገኘቱ የተነሳ የተቀጣጠለው የኢትዮጵያውያን ፈለሾች ንዴት የተሞላበት የተቃውሞ ሰልፍ ትዝ ይለኛል፡፡ ያን ኋላ ይቅርታ ጠየቋቸው መሰለኝ፡፡ ከዚያም በኋላ ግን ምንም ያልታጠቀን ኢትዮጵያዊ ወጣት አንድ የእስራኤል ፖሊስ ቤቱ ድረስ ሄዳ ተኩሳ ገድላው ሌላ ተቃውሞም ተነስቶ እንደነበረ የምናስታውሰው ነው፡፡ ግን ምንድነው ይሄ ሁሉ? ዘረኝነት የወለደው ድርጊት ነዋ! ሌላ ምን ሊሆን ይችላል… ?
ያን የድሮ ጓደኛዬን… “አገላጋይ – እንዴት በጠብ ይደባለቃል?” ብዬው – እየሳቀ – “አንተ ብትሆን ከኔ ትብሳለህ አሴ ሙት!” ነበር መልሱ፡፡ እርግጥ እርሱን ያ “ናሽናል ሰርቪስ” የተባለ የሚሊቴሪ ሥልጠናና ግዳጅ ደመ-ቁጡ ካላደረገው.. እጅግ በጣም ትሁትና ሥርዐት የነበረው ልጅ ነበረ ሳውቀው፡፡ ግን በሰው ጠብ ተደባልቆ ተጣላ፡፡ ምክንያት? እውነትም እንዳለው – አትችለውማ የአንዳንዱን ዘረኝነት! በቃ ሰው ከሆንክ – አትችለውም! ሰው ከሆንክ – በቃ የሆነ ነገር ይሰማሃል፡፡ የሆነ ስሜት ይፈጠርብሃል!
የዘረኝነት ክፋቱምኮ ይሄው ነው፡፡ ዘረኝነት ከጉንፋንም፣ ከኢንፍሉዌንዛም፣ ከአተትም፣ ከኮሌራም፣ ከኮሮናም ይብሳል ከሰው ወደ ሰው ሲዛመት፡፡ ከሰው ወደ ሰው ሲጋባ፡፡ የዘረኛ ሰው ጥላቻ ክፋቱ ወደ ሌሎች መጋባቱ ነው፡፡ የዘረኛ ሰው ጥላቻው በውስጡ ከመሞላቱ ብዛት – ከውስጡ አልፎ በድርጊት መልክ ወደ ውጭ ገንፍሎ ሲወጣ – በዙሪያው ያለውን ሁሉ ያቆሽሻል፡፡ ይነካል፡፡ እና ደግሞ መጥፎው ነገሩ – ይጋባል!
በአሜሪካ ሀገር የነጮችን ዘረኝነት አምርረው የሚቃወሙ – ፍጹም ሰብዓዊና ሚዛናዊ ልብ የነበራቸው ብዙ ጥቁሮች – የዘረኝነትን ክፋቶች ከመከታተላቸውና ከመቃወማቸው ብዛት – በመጨረሻ ሳያስቡት እነሱም ነጮችን የሚጠሉ ጥቁር ዘረኞች ሆነው ተገላግለውታል፡፡ ‹‹ካውንተር ሬሲዝም›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውም ይሄ ነው፡፡ የሆኑ በጥላቻ የተሞሉ ዘረኞችን አምርረህ ስትጠላ – አንተም ውስጥ አፀፋዊ ዘረኝነት ያቆጠቁጥብሃል፡፡ ሳትወድ በግድ አንተም እነዚያን የምትፀየፍ ዘረኛ ትሆናለህ፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን – የጥቁር አሜሪካውያን ቁርጠኛ የነፃነት ታጋይ – ማልኮም ኤክስ ነው፡፡ ማልኮም ኤክስ በአንድ ‹‹አዎ ዘረኛ ነኝ!›› በሚል የታወቀ ንግግሩ፡-
‹‹ከሰው እኩል ልሁን ማለቴ ዘረኛ የሚያስብለኝ ከሆነ – አዎ ዘረኛ ነኝ፡፡
ጥቁርን የሚጠላውን ነጭ መጥላቴ – ዘረኛ ካስባለኝ – አዎ ዘረኛ ነኝ፡፡
ጥቁር የቆዳ ከለር ነው ጥቁርም እንደ ነጭ ሙሉ አዕምሮ፣ ሙሉ ክብር፣
ሙሉ መብት ያለው ሰው ነው ማለቴ – ዘረኛ ካስባለኝ – አዎ ዘረኛ ነኝ፡፡
አዎ እልም ያልኩ የጥቁር አክራሪ ዘረኛ ነኝ!››
– ነበር ያለው፡፡ በበመጨረሻ ማልኮም ኤክስ – የአሜሪካው ወጣት መሪ ጆን ኤፍ ኬኔዲ በሰው እጅ ተገደለ፡፡ እና ስለግድያው አስተያየቱን አንድ ጋዜጠኛ ጠየቀው፡፡ ማልኮምም እንዲህ ሲል መለሰ፡- ‹‹እውነቱን ልንገርህ? ለእኔ የኬኔዲ ሞት ምኔም አይደለም! ለእኔ የእርሱ ሞት የአንድ ነጭ መቀነስ እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም አይሰጠኝም!››፡፡ ካውንተር ሬሲዝም የምህልህ ይሄንን ነው በቃ፡፡ ማልኮም የነጮችን ዘረኝነት የወለደው ግፍና ጥላቻ ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ ሲከታተልና ሲያጠና፣ ሲያጥላላና ሲታገል ኖሮ – በመጨረሻ እርሱም ራሱ የዘረኝነቱ፣ የጥላቻው፣ የንቀቱ ሰለባ ሆነ!!
እና የጥላቻ የሚበክለው አየር – ንፁሁንም ሰው የጥላቻ ዓየር ወደ ውስጡ እንዲምግ ያደርገዋል፡፡ ትንሽ ጥላቻ ብዙ ጥላቻን ትዘራለች፡፡ አንዷ ዘረኝነት ብዙ ዘረኞችን ትወልዳለች፡፡ ዘረኝነት ያልተጻፈ የመንግሥት ፖሊሲ በሆነበት ሥፍራ ደግሞ – በተቃራኒ የዘረኝነት ጎራዎች በኩል በሚለቀቀው በጥላቻ የተበከለ ዓየር የተነሳ – ምን ሊፈጠር እንደሚችል እንግዲህ አስበው፡፡ ዕለት ዕለት በሚለቀቀው በጥላቻ የተበከለ አሳዛኝ ዜና የተነሳ ንፁኅ ሰዎች መተንፈሻ፣ መላወሻ ጥግ አጥተዋል፡፡ በብዙዎች እምነት – በአሜሪካ እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡
/በነገራችን ላይ በእኛም ሀገር የሆነውና እየሆነ ያለውኮ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ዘረኝነት ሰውን ከነነፍሱ እንደ ከብት ሲያሳርድ አይተናል፡፡ ሰውን ሰው ከነነፍሱ ሲያቃጥል አይተናል፡፡ ዩኒፎርም ያልገደበውን፣ የህዝብ ሥልጣንና ኃላፊነት ያልገደበውን ስንቱን ዓይነት ዘረኝነት እኛም ሀገር አስተናግደናል፡፡ ከሌላውም ሀገር ብሶ ጭራሽ በእኛ ዘንድ ዘረኝነት የመንግሥት ቅርፅ አግኝቶ በዘር ላይ የተመሰረቱ አንዱን ከሌላው የነጠሉና የሚነጣጥሉ ክልሎች ተመስርተዋል፣ ህጎች ወጥተዋል፣ ዘረኝነት የመንግሠት ወንጌልም ፖሊሲም ሆኗልኮ በእኛም ሀገር! እንዲያውም በዚያ አመቺ ዕድል ባገኘው ልክ በእኛ ዘንድ ዘረኝነትና ጥላቻ አለመኖሩም አንድም ለዘመናት የኖረና በቀላሉ ሊጠፋ ያልቻለ የህዝባችን ጨዋነትና ይሉኝታ ውጤት ቢሆን ነው – አሊያ ግን የፈጣሪ ተዓምር ነው ያስብላል በእውነት! ፈጣሪ ይመስገን በዚህስ! ሌላ ቀርቶ – እንደ አሜሪካና እስራኤልም እንኳ – ከሆነ በኋላም ቢሆን የሚጠይቅ አካል በሌለበትና ፍትህ ባልነገሰበት የዘረኞች መፈንጫ ሀገር – እኛንማ ከክፉ ጠብቆናል ፈጣሪ! ገና ወደፊትም ይጠብቀናል (ብለን ተስፋ እናደርጋለን)! /
– እውን ግን ሥልጡን የአሜሪካ ፖሊሶችን ከዘረኝነትና ከጥላቻ ያልጠበቀ አምላክ – እኛን ይጠብቀናል ግን? ሩዋንዳን ያልጠበቀ አምላክ፣ አሜሪካንን ያልጠበቀ አምላክ፣ እስራኤልን ያልጠበቀ አምላክ፣ ጎረቤት ሱዳንን ያልጠበቀ አምላክ፣ ግብፅን ያልጠበቀ ፈጣሪ አምላክ – ኢትዮጵያን ይጠብቃታል – ብሎ ማሰብ – ትንሽ – ከየዋህ ወደ በጣም የዋህነት እንደ መጠጋገት አይሆንብንም ግን?
– ግጥም አድርጎ እንጂ! አዎን ድብን ያለ የዋህነት ነው እንጂ! ታዲያ እየኖርን ያለነውስ በምን ሆነና? የዋህነታችን አድልቶ አይደለም ወይ? በየዋሃን እናት አባቶቻችን፣ በየዋሃን አያት ቅድመአያቶቻችን ቅንነትና መልካም ተግባር፣ ከየዋህ አንደበታቸው በፈለቀ ምልጃና ፀሎት እንጂ ጨርሰን ያልጠፋነው – እንደኛ ሥራማ – የአቅማችንን ስንት ጊዜ እየደጋገምን በዘረኝነት ጥላ ሥር ተመራርዘን – እርሰ በእርስ ለመጠፋፋት ያልወጣነው ዳገት ነበር`ንዴ?! አዎ እንድገመው፡፡ የምንኖረው – ያልጠፋነው – በፈጣሪ ቸርነት – በፈጣሪ ምህረት የተነሳ ብቻ ነው!
ፈጣሪ የዘረኝነትንም – የካውንተር ዘረኝነትንም ልክፍት – ከሀገራችን ይንቀልልን!
ጥላቻ ከዓለም ይጥፋ!
ዘረኝነት ገዢ አጥቶ ተበሳብሶ ይቅር!
ፍቅር ለዓለም ይሁን!
ሠላም፡፡
Attachments area