Connect with us

ህወሓት የለውጥ ኃይሉን ወነጀለ

ህወሓት የለውጥ ኃይሉን የአገርን ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ወነጀለ

ፓለቲካ

ህወሓት የለውጥ ኃይሉን ወነጀለ

ህወሓት የለውጥ ኃይሉን የአገርን ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ወነጀለ (ሙሉ መግለጫው እነሆ)
***

29ኛው ዓመት፣ የግንቦት 20፣ የድል ቀን በማስመልከት፣ ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!

ኢትዮጵያ ዳግም የብሄርና ብሄረሰቦች እስርቤት ፈፅሞ አትሆንም!! ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በማንም ምድራዊ ሐይል አይነጠቅም!!

ከሁሉ አስቀድሞ፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ እንኳን ለ29ኛው ዓመት፣ የግንቦት 20፣ የድል ቀን፣ በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን! የሚል መልእክት፣ በትግራይ ህዝብ ስም ሲያስተላልፍ፣ እንደ ትላንቱ ሁሉ፣ ዛሬም የጋራ ክንዳችን ኣፈርጥመን፣ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን አንኮታክተው፣ ሃገራችንን ብተና ኣፋፍ ላይ ያደረሱትን የጥፋት ሃይሎች፣ አደብ እንዲገዙ ሁላችን ተባብረን እንደምንንቀሳቀስ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግንቦት 20 በየዓመቱ እያከበሩ ዓመታት የዘለቁት፣ በዋነኛነት ብሄራዊ ክብራቸውና ማንነታቸው በጉልበት ተደፍቆ፣ በገዛ ሃገራቸው፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተደርገው የሚቆጠሩበት፣ በኣጭሩ ገዢዎቹ እግር ተወርች አስረው ባደረሱባቸው፣ ምህረት የለሽ ብዝበዛና ጭቆና ለችግር፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ እንግልት ስደትና ሞት፣ የዳረጉዋቸውን፣ ዘውዳዊ የመሳፍንትና የወታደራዊ ፋሽሽታዊ ደርግ ኣፋኝ ስርዓቶች፣ በዋነኛነት በቀድሞ ኢህኣዴግ እየተመሩ፣ በገጠርና በከተማ በዋጀው ደማቸውና በተከሰከሰ አጥንታቸው፣ የትምክህት ሓይሎች፣ ከመንበረ ስልጣናቸው አስወግደው፣ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች፣ የአርነት ችቦ አውለብልበው፣ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብቸኛ የሃገሪቱ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውንና ቀጣይ የህዳሴ ጉዞ ያወጁበት ቀን በመሆኑ ሁሌም በጉጉት ይጠባበቁታል፡፡

በመሆኑ በቅድሚያ ለዘመናት ተንሰራፍተው በቆዩት ኋላቀር ስርዓቶች የተፈጠሩትንን የተዛቡ ግንኙነቶች ለማረም እና የችግሩ ምንጮች ከእነሰንከፋቸው በመቅበር፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማክበር፣ አንድ የፖለቲካና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት እንዲቻል በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ማለትም ከ19 ሚልዮን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ የተሳተፈበት፣ በመጨረሻም መርጦ በላካቸው ተወካየቹ ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተደረገ በኋላ፣ በዴሞክራሲያዊ ኣኳሃን፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት፣ ህዳር 29/1987 ዓ/ም፣ ፀድቆና የሃገሪቱ የሁሉም ህጎች የበላይ ሕግ ሆኖ ሳይሸራረፍ 27 ዓመት ሙሉ ስራ ላይ ውሏል፡፡

በመሆኑም ሃገራችን ኢትዮጵያ በ2017 ዓ/ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ግልፅ ራእይ ተቀምጦ፣ በሃገራችን ሰላም እንዲነግስ፣ ዲሞክራሲ ስር እንዲሰድ እና ዙሪያ መለስ ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ፣ የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት መሰረታዊ እምነቶችና ምሶሶዎች መነሻ ያደረጉ፣ ኣራት ዓበይት ግቦችን ለማሳካት ወደር የለሽ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ ይኸውም ከሁሉም በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጎናፅፈዋል፡፡

በመሆኑም ከ1983 ዓ/ም እስከ 2008 ዓ/ም በነበረው ሩብ ክፍለ-ዘመን፣ በየአመቱ በአማካይ ስምንት በመቶ፣ በ1993 ዓ/ም የተካሄደውን ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ በነበሩት 15 ዓመታት ደግሞ በየዓመቱ ባለሁለት ኣሃዝ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ፣ በ1980ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ከድህነት በታች የነበረውን 48 ከመቶ ምጣኔ፣ በ2008 ዓ/ም ወደ 23 ነጥብ ሰባት ከመቶ ወርዷል፡፡ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችም ከድህነት ተላቀዋል፡፡ በሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ባለሃብቶቾም ተፈጥረዋል፡፡ የነፍስ – ወከፍ ገቢም ወደ 790 ዩኤስ ኣሜሪካ ዶላር ከፍ ብሎ ነበር፡፡ 45 ዓመት የነበረው በህይወት የመኖር አማካይ የዕድሜ መጠንን ወደ 66 ከፍ ብሏል፡፡ በትምህርት መስክ ከሁለት ዩኒቨርስቲዎች ተነስታ ሃገራችን የ45 ዩኒቨርስቲዎች ባለቤት ሁናለች፡፡ ይህም ከ110 ሚሊዮን በላይ ከሚገመተው ህዝቧ ሩብ ያህሉ ትምህርት ገበታ ላይ እንዲውል ሁነዋል፡፡

ባጠቃላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ እስከ ግንቦት 1983 ዓ/ም ድረስ በአለም በድህነት መዝገብ ሰፍረው ከነበሩት 10 ሃገራት ኣንዷ ነበረች፡፡ ሆኖም የደርግ ስርዓት ከተደመሰሰ ማግስት ጀምሮ በዋነኝነት ከግንቦት 20/1983 ዓ/ም በኋላ ባስመዘገበችው የሚጨበጥ የልማት ግስጋሴ በፍጥነት እያደጉ ካሉት 10 የዐለም ሃገራት መካከል በመጀመሪያ ረድፍ እንድትቀመጥ አስችሏት ነበር፡፡ ይህ የህዳሴ ጉዞና የግንቦት 20 ቱሩፋቶች በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥረት እና የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ህዝባዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የአመራር ብቃት ውጤት በመሆኑ፣ ሁላችንም ልንኮራበትና አንገታችን ቀና አድርገን በየትኛውም ጊዜና ቦታ በድፍረት የምንናገረው መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው፡፡

በመሆኑም ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው የቀድሞ ኢህኣዴግ፣ አልፋ-ኦሜጋ እምነት፣ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላዕላዊ የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጠው፣ በዋነኝነት ለተጋላጭነት የዳረገን ድህነትን የማስወገድ፣ ከየትኛውም የዓለም ጫፍ ሲዘነዘር የነበረውን የውጪ ጣልቃ ገብነት እና ተፅዕኖ ሳይንበረከክ፣ ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ የፖሊሲ ነፃነቱን ጠብቆ ተመፅዋትነት ለማስወገድ፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ ለማስፋፋት የሚረዳ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ ኣድርጓል፡፡ ባጭሩ የኢትዮጵያን አገራዊ ጥቅም የሚያረጋግጥ ነፃነቷና ሉኣላዊነቷ ክብሯ ከፍ የሚያደርግ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያማትር ማለትም ድህነትን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ ውስጣዊ ኣቅምን ለማጠናከር ምሰሶ የሆነውን የሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ያደረገ የደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፆ በመንቀሳቀሱ፣ ኢትዮጵያ፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏት ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ ለአመታት የራሳችን ሃብት እንዳንጠቀም የነበሩትን መሰናክሎች ጥበብ በተሞላበት የዲፕሎማሲ አካሄድ፣ ኣመራርና ትግል በመበጣጠስ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ለመገንባት አስፈላጊውን ሁሉ ተደርጓል፡፡ ባጭሩ የአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ከኣዲስ ኣበባ ለማስነሳት የነበረው ሴራም በማክሸፍ ሃገራችን በታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ እየተወከለች የአፍሪካ ቃል አቀባይ በመሆን፣ ጂ-7፣ ጂ-20 የሚባሉት መድረኮች ጨምሮ በተለያዩ የዐለም ኣቀፍ መድረኮች ኣሳማኝ፣ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብ የዐለም ጉፉኣን ህዝብ ጠበቃ መሆኗን በተግባር ኣሳይታ ነበር፡፡ በዋነኛነት ቀደም ሲል በታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ የተነደፈው የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ለማሳካት በተለይ የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ዩኤስ ኣሜሪካን ጨምሮ የዐለም ሃያላን መንግስታት በማሳመን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለማስፈረም በታላቁ መሪያችን ታጋይ መለስ ዜናዊ የተደረገው እልህ ኣስጨራሽ ትግልና የተመዘገበው ውጤት ታሪክ ለዘለዐለም ሲዘክረው የሚኖር ታላቅ ፍፃሜ ነው፡፡ ባጠቃላይ ሃገራችን የራሷ ኣቅምና ውስጣዊ ሰላሟ በማጠናከርዋ፣ እና የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት የመጨረሻ ዋልታና ማገር የሆነውን ህዝባዊ የመከላከያ ሰራዊት ገንብታ በዓለም ሰላም የማስከበር ተልእኮ ቁጥር አንድ ተመራጭ ሆና ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ የሚያስጎመጅ ግስጋሴና እድገት በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ኣልቀጠለም፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል በህዳሴ ጉዞ የተፈጠረውን የጠያቂ ህብረተሰብ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በወቅቱ ባለመመለሳቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ ኢህኣዴግ የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት ኣመለካከትና ተግባር የፈጠራቸውን ችግሮች ተንሰራፍተው በመቀጠላቸው ነው፡፡ በወቅቱ እነዚህ ችግሮች የለየው የቀድሞ ኢህኣዴግ ዳግም ጥልቅ ተሃድሶ ለማካሄድ ወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ከህወሓት በስተቀር የቀድሞዎቹ ኦህዴድ፣ ብኣዴን እና ደኢህዴን፣ የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ ባለማካሄዳቸው እንዲሁም ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ በቀድሞ ኢህኣዴግ ኣባል የነበረው እና የፌደራል መንግስት እያስተዳደረ ያለው ኣካል በ27 ዓመታቱ የትግል እና የድል ጉዞ ማለትም፣ በልማቱም በጥፋቱም መላ ኣካሉን ተነክሮበት የነበረውን ሂደት፣ ኣይኑን በጨው ዓጥቦ በመካድ ዓለም የመሰከረለትን እድገት ከል ከማልበስ ባሻገር ፣ የተጀመረው የህዳሴው ጉዞ ተንገራግጮ የኋሊዮሽ ለመመለስ በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል፡፡

ፋሽሽታዊ ወታደራዊ ደርግ ህዝቡ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ በጉልበት በመቀማት “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” ብሎ መንበረ ስልጣኑ በተቆጣጠረበት ማግስት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በቀይ ሽብር በየኣደባባዩ ረሽኖና ጨፍጭፎ ሃገሪቱ የደም እንባ እንድታነባ አደረጋት፡፡ ባጭሩ ደርግ ያደረሰው ግፍና ሰቆቃ በዋነኛነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ያለው የቀይ ሽብር ሰላባ የሰማእታት መታሰቢያ ሙዝየም ልብ ይሏል፡፡ ኣሁን የፌደራል ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው አካልም፣ “አካታችነት፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ አንድነት” ወዘተ በሚሉ ቃላት፣ ህዝብን እያማለለ ሳይውል ሳያድር፣ ከሶስት ሚልዮን በላይ ህዝብ ተፈናቀለ፣ በሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በፖለቲካዊ እምነታቸውና በማንነታቸው ብቻ በየእስርቤቱ ታጎሩ፡፡ በዓለም ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ፣ የሰው ልጅ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሁም በኣደባባይ ተዘቅዝቆ የሞተበት አረሜናዊ ተግባርም ተፈፀመ፣ ብሄር ተኮር ጥቃት በሰፊው ተካሄደ፣ ዜጎች በጠራራ ፀሓይ እየታፈኑ የገቡበት የማይታወቅበት ሁኔታ ተፈጠረ፣ ህዝብ ለህዝብ እንዳይገናኝ አውራ መንገዶች ተዘጉ፣ ባጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈፀመው ግፍ ዐይነቱና ብዛቱ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም ታሪክ መዝግቦታል እና እነዚህን ኣረሜናዊ የጭካኔ ተግበራት የመሩና በኣስፈፃሚነት የተሰለፉ ሁሉም መሪ ተዋንያንም ከተጠያቂነት ኣያመልጡም፡፡

ባጭሩ የፌዴራል መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ ስልጣን ቀምቶ፣ ከትግራይ ክልል በስተቀር የሁሉንም የክልል መስተዳድሮች በጉልበት አፍርሶ የራሱን ምስለኔዎች ተክቶ ሃገራችን ሰላም ርቋት፣ የስርዓት ኣልበኛ፣ የጎቦዝ ኣለቆችና ጠመንጃ ነካሾች መፈንጫ ሆናለች፣ ቢባል ማጋነን ሳይሆን መሬት ላይ ያለው እውነታ መግለፅ ነው፡፡

የፌደራል መንግስቱ ኢትዮጵያ ክብሯና ነፃነቷ በሚያዋርድ መልኩ የሃገሪቱን የፖሊሲ ነፃነት አሽቀንጥሮ ጥሎ ሁሉም የሃገሪቱ መግቢያ በሮች በርግዶ ለውጭ ሃይሎች አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የልማት ምሶሶ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ አየር መንገድ፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ የልማት ተቋማት፣ እንደ ተራ ሸቀጥ እንዲቸበቸቡ ለሽያጭ አቅርቦአቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሲባል የተጀመረ ነው፣ በቀጣይ አስር ዓመታትም አይጠናቀቅም፣ በማለት የኢትዮጵያን እድገት የሚወስነውና እያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ ዜጋ አሸራ ያረፈበትን ይህንን ግድብም ዓይኑ ሳያሽ በማን አለብኝነት ለድርድር አቀረበው፡፡ ይህንን ክህደቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማይቀበለው በተገነዘበበት ሰዓት ደግሞ፣ ደሮን ሲያታልሏት እንደሚባለው የግድቡ ተቆርቋሪ መስሎ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሆኖ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎቹ ነጋጠባ የአዞ እንባ ልፈፋውን ተያይዞታል፡፡ ይህንን እያደረገ ያለውም የተዘፈቀበትን ችግር ለመሸፋፈንና ኢትዮጵያውያን በየኣቅጣጫው እያካሄዱትን ያለውን ትግል በማደብዘዝ ኣጀንዳ ለማስቀየስ የተጠነሰሰ ሴራ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፌደራል መንግስቱ ከቆዩት የሃገራችን ኢትዮጵያ ወዳጅ የጎረቤት ኣገሮች ጋር አጋጭቶ፣ ከልማት አጋሮቻችንም አራርቆ የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ከማይመኙት፣ የቅርብና የሩቅ ሃገራት ያልተቀደሰ ግንኙነት መስርቶ፣ ሃገራችን ባለፉት 27 ዓመታት የገነባችው አወንታዊ ገፅታና የነበራት ዓለም ኣቀፍ ተቀባይነትና ተሰሚነት ተሽመድምዶ ደብዛው እንዲጠፋ ኣድርጓል፡፡

ተጠቃልሎ ሲታይ ልማት ሳይሆን ተመፅዋችነትና ልመናን መርህ ኣድርጎ የሚንቀሳቀሰው ይህ ኣካል፣ የሃገራችን ኢኮኖሚ መቀመቅ እያስገባው ይገኛል፡፡ ይኸውም በቀድሞ ኢህኣዴግ ዘመን ከፍተኛ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲጎርፍላት የነበረችው ሃገራችን ይህ ሓይል ወደ ስልጣን ከመጣበት ማግስት ጀምሮ ማለትም በአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ 17 ነጥብ ስድስት በመቶ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ቀንሷል፡፡ የገቢና የውጭ የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ሁኔታ ከመዛባቱ ባሻገር ወደ ውጭ የምንልከው የምርት መጠንም 48 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ቁጠባ ተዳክሞ ግብር የመሰብሰብ አቅምም ቁልቁል በመውረድ ላይ ይገኛል፡፡ በኣሁኑ ወቅት ሃገራችን 52 ነጥብ 3 ቢልዮን ዶላር የእዳ ቁልል አለባት፡፡ ይህም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት 59 ከመቶ መሆኑ ነው፡፡ በሚያዝያ ወር 2012 ዓ/ም፣ የአገሪቱ የዋጋ ንረትም 26 ከመቶ ደርሷል፡፡ የስራ አጥነት ቁጥሩ በመጨመር ላይ ነው፡፡ በኣሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ያለው የስራ ኣጥ ቁጥር 19 በመቶ መድረሱ የኢኮኖሚ ሙሁራን በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡

ባጭሩ የፌደራል መንግስቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በማንኣለብኘት የሃገራችን ሃገራዊ ክብርና ጥቅም በስውር እና በግላጭ ለባዕድ ሓይሎች ኣሳልፎ ከመስጠት ባሻገር የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ ስልጣን ቀምቶ ኣምባገነን መሆኑን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግስቱ በጀመረዉ አካሄድ ከቀጠለ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ እንደሚሆን ንፁህ ህሊና ላለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ ኣይደለም፡፡

የተከበርክ የትግራይ ህዝብ !!

አፋኙ የደርግ ስርዓት ለማስወገድ፣ ታሪክ ለዘለኣለም የሚዘክረውን አኩሪ ተግባር ፈፅመሃል፡፡ ባጭሩ የልብህ ስላደረግክ፣ የምታፍርበት ሳይሆን የምትኮራበት የድንቅ ገድል ባለቤት በመሆንህ ሁሌም ክብርና ሃሴት ሊሰማህ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው ለከፈልከው ወደር የለሽ መስዋእትነትም ከማንም ካሳ ኣልጠየቅክም፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም የተለየ ጥቅም አላገኘህም፡፡ ሆኖም ከማንም በላይ ሰትመኘው የነበረው ሰላም፣ ደምህና ኣጥንትህን ገብረህ ባሰፈንክበት ማግስት፣ በጥረትህና በላብህ ብቻ የግንቦት 20 ፍሬዎች ተቋዳሽ ሆነሃል፡፡ በመሆኑም በግብርና የተሰማራው ህዝባችን ከረሃብና እንግልት ደረጃ በደረጃ እየተላቀቀ የአቅሙን ያህል ሀብትና ንብረት ቋጥረዋል፡፡ በመቋጠርም ይገኛል፡፡ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ባሳየኸው ድንቅ ተግባር ለምድራችን ተምሳሌት በመሆን ዓለምኣቀፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በጥቃቅን እና ኣነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጀው ህዝባችንም የልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡ ባጠቃላይ ህዝባችን መንገድን ጨምሮ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ካስከፊ ድህነት ባለመላቀቃችን ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

የትግራይ ህዝብ በትጥቅ ትግሉም ይሁን ባለፉት 27 ዓመታት ላበረከትከው ኣስተዋፅኦ፣ የፌዴራል መንግስቱ ክዶ ጥላሸት ቀብቶ፣ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት እና ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ይጠበቅ፣ የህግ የበላይነት ይከበር ስላልክ ብቻ ብሄር ተኮር ጥቃት፤ እስራት፣ እንግልት፣ መድልዎ፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ፈጽሞብሃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሉአላውነትህ መገለጫ የሆነውን 6ኛው ዙር ምርጫ አካሂዳለሁ ስላልክ ብቻ ትጨፈለቃለህ፣ እናቶች ተጠንቀቁ ደም ይፈሳል በማለት አስፈራርቶሃል፡፡ ሆኖም የራስን የማስተዳደር ጉዳይ ለማንም አሳልፈህ እንደማትሰጥ፣ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ መሆኑ የትምክህት ሓይሎችም ኣበጥረው ያውቁታል፡፡

በአጭሩ የትምክህት ሓይሎች አሁንም ህልውናህንና ማንነትህን ለማጥፋት የማይፈነቅሉት ድንጋይና አለት ኣይኖርም፡፡ ስለዚህ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጎን ተሰልፈህ ያከሸፍካቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሴራዎች፣ አሁንም አንድነትህ እንደብረት አጠንክረህ እንደምትመክታቸው አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኮረና ቫይረስ፣ የበረሃ ኣንበጣ እና የኣሜሪካ ባርኖስ በመመከት ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ በግንቦት 20 የተጎናፀፍካቸውን ዘርፈ ብዙ ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ባአጠቃላይ በተሰማራህበት የስራ መስክ በተለይም የ2012/13 ዓ/ም የኣዝመራና ሌሎች የክረምት ወቅት ስራዎችን ለማሳካት እንደምትረባረብ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይተማመናል፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የፌደራሊስት ሃይሎች!

የማንነታችን መገለጫ የሆነው ሕገ-መንግስታዊ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በመፈራረስ ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ ወደ ባርነት የሚመልሰንን አሃዳዊ የግዛት አንድነት ከመቃብር አውጥቶ ዳግም ለመመለስ ሩጫው ተጧጥፏል፡፡ ነገር ግን ይህ እውን እንደማይሆን የጋራ ድምፃችን የምናሰማበት ወቅት አሁን ነው፡፡ በዚህ ኣጋጣሚ የፌዴራል መንግስቱ የትግራይ ህዝብና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስቱን፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለማጋጨት የሸረበውን ሴራ እና ያሰራጨው ሓሰተኛ የበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ እንዲከሽፍ የበኩላቹሁን ድርሻ ስላበረከታቹሁ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በትግራይ ህዝብ ስም ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲ፣ መሪዎችና ሙሁራን!

አገራችን ኢትዮጵያ ገደል ኣፋፍ ላይ መድረሷ በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ፣ የኮሮና ቫይረስ ሰበብ አድርጎ፣ የስልጣን ዘመኑ ለማራዘም ላይ ታች በማለት ላይ ነው፡፡ በእርግጥ የኮሮና ቫይረስ አደገኛና ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ለዚህም ነው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከፌደራል መንግስት ኣስቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ኮረና ቫይረስን በመመከት ላይ ያለው፡፡ ስለዚህ ኮሮና ቫይረስን በጋራ እየመከትን ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በጋራ እንድንንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተከበርክ የኤርትራ ህዝብ!

በቅድሚያ ከ30 ዓመታት መራራ ትግል በኋላ ነፃነትህ ለተጎናጸፍክበት 29ኛው ዓመት ግንቦት 16፣ እንኳን በሰላም ኣደረሰህ! ኣደረሰን! እያልን፣ ተጀምሮ የነበረውንና በሁለቱ አገር መሪዎች ግልፅ ያልሆነ ግንኙነት ሳንካ የገጠመውን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩልህ አስተዋፅኦ እንድታደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የዓለም-አቀፍ ማህበረሰብ!

በፈጣን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ የእድገት ምህዋር ገብታ የነበረችውና ተስፋ ተጥሎባት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት አልባ የመሆን ዳር ላይ ደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያ መበታተን ማለት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ እና የቀይ ባህር አካባቢ የትርምስ ቀጠና በማድረግ፣ ከ60 በመቶ በላይ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ እንዲገታና ያሸባሪዎች መፈንጫ እንዲሆን መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ተረድታችሁ ለጋራ ጥቅም ሲባል የመፍትሔ አካል እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ታሪክ ራሱ ይደግማል እንደሚባለው፣ የፌደራል መንግስቱ እንደ ወታደራዊ ደርግ አምባገነን መሆኑ እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከአሁን በኋላ፣ ኢትዮጵያ ዳግም የብሄርና ብሄረሰቦች እስርቤት ፈፅሞ አትሆንም! ራስን በራስ የማስተዳደር መብትም በማንም ምድራዊ ሓይል እንደማይነጠቅ ወዳጅም ጠላትም ሊያውቅ ይገባል፡፡ አሁንም መስመራችንን ኣፅንተን እንመከታለን!!

ዘላላማዊ ክብር ለትግሉ ለወደቁ ታጋዮች!!
የግንቦት 20 ትሩፋቶች ወደላቀ ከፍታ እናሸጋግራለን!

(ምንጭ :-የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ፡ግንቦት 19/2012 ዓ/ም)

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top