Connect with us

የካናዳውያን ህገመንግሥት የሥልጣን ጊዜን ስለማራዘም ምን ይላል?

የካናዳውያን ህገመንግሥት የሥልጣን ጊዜን ስለማራዘም ምን ይላል?

ህግና ስርዓት

የካናዳውያን ህገመንግሥት የሥልጣን ጊዜን ስለማራዘም ምን ይላል?

የካናዳውያን ህገመንግሥት የሥልጣን ጊዜን ስለማራዘም ምን ይላል?

– ዲሞክራሲ እና ሥልጣን፣ ብዙሃን እና ህዳጣን፣ መዋደድ እና መጓደድ*
(አሰፋ ኃይሉ)

የካናዳ ህገመንግሥት ስለ ምርጫ ማራዘም የሚያስቀምጠው መርህ ቁርጥ ያለ ነው፡- የሕዝብ ወኪሎች የሥልጣን ዘመን ከሚያበቃበት የ5 ዓመት ጊዜ ማራዘም አይቻልም! የሚል፡፡ ነገር ግን ይህ በልዩ ሁኔታ ሊጣስ የሚችልበትን ምክንያት እና የሕዝብ ተወካዮችና ህግ አውጭ ምክርቤት አባላት የሥልጣን ጊዜ በምን አኳኋን እንደሚራዘም በአጭርና በግልጽ መልክ ያስቀምጣል፡፡

በዚሁ መሠረት የካናዳውያኑ የሕዝብ ተወካዮች ሥልጣናቸው ሊራዘም የሚችለው ጦርነት ካለ፣ ወይም የጦርነት ስጋት ካለ፣ ወይም ወረራ ካለ፣ ወይም አመጽ ከተቀጣጠለ ነው፡፡ ታዲያ ካናዳውያኑ በታሪካቸው የተወካዮችን ምርጫ ያራዘሙት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ1916 በ1ኛው የዓለም ጦርነት መካከል መካሄድ የነበረበት የካናዳውያኑ ምርጫ ነበረ፡፡ እርሱም ለ 1 ዓመት ተራዝሞ ግን በቀጣዩ ዓመት በ1917 (ጦርነቱ ሳይገባደድ) ምርጫው እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡

የካናዳውያኑ ህገመንግሥት በሀገራዊ ወረርሽኝ የተነሳ የፓርላማ አባላት የሥልጣን ጊዜ ከተመደበለት ዓመት በላይ መራዘም ይችል እንደሆነ የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ህገመንግሥታቸው ለዚህ ዝግ አይደለም፡፡ አጨቃጫቂ ነገር ሲገጥማቸው ለትርጉም ወደ ፍርድቤትና ወደ ሪፈረንደም መሄድ የሚችሉበት ህጋዊ አሠራር ዘርግተዋል፡፡ የሥልጣን ጊዜ ግን በካናዳ ዝም ብሎ በህዝብ ተወካዮችና ህግ አውጭ ምክርቤቶች አብላጫ ድምፅ ብቻ አይራዘምም፡፡ ሥልጣን የሚራዘምበትን አኳኋን ህገመንግሥታቸው በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ ከዚያ ውልፍት የለም፡፡ ያ ስትሪክት ፕሪከንዲሽን ምንድነው?

በካናዳ የሥልጣን ጊዜን ማራዘም የሚቻለው በአንድ ቅድመ-ሁኔታ ነው፡- ከሁለቱ ምክር ቤቶች ውስጥ በአንደኛቸው ካሉ የፓርላማ (የምክር ቤት) አባላት ውስጥ – 1/3ኛው (ቁጥራቸው ከምክር ቤቱ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ የሕዝብ ተወካዮች) – የሥልጣን ጊዜ መራዘሙን ከተቃወሙት – የሥልጣን ጊዜን ማራዘም ፈጽሞ አይሞከርም!

ያ ማለት ምን ማለት ነው? አብዛኛውን መቀመጫ የያዘው ገዢው ፓርቲ – የሥልጣን ዘመናችንን ላራዝም ነው – ብሎ ያቀረበው ሃሳብ በህግ አውጭና በህግ መወሰኛ ምክርቤቶቹ ድምፅ እንዲሰጥበት ያቀርበዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ያን ሲያደርግ ግን – አብዛኛውን መቀመጫ ያልያዙ አናሳ ወንበር ያላቸው (ቁጥራቸው የፓርላማውን 1/3ኛ የሚሞላ) ተወካዮች ከተቃወሙት – ምርጫውን ማራዘም አይችልም! ስለዚህ የካናዳውያኑ ህገመንግሥት – እውነተኛ ዲሞክራሲ በተግባር ላይ እንዲውል ተደርጎ ዲዛይን የተደረገ ነው!

በካናዳውያኑ ህገመንግሥት በተዘረጋው ልዩ ሁኔታ መሠረት – አብላጫ ድምፅ ያለው ፓርቲ ገና ለገና አብላጫ መቀመጫ አለኝ ብሎ ብቻውን የሥልጣን ዘመኑን ማራዘም አይችልም፡፡ የግዴታ አነስተኛ ወንበር ያላቸውንም ወኪሎች ጭምር ዓላማውን አስረድቶ፣ አግባብቶ፣ አሳምኖ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህን ካላደረገ – ይህን 80 በመቶውን የህዝብ ወኪል የማሳመን ሥራ ካልሰራ – ከሁለቱ ምክር ቤቶች በአንዳቸው ውስጥ ያሉ ጥቂቶቹ 34 ፐርሰንቶቹ – የሥልጣን ይራዘምልኝ ፕሮፖዛሉን ውድቅ ሊያደርጉበት ይችላሉ፡፡

እና በዚህ አንፃር ሳየው የካናዳውያኑን ህገመንግሥት በዓለማችን የዲሞክራሲን መሠረት በመጣል የታወቁ አንቱ የተሰኙ ቀደምት የዓለማችን አሳቢዎች እነ ጆን ሎክ፣ እነ በርክሌይ፣ እነ ዴቪድ ሂዩም፣ እነ ዣን ዣክ ሩሶ፣ እነ ጆን ስቱዋርት ሚል፣ እነ ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ፣ እነ ቶማስ ጄፈርሰን፣ እነ ቶማስ ፔይን፣ እነ ዣን ሚስሊዬ፣ እና ሌሎችንም የዐለማችን ድንቅ ቀደምት የስነመንግሥትና የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ጉምቱ ሊቃውንት እስካሁንም ተጠብቀው በቆዩ በተለያዩ ዘመን አይሽሬ ሥራዎቻቸው ውስጥ ደግመው ደጋግመው ያሏቸውንና ያሳሰቧቸውን የዲሞክራሲ መርሆዎች በተግባር ለማዋል ከፍ ያለ ጥረት ያደረገ ህገመንግሥት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

እነዚያ ጉምቱ የዓለማችን የዲሞክራሲ አራማጅ ቀደምት ሊቃውንት እንደሚሉትና እንደሚያሳስቡት – ዲሞክራሲ ማለት – በብዙሃን የሚመራ – እና ግን – የህዳጣንንም (ማለትም የጥቂቶችንም) ስምምነት፣ መብትና ፍላጎት ያከበረ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ጆን ስቱዋርት ሚል የተሰኘው የዓለማችን ታላቅ የዲሞክራሲ ሊቅ እጅግ ታዋቂ በሆነለት ‹‹ኦን ፍሪደም›› በተሰኘ ሥራው ውስጥ እንዲህ በማለት አስቀምጦት እናገኛለን፡-

‹‹ለምሳሌ እንበልና አንድ ሚሊዮን ሰዎች ቢኖሩና፣
ከአንድ ሚሊየኑ ሰዎች 999,999 የሚሆኑት ሰዎች
አንድ ዓይነት ሃሳብ ቢኖራቸው፣ እና እነዚያ ከእነርሱ
የተለየ ሃሳብ ያለውን የአንዱን ሰው ሃሳብ ጨፍልቀው
የሚፈልጉትን ነገር ቢያራምዱ፣ ይሄን እኔ የምመለከተው
‹‹ያ አንዱ ሰው ጉልበት ቢኖረውና የ 999,999ኙን
ሰዎች ሃሳብ ጨፍልቆ የራሱን ሃሳብ ብቻ ቢያራምደው
ኖሮ የሚሰማኝን ያንኑ ተመሳሳይ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡
ብዙዎቹ አንዱን መጨፍለቃቸው እና አንዱ ብዙዎቹን
መጨፍቁ ለእኔ ከቁጥር የሚገባ ነገር አይደለም፡፡
ሁለቱም ለእኔ አንድ ናቸው፡፡ ዲሞክራሲ – ብዙሃን
የህዳጣንን ሃሳብ የሚጨፈልቁበት ሥርዓት ሳይሆን፣
ብዙሃንና ህዳጣን ወደሚያቀራርባቸው መካከለኛ
መንገድ በመምጣት በውይይት የሚገናኙበት
የሰው ልጆች ህሊናና እውነት ገዢ የሆኑበት
ታላቅ የጋራ ቃልኪዳን አማካይ ሥፍራ ነው..››

 

በማለት ይናገራል፡፡ እና እነዚያ ዲሞክራሲ ሀገርን በአሸናፊና ተሸናፊ መንገድ ለመምራት የተፈጠረ የመንግሥት አስተዳደር ሲስተም ሳይሆን – ሀገርን በውይይትና በመረዳዳት (በመግባባት) ላይ ተመስርቶ ለመምራት የተፈጠረ ሁነኛ ሀገራዊ የኮምፕሮማይዝ መንገድ (ማለትም የመመቻመች – የመግባባት – አንተም ተው አንተም ተው የመባባል – እርቅና ህብረትን የመፍጠሪያ) መንገድ ነው፡፡ ካናዳውያኑ በተግባር ህገመንግሥታቸው ላይ አስቀምጠው ያየሁት ይህን ታላቅ የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ መሰለኝ፡፡

 

ከላይ እንደገለጽኩት አብዛኛው የህዝብ ተወካዮች ወይም የህግ መወሰኛ ምክርቤት ድምጽ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም በህዝብ ተመራጭ የሆነ ብዙሃኑ አካል “ሥልጣናችንን አራዝማለሁ!” ብሎ ይነሳል፡፡ ወይም እንዲራዘም ይጠይቃል፡፡ ግን የሚያራዝመው ጥቂቶች እስካልተቃወሙት ድረስ ብቻ ነው!! ያ ተቃውሞ ከጥቂቶችም ቢሆን እንዳይነሳበት፣ እና ያን የሚፈልገውን የሥልጣን ማራዘም ለማምጣት የሚያበቃውን የብዙዎችን ስምምነት ለማግኘት ሲል – ዶሚናንቱ ፓወር ሆልደር – እነዚያን ጥቂቶችን የህዝብ ተወካዮች ደግሞ ደጋግሞ ማወያየት፣ ማነጋገር፣ ማግባባት፣ ማስማማት ይኖርበታል፡፡

– ሃሳቡን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲያመጣና፣ ሁሉም ወገን ሃሳቡን በጋራ አዎንታ ላይ ወደ ተመሠረተ የድርድር ውጤት ለማምጣት ይገፋፋል ወይም ይገደዳል፡፡ ዲሞክራሲ ይሉሃል ይሄ ነው! በካናዳ የምታገኘው ይሄንን ነው፡፡ እና በዚህ የዲሞክራሲን ቲዎሪንና ተግባርን አስታርቀው – በዲሞክራሲ ለመኖር በነደፉት ህገመንግሥታዊ ነገራቸው – ከልብ አስደምመውኛል፡፡

 

ምናልባት እኛም ሀገር እግዜር አድሎን አንድ ቀን – እውነተኛ ዲሞክራሲን ያነገበና የዲሞክራሲን መርሆዎች በእውነት ለመተግበር የቆረጠ ታላቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የጋራ ስምምነት ውጤት የሆነ – ወርቃማ ህገመንግሥት በሚኖረን በአንድ እግዜር ባለልን ቀን ላይ – ምናልባት ይሄ የካናዳውያኑ የዲሞክራሲ ተሞክሮ መንገድ – ጥሩ አርዓያ ሆኖን ህገመንግሥታችንን በዚያ ዓይነቱ መንገድ ለመቅረፅና፣ ከዚያም አልፈን እነርሱ ያልደፈኑትን ቀዳዳም ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚደፍን መፍትሄን ያመላከተ – አስደማሚ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግሥት – ውብ አድርገን በወርቃማ ልቦናና በወርቃማ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ማሻሻል እንችል ይሆናል – የሚል የበዛ ምኞት አለኝ፡፡ ማን ያውቃል?

‹‹ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?››

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

__________________________
Photo: The Constitution Act of Canada, 1982, Schedule-B (Photo by Assaf H. Dossegnaw, 24 May 2020).

“መጓደድ” — መኵራት ፡ መደገግ ፡ መታበይ ፡ መታጀር፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top