ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ ማብራሪያ
***
በኢትዮጵያ አየር መንገድ መልካም ስም ላይ በተለያዩ ጊዜያት ለሚነዙ የፈጠራ ዘገባዎች የተሰጠ ማብራሪያ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን መልካም ስም እና ዝና ለማጠልሸት ጥቂት የቀድሞ ሠራተኞች በነበሩ ግለሰቦች እና በአዲሱ ማህበር የቀድሞ ጥቂት አመራሮች አስተባባሪነት እየተደረገ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ አየር መንገዱንና አስተዳደሩን የማይገልፅ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።
አየር መንገዱ እንደ ማንኛውም ድርጅት የውስጥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚፈታበት አሰራር ያለው ሲሆን እነዚህም የውስጥ ጉዳዮች የሚፈቱት በድርጅቱ ባሉ አሰራሮች እና በሕግ በተቀመጡ መንገዶች ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የተወሰኑ የሚዲያ ተቋማት እና ባለቤቶች የድርጅቱን አስተዳደራዊ ጉዳዮች በመቀበል በድርጅቱ ጉዳይ ላይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እያደረጉ ይገኛሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድርጅታችን ላይ በሚነሱ አሉባልታዎች ዙሪያ እውነቱን መናገር ተገቢ በመሆኑ ጉዳዩን እንደሚከተለው ለማብራራት እንወዳለን።
ይህንን የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱት በሀገር እና በአየር መንገዱ ላይ ከፍተኛ ጥፋት የፈፀሙና በዚህም የተነሳ ከድርጅቱ የተሰናበቱ ሠራተኞች ናቸው። አንዳንዶቹ በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ውስጥ የነበሩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከድርጅቱ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በጥያቄያቸው መሠረት ድርጅቱ ያካበቱትን የሥራ ዕውቀትና ልምድ ለወጣቱ ትውልድ እንዲያካፍሉ እንደገና በኮንትራት የቀጠራቸው እና የወጡ ግለሰቦች ናቸው።
1. የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስር ቤት የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም
የእስር ቤት ጉዳይን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት አንዳንድ ግለሰቦች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስር ቤት አለው በማለት ፍፁም ውሸት የሆነና ህዝቡን የሚያደናግር ተራ ወሬ ሲያሰራጩ ይስተዋላል።
ህዝቡ እንዲያውቀው የምንፈልገው፣ በማንኛውም ሀገር እንዳለ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ በርካታ ህግ አስከባሪ የመንግስት ተቋማት አሉ። እነዚህም የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ ደህንነት እና መረጃ አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽን ባለስልጣን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ሕግ የማስከበር ተልዕኮ የተሰጣቸው በመሆኑ ሕግ ያስከብራሉ። ስለዚህም ማንኛውም ሠራተኛም ሆነ መንገደኛ የሀገሪቱን ህግ አክብረው እንዲሰሩ እንዲሁም እንዲዘዋወሩ ይጠበቃል።
ይህንንም ህግ ለማስከበር እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በፌዴራል ፖሊስ ሥር የሚተዳደሩ የዋናው ጣቢያ ቅርንጫፍ የሆኑ ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ማለትም አንደኛው የሀገር ውስጥ ተርሚናል አካባቢ፣ ሁለተኛው ደግሞ በአለም አቀፍ ተርሚናል አካባቢ የሚገኙ ሲሆን ሁለቱም ፖሊስ ጣቢያዎች በግልፅ በሚታይ ቦታ የሚገኙ፣ በበርካታ ሰዎች እይታ ውስጥ ያሉ እንጂ የተደበቁ አይደሉም። በዚህ ጉዳይ ላይ ማንኛውም አካል ወይም ሚዲያ የሚመለከታችውን ተቋማት እና የፀጥታ አካላት መጠየቅና ማጣራት እየቻለ የአየር መንገዱን እንዲሁም የፀጥታ አካላትን ስም በሚያጎድፍ መልኩ የአሉባልታ ጋጋታ ማዝነቡ እጅግ አሳፋሪ እና በህግ ጭምር የሚያስጠይቅ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።
የአየር መንገዱ ሰራተኞች ማንኛውንም ጥፋት በሚያጠፉበት ጊዜ አስተዳደራዊ እርምጃ በህጉ መሰረት የሚወስድ ሲሆን ከዚህ ውጪ የሆኑ የወንጀል ድርጊቶች በአየር ማረፊያው አካባቢ ሲፈፀሙ እና የአየር መንገዱ ሰራተኞችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች (መንገደኞችን ጨምሮ) በጥፋተኝነት ሲጠረጠሩ ከላይ የተገለፁት የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ለህግ እንዲቀርቡ ያደርጋሉ። ስለሆነም የአየር መንገዱ ሰራተኞች በወንጀል ተጠርጥረው በፀጥታ አካላት ምርመራ ሲደረግባችው፣ በሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ምርመራ ስለሚካሄድባቸው ሰራተኞች አስፈላጊውን መረጃ ማቅረብ እንጂ አስሮ የማስቀመጥም ሆነ መመርመር ስልጣን የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም። ይህም ሂደት በቅርቡ በአንድ ሚዲያ ተላለፈ ዶክመንተሪ ላይ ተበደልን ባሉት የቀድሞ ሰራተኞች በግልፅ ተገልጿል።
በመሆኑም አየር መንገዱ እሥር ቤት አለው የሚለው የድርጅቱን ሕዝባዊ አመኔታ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የሚደረግ በደንብ የተቀናጀ ድራማ ነው። አየር መንገዱ ምንም ዓይነት እሥር ቤት የለውም፤ ሊኖረውም ፈፅሞ አይችልም።
2. የሠራተኛ ዲስፕሊን እና ቅሬታ አስተዳደር
አየር መንገዱ የዳበረ የሠራተኛ የዲሲፕሊን እና ቅሬታ አስተዳደር ሥርዓት ያለው ሲሆን ይህም አስተዳደራዊ ሥርዓት እንደ ድርጅቱ ሁሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው።
ከዲሲፕሊን ሥርዓቱ ብንጀምር፣ አንድ ሠራተኛ ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጥፋት አጠፋ ተብሎ ቢጠረጠር በኮርፖሬት ሰው ሀብት አስተዳደር ገለልተኛ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተቋቋሞ ጉዳዩ በዝርዝር ይታያል። የኮሚቴው አባላት ከማኔጅመንቱና ከሠራተኛ ማህበሩ ይወከላሉ። በሂደቱ ሠራተኛው በበቂ ሁኔታ እንዲደመጥ ይደረጋል። ኮሚቴውም ግራ ቀኙን በአግባቡ ከመረመረ እና ማስረጃዎችን ከመዘነ በኋላ የውሳኔ ሃሳቡን አቅርቦ እንደ ጥፋቱ መጠን እና ክብደት በህብረት ስምምነቱ እና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ መሠረት ይወሰናል። በዚህም አስተዳደራዊ ፍትህ በተገቢው ሁኔታ ይረጋገጣል። ይህ አሠራር በአየር መንገዱ የዳበረ መልካም አሠራር እና በርካታ ድርጅቶች ልምድ ለመካፈል በየጊዜው የሚመጡበት ነው።
በውሳኔው ላይ ቅሬታ ያለው ሠራተኛ በሠራተኛ ማህበሩ በኩል ወይም በግሉ ፍርድ ቤት ይከሳል፡፡ ይህ የተለመደና ለዘመናት ያለ ህጋዊ አሠራር ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ድርጅቱ በጥፋታቸው የተባረሩ ሠራተኞችን ይቅርታ የሚመለከትበት የይቅርታ ደንብ እና አሠራር (Pardon Policy and Procedure) አለው፡፡ ይህም የይቅርታ አሠራር የትም ድርጅት የሌለ እና ድርጅቱ ጥፋት አጥፍተው ለተሰናበቱ ሠራተኞች ዳግም ዕድል የሚሰጥበት አሠራር ሲሆን የሠራተኛ ማህበሩም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግበት ነው። በዚህም የይቅርታ ደንብ እና አሠራር ባለፉት 5 ዓመታት 413 ሠራተኞች ጉዳያቸውን በድጋሚ ለማየት ተችሏል። ሌላው ድርጅቱ የሠራተኛ ቅሬታ የሚያስተናግድበት ሥርዓት (Grievance Hearing Procedure) ነው። የቅሬታ አስተዳደር ዋና መለኪያው ሠራተኛው በማንኛውም የሥራ ጉዳይ ደረጃ በደረጃ ቅሬታ እያቀረበ በተገቢዉ መንገድ ምላሽ የሚያገኝበት ሥርዓት ሲሆን ነው። አየር መንገዱም በድርጅቱ ውስጥ የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ቅሬታ የሚባሉ ደረጃ በደረጃ የሚሄዱ የዳበረ የቅሬታ አፈታት አሠራር ያለው ድርጅት ነው።
3. ከስራ የሚለቁ ሰራተኞችን በተመለከተ
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ፍለጋ መንቀሳቀስ የተለመደና ውደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በዓለም አየር መንገድ ኢንዱስትሪ የሠራተኛ ፍልሰት 10 በመቶ እንደሆነ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) ጥናት ያመለክታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን አማካይ የሠራተኛ ፍልሰት ስንመለከት ከ 2 በመቶ አይበልጥም። ይህም የድርጅቱ ሠራተኞች ድርጅታቸውንና ስራቸውን የሚወዱና አክብረውም በመስራት የሀገር ግዴታቸውን የሚወጡ አለም ያደነቃቸው ሰራተኞች ለመሆኑ ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው። በመሆኑም ጉዳዩን ማገናዘብ ያለብን ከኢንዱስትሪው አማካይ የሠራተኛ ፍልሰት አንፃር ነው።
ስለዚህም ወሬው ምን ያህል በማስረጃ ላይ ያልተመሠረተ ተራ አሉባልታ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
4. ኮንትራት ቅጥርና የውጭ ሀገር አብራሪዎች ቅጥር (Expat Pilots Recruitment)
አየር መንገድ ውስጥ ድርጅታቸውን በቅንነት ለበርካታ አመታት አገልግለው ጡረታ የወጡ ሰራተኞች ተመልሰው በኮንትራት ሲሰሩ ማየት የተለመደና ለሰራተኛውም ለድርጅቱም ጠቃሚ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በጥያቄያቸው መሠረት ድርጅቱ ለወጣቱ ትውልድ ያካበቱትን የሥራ ዕውቀትና ልምድ እንዲያካፍሉ፣ የሰለጠነ የሰው ሀይል በጊዜያዊነት ለመሙላት እንዲሁም ከድርጅቱ ጋር ያላቸው የቆየ ቁርኝት እንዳይቋረጥ በኮንትራት የቅጥር ሁኔታ ተቀጥረው እንዲሰሩ ይደረጋል።
በኮንትራት በሚሰሩበት ጊዜ ግን የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ በግልፅ በኮንትራት በተቀመጠ መልኩና በሁለትዮሽ ስምምነት የጡረታ ገቢያቸው ሳይቋረጥ ተጨማሪ ገቢ የሚመደቡበትን የስራ መደብ የደመወዝ መነሻ ስኬል የሚከፈላቸው ይሆናል፡፡ ይህ ማንኛውም በጡረታ ከተገለለ በኋላ የሚቀጠር ሰራተኛ የሚስተናገድበት የተለመደ አሰራር ነው፡፡ ግን በዶክመንተሪው ላይ የወጣው የቀድሞ ሠራተኛ ህዝብን ለማሳሳት ተጨማሪ ጥቅም ሳይሆን በደል እንደደረሰባቸው ለማስመሰል ያነሱት ሀሳብ ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡
በሌላ በኩል አየር መንገዱ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደገለፀው ከዕድገቱ ጋር የሚመጣጠን በቂ የፓይለት ቁጥር ባለመኖሩ፣ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ፓይለቶችን በነፃ በማሰልጠን፤ በቂ ልምድና አስፈላጊው ችሎታ ያላቸውን የውጭ ሀገር ፓይለቶች በማወዳደር በኮንትራት ይቀጥራል፡፡ ድርጅቱ በቂ ኢትዮጵያውያን ፓይለቶች ሲያፈራ በሂደት ሊተካቸው ይችላል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በድሬደዋ፣ በመቐለ፣ በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ የበረራ ማሰልጠኛ ተቋሙን በማስፋፋት በዓመት 1000 አብራሪዎችን ለማሰልጠን ተግቶ እየሰራ ነው። በመሆኑም ህዝቡን በስሜት ነድቶ ማሳሳት በተለይ ጉዳዩን በጥልቀት ከሚያውቁ ግለሰቦች የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ከላይ በጠቀስነው ዶክመንታሪ ላይ የታዩትና በጡረታ የተገለሉትን ፓይለቶች እንደ ምሳሌ የወሰድን እንደሆነ የግለሰብን ደመወዝ መግለፅ ተገቢ ባይሆንም እያንዳንዳቸው በወር ሲከፈላቸው የነበረው ደመወዝ ቢያንስ የሃያ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ወርሃዊ ደመወዝ ያህል እንደሚሆን ግን ህዝብ ሊያውቅ የሚገባው ጥሬ ሀቅ ነው፡፡
ሆኖም አየር መንገዱ አሁንም እንደሚያደርገው ትጉህ ሠራተኞቹን ለማበረታታት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችንና የደመወዝ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ከሌሎች አየር መንገዶች ጋር ለማወዳደር ግን የሌሎችን ሀገራት የኑሮ ወጪ (cost of living) ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ሊታሰብ ይገባል፡፡
5. የሠራተኞች ህክምና አገልግሎት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች ድርጅቶች ከሚለይባቸውና በሰራተኞቹ ተመራጭ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ለሰራተኞቹ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎትና የ24 ሰዓት ህይወት መድን ሽፋን ነው። ዘመናዊ በሆነ የህክምና መሳሪያዎች የተደራጀ ላብራቶሪ እንዲሁም በቂ ሀኪሞችንና የጤና ባለሙያዎችን የያዘና ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት የሚሰራ ክሊኒክ ለሰራተኞቹ ያለው ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ህመም ሲሰማው በክሊኒኩ ህክምና የሚያገኝ ሲሆን በሽታው ከአቅም በላይ ሲሆን ወደ ሌሎች ከፍተኛና ልዩ የህክምና ተቋማት እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ በህክምና ቦርድ ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ እንዲታከም ለተወሰነለት ሰራተኛ ለራሱ እና ለአንድ አሳካሚ ከሚሰጥ የአየር ትኬት በተጨማሪ ለህክምና ወጪው የሚውል እስከ አሥር ሺህ የአሜሪካን ዶላር በመክፈል የሚያሳክም ነው፡፡
በአጠቃላይ ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ግለሰቦቹ እንደዚህ የመሳሰሉ ድፍን ያሉ ተራ ወሬዎችንና አሉባልታዎችን በያገኙት ሚዲያ በማውራት ህብረተሰቡን ለማሳሳትና ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሌተቀን የለፉለትን ድርጅት ስም ለማጥፋት መሞከራችው እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ሆን ተብሎ የተደራጀ በሚመስል መልኩ በተከፈተ ዘመቻ የሀገር ሀብት እና ኩራት በሆነው አየር መንገዳችን ላይ እየተካሄደ ያለውን የስም ማጥፍት ጥቃት እየተቃወምን ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን ተገቢውን አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንደምንወስድ ለማሳወቅ እንወዳለን።