Connect with us

ከሕግ ውጭ የመንግሥት ሀብት ያባከኑ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ከሕግ ውጭ የመንግሥት ሀብት ያባከኑ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ ቀረበ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ከሕግ ውጭ የመንግሥት ሀብት ያባከኑ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ለአንድ ላፕቶፕ 152 ሺህ፤ ለአንድ ሞባይል 94 ሺህ ብር ግዥ ተፈፅሟል
42 ተቋማት ለኃላፊዎች ላፕቶፕና ሞባይል ግዥ 10 ሚሊየን ብር በላይ አውጥተዋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የማይመለስ ሞባይልና ላፕቶፕ ለአንድ ጊዜ እንዲገዛላቸው ያስተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ ከሕግ ውጭ በተጋነነ ዋጋ ግዥ የፈፀሙ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ ቀረበ።

በገንዘብ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ ፍቃዱ አጎናፍር፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት የከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ለማሻሻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት በነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር መ30-899/56 ባወጣው መመሪያ በአንቀጽ 8 ቁጥር 4 ተመላሽ የማይደረግ ሞባይልና ላፕቶፕ ለአንድ ጊዜ ተገዝቶ እንዲሰጥ ወስኗል። ይሄንን መሠረት በማድረግ እንዲሁም ከግዥና ንብረት አስተዳደር የተላለፈውን የግዥ መመሪያ በጣሰ መልኩ አንዳንድ ተቋማት በተጋነነ ዋጋ ግዥ ፈጽመዋል። በመሆኑም በሕግ ተጠያቂ መሆንና ልዩነቱንም ሊከፍሉ ይገባል የሚል አስተያየት ለገንዘብ ሚንስቴር ዴኤታ ሐሳብ ቀርቧል።

አቶ ፍቃዱ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ በመስከረም ወር የሚገዛውን የላፕቶፕና ሞባይል የዕቃ አይነት ዝርዝርና የአፈፃፀም መመሪያ ለተቋማት መላኩን ጠቅሰው ይሁን እንጂ አንዳንድ ተቋማት ከተላለፈው መመሪያ ውጭ እና በተጋነነ ዋጋ ዕቃዎቹ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በየተቋማቱ ያለው የግዥ አፈፃፀም በመመሪያው መሠረት መሆኑን ለማረጋገጥ የተቋማት የውስጥ ኦዲተሮች ባደረጉት ልዩ ኦዲት በአፈፃፀም መመሪያው ከተዘረዘረው ውጭ እንደ አይፎን ስልክና አፕል ላፕቶፖች ሕገ ወጥ ግዥ መፈፀሙንና በመመሪያው ዝርዝር መሠረት የገዙትም ቢሆን በተጋነነ ዋጋ የገዙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በግዥ መመሪያው መሰረት በግልጽ ጨረታ መገዛት ሲገባው በፕሮፎርማ ተገዝቷል፤ አንዳንድ ኃላፊዎች የመመሪያውን መውጣት ተከትሎ ስልክና ላፕቶፕ ቢገዙም በፊት የነበራቸውን ለመመለስ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፤ አንዳንድ ተቋማት ለማይመለከታቸው ኃላፊዎች ጭምር ገዝተው መገኘታቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

አቶ ፍቃዱ፤ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ለኃላፊዎች ግዥ ከፈፀሙ ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ለዋናና ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ ለአንድ ላፕቶፕ 152 ሺህ ብር እና ለአንድ ሞባይል 94 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ በድምሩ 492 ሺህ ብር ግዢ ፈጽሟል። ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ደግሞ ለዋናና ለሁለት ምክትል ዳይሬክተሮቹ ለአንድ ላፕቶፕ 125 ሺህ 499 እና ለአንድ ሞባይል 53 ሺህ 600 በድምሩ 537 ሺህ 297ብር በመግዛት ለእያንዳንዳቸው መስጠቱን ገልፀዋል።

የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬቱ የየተቋማቱን ልዩ ኦዲት ከመረመረ በኋላም ዘርፉን ለሚመራው የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ከግዥ መመሪያው ውጭ በመግዛት የህዝብና የመንግሥትን ገንዘብ ያባከኑ ከፍተኛ አመራሮች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲሁም ገበያውን በማጥናት የተጋነነ ግዥ የፈፀሙ ከፍተኛ አመራሮች ደግሞ ልዩነቱን ለተቋሙ እንዲመልሱ ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን ግዥ ላልተፈፀመላቸው ከፍተኛ አመራሮች የላፕቶፕና የሞባይል ዋጋን በማጥናት የሚገዛው ዕቃ የዋጋ ጣሪያ እንዲቀመጥ፤ በቀጣይም በየጊዜው አዳዲስ ኃላፊዎችም ሲመጡ የሚገዛ በመሆኑም በአገልግሎቱ በኩል በማዕቀፍ ግዥ እንዲከናውን በማድረግ የህዝብንና የመንግሥትን ገንዘብ ከብክነት ለማዳን የሚረዳ ሐሳብ ቀርቧል።
በየተቋማቱ የውስጥ ኦዲት ልዩ ኦዲት በማድረግ አፈፃፀሙን እንዲልኩላቸው ባለፈው የካቲት ወር ደብዳቤ መላካቸውን አስታውሰው ከተላከላቸው 137 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መካከል እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ያሳወቁት ተቋማት 58 ናቸው። ከእነዚህም መካከል የ16 ተቋማት ኃላፊዎች ግዥ ያልፈፀሙ ሲሆን 42ቱ ተቋማት ግን ለኃላፊዎቻቸው ግዥ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ግዥ የፈፀሙት 42ቱ ተቋማት ብቻ 10 ሚሊየን 96 ሺህ 896 ብር ወጪ አድርገዋል። በግዥው ከፍተኛው ለአንድ ላፕቶፕ 152 ሺህ፣ለአንድ ሞባይል 94 ሺህ ብር ሲሆን ዝቅተኛ ወጪ ደግሞ ለአንድ ላፕቶፕ 20 ሺህ 254 ብር፣ ለአንድ ሞባይል 12 ሺህ ብር መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ “ከዚህ በኋላ ቢያንስ አንሰርቃችሁም” ብለው ለህዝብ ቃል ቢገቡም በእሳቸው የሚመሩ አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ግን ከተፈቀደላቸው ውጭ የላፕቶፕና ሞባይል በተጋነነ ዋጋ በማስገዛት የህዝብና የመንግሥትን ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ለግል ጥቅም እያዋሉ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

(ምንጭ:-አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top