Connect with us

አባይን የምንገድበው በጉልበታችንና በገንዘባችን ሳይኾን በልባችንና በአንድነታችን ነው

አባይን የምንገድበው በጉልበታችንና በገንዘባችን ሳይኾን በልባችንና በአንድነታችን ነው

ባህልና ታሪክ

አባይን የምንገድበው በጉልበታችንና በገንዘባችን ሳይኾን በልባችንና በአንድነታችን ነው

አባይን የምንገድበው በጉልበታችንና በገንዘባችን ሳይኾን በልባችንና በአንድነታችን ነው፤ ያ ካልኾነ እንኳን አባይ እኛም ገዳቢ ያስፈልገናል፤ ስህተታችን ያፈሰናልና፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

በአባይ ጉዳይ እከሌ ከዳኝ እከሌ ወደደኝ ማለት ሞኝነት ነው፡፡ እንደኢትዮጵያ ሁሉን ሰጥቶ ባዶ እጇን ያስቀራትን ሀገር ማንም ወዳጅ ብሎ ላይጠጋ ይችላል፡፡ የሌላውን ፍቅር የሚስበው የራሳችን ህብረትና ፍቅር ነው፡፡ ከጸናች ሀገር ጋር መወዳጀት ለየቱም ሀገር ምርጫ ሳይኾን ብልጫ ይኾናል፡፡

የእኛ ጉዳይ ብዙው ገራሚ ነው፡፡ ትልቅ ሀሳብ ይዘን በትንንሽ ጉዳዮች የምንታመስ ነን፡፡ ብሔር ለሚያባላት፣ ዘር ለሚያጫርሳት ሀገር የሚወግን የአበደ መንግስት የለም፡፡ የሚያፈርሱ ሀሳቦቻችን በዲፕሎማሲው ዓለም እንዳንፈለግም እንዳንደገፍም ያደርጉናል፡፡

አባይን ለመገደብ ስንጀምር ብዙ መነሻም መድረሻችንም እኛው ነን፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሌላ ወገን የሚመጣን ድጋፍም ተቃውሞም ትልቅ ቦታ አልሰጡትም ነበር፡፡ እኛው ማድረግ እንችላለን የሚለው መንፈስ አባይን ደፈረው፡፡

እኛ ገንዘብ የለንም፤ እውቀት የለንም፡፡ ከእኛ ባለመወዳጀቱ የሚራብ ሀገር የለም፡፡ በተቃራኒው ከእኛ ቢኳረፉ ከመለመን የሚድን ሀገር ይኖር ይኾናል፡፡ ዛሬ ጉልበት ገንዘብና እውቀት ነው፡፡ ጦርና ጎራዴ ከጦርነት ርቀዋል፤ ጦርነት ዛሬ መልኩን ቀይሯል፡፡ የጦር መሳሪው ዲፕሎማሲና ሀብት ነው፡፡

እንዲህ ላለው ዘመን የሚመጥን ተክለ ቁመና ላይ አይደለንም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ግድቡ ሲከሽፍ ማየትን የሚሻ የእናት ጡት ነካሽ አለ፡፡ ትናንት ግድቡን ተቃውሞ ግብጽ ጉያ የነበረው ተቃዋሚ ዛሬ ግብጽ አትገድቡም ለሚለው ሩቅ መንገድ እንድትሄድ ስንቅ ያዘጋጀላት መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡

ዛሬም እንዲህ ያለ ስንቅ አቀባይ መንፈስ አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሱዳን ፊቷን አዞረች እከሊት ልቧን ነሳች ብሎ ሀገር መቁጠር ረብ የለውም፡፡ አባይን መገደብ የምንችለው በእውቀታችንም በጉልበታችንም በገንዘባችንም አይደለም፡፡ በልባችን ነው፡፡

እንደአባቶቻችን ልበ ሙሉ ሆነን፤ ደግሞም በፍቅራችን ነው፡፡ ዘር ብሔር ሃይማኖት እያነሳን ዓለም ፊት ዛሬ ስፍራ በሌለው የልዩነት አጀንዳ ከመነታረክ ስንርቅ ነው፡፡

አንድ ስንሆን ብር ያለው ይመጣል፡፡ አንድ ስንሆን እውቀት ያለው ይጠጋናል፡፡ አንድ ስንሆን ጉልበት ያለው ከእኛ ጋር መሆንን ይመርጣል፡፡ ስንበዛ፣ ስንበተን፣ መደማመጥ ሲያቅተን ግን እንኳን ታላቁን ጊዮንን ልንገድብ እኛን ገዳቢ ያስፈልገናል፤ እንዲህ ያለ ህዝብ ባገኘበት የሚፈስ የአሸዋ ላይ ጎርፍ ነውና የትም ይቀራል፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top