“ምርጫ ለማካሄድ የያዝነው አቋም ፖለቲካዊና ሕገመንግስታዊ ነው” ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ህወሓት ምርጫን በሚመለከት የወሰደው አቋም ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ህገመንግሰታዊ መሆኑን የትግራይ ክልል ም/ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካእል አስታወቁ፡፡
ዶክተሩ ትላንት በፅህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፌዴራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በማስታወቁ በክልል ደረጃ የኮሮናን ወረርሽን እየተከላከልን በጥንቃቄ ምርጫውን ማካሄድ አለብን የሚል አቋም መያዛችን ሕገመንግስታዊና ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ ምርጫን የማራዘምና ያለማራዘም ብቻ አይደለም ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ይህ የህዝብን ውሳኔ አለመተግበር፣ ሕገመንግስቱ ያለማክበር፣ እንደዚሁም የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብትን መጣስ የሚያስከትል በመሆኑ ነው ምርጫ መካሄድ አለበት የምንለው ብለዋል፡፡
በሕገመንግስቱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ መካሄድ እንዳለበትና ከህዝብ ምርጫ ውጭ ወደ ሃላፊነት መምጣት እንደማይቻል በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ ከመስከረም በኋላ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች አሁን ያሉት መንግስታት የስልጣን ጊዚያቸው ስለሚያበቃና ህጋዊነት ስለማይኖራቸው ምርጫውን ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የሕገመንግቱን አንቀፆች ማስተርጎም የሚባለው የሚተረጎም ነገር የለውም። አምስት ዓመት ማለት አምስት ዓመት ነው፤ ሌላ ትርጉም መስጠት አይቻልም ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን ምርጫ ማካሄድ የበይ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ ሕገመንግስቱን በጣሰ መንገድ ስልጣንን ለማራዘም የተለያየ ሰበብ ከማብዛት ከህዝብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ችግሩን መፍታት ይሻል ነበር ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን ምርጫ አይካሄድም እየተባለ ያለው በኮሮና ምክንያት እንዳልሆነና ቀደም ሲል ፍላጎትና ዝግጅት ቢኖር ኖሮ በግንቦት ወርም ማድረግ ይቻል እንደነበር ጠቁመው የትግራይ መንግስት በክልል ደረጃ ምርጫ እናካሂዳለን ስንል ለኮሮና ቫይረስ ትኩረት ባለመስጠታችን ሳይሆን ለህዝብ ውሳኔና ለሕገመንግስቱ ተገዥ በመሆናችን መሆኑ ልታወቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ቀድመን ህዝባችንን ከቫይረሱ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥረት መደረጉንና አሁንም እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በትግራይ ክልል ምርጫው በሕግ ማዕቀፍ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከማህበራትና ከህዝብ ጋር በመመካከር የምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ህጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን አያይዘውም ምርጫውን እናካሂዳለን ማለታችንን ተከትሎ የተሰማው “እንቀጠቅጣችሁ አለን” የሚለው ተገቢነት የሌለው እንደሆነ በመጠቆም ስልጣን ላይ መቆየት የለብንም ስልጣችንን በህዝብ ለሚመረጥ አካል እናስረክብለን ህዝብ ቀጥሉ የሚል ይሁንታ ከሰጠንና ከመረጠን ደግሞ ሕዝባችንን ሕጋዊ የክልል መንግስት ሆነን እናገለግላለን በማለታችን መደገፍ እንጂ ትቀጠቀጣላችሁ መባሉ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን አያይዘውም ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በኋላ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት ቅቡልነትም ሆነ ህጋዊነት እንደማይኖራቸው በመጠቆም በአገር ደረጃም ምርጫ አለመካሄዱ አደገኛ ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ብጥብጥና ሁከት ሊያስከትልና ሰላም ሊደፈርስ ስለሚችል መንግስት ስልጣኑን ከሰጠው ህዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጀቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአግባቡ ሊመክርበትና መፍትሄ ሊያስቀምጥ ይገባል እንጂ በኮሮና ሰበብ ስልጣኑን ለማራዘም ወዳልሆነ መንገድ መሄድ አይገባም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፡፡(ትግራይ ኤክስኘረስ)