Connect with us

ሜቴክ ወንጀለኛ የተባለበት ተግባር ትክክለኛ አሠራር ሆኖ የተገኘበት አደባባይ

ሜቴክ ወንጀለኛ የተባለበት ተግባር ትክክለኛ አሠራር ሆኖ የተገኘበት አደባባይ
Photo: Ethiopian Reporter

ህግና ስርዓት

ሜቴክ ወንጀለኛ የተባለበት ተግባር ትክክለኛ አሠራር ሆኖ የተገኘበት አደባባይ

ሜቴክ ወንጀለኛ የተባለበት ተግባር ትክክለኛ አሠራር ሆኖ የተገኘበት አደባባይ | (አሳዬ ደርቤ )

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ የዓባይ ግድብ ዋና ሥራ-አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ ላይ ከቆመች መኪናቸው ውስጥ እራሳቸውን ዘንበል አድርገው ተገኙ፡፡ ያም ዘግናኝ ምሥል ለዘላለም ላይጠፋ በብዙዎች ጭንቅላት ውስጥ ታትሞ ቀርቷል፡፡ ቀይ ሸሚዝ፣ ሰማያዊ ኮፊያ፣ ዘንበል ያለ አንገት፣ ደም የተሰመረበትና ፂም የወረረው ፊት…

በጊዜው የኢንጂነሩን ሞት ማመን ከባድ ቢሆንም ሥርዓተ-ቀብራቸው ከተፈጸመ በኋላ መራሩን ሐቅ ተጎንጭተን ገዳያቸውን ለማወቅ ስንጠባበቅ ከረመን፡፡ ከተወሰነ ጥበቃ በኋላም ገዳይም፣ ሟችም እራሳቸው መሆኑን ተነገረን፡፡ ኢንጂነሩ በእራሳቸው ሽጉጥ እራሳቸውን ማጥፋታቸውን ሰማን፡፡

ከመግለጫው በኋላም ኢንጂነሩን ከሞት የማያስነሱና በፖሊስ የማይመለሱ እልፍ አእላፍ ጥያቄዎችን እያነሳን ከእራሳችን ጋር ስናወጋ የነበረ ሲሆን… ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንዶች ‹‹ኢንጂነሩ እራሱን አላጠፋም›› በማለት ሲደመድሙ፣ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ሥራ አስኪያጁ ካልጠፋ ቦታ መስቀል አደባባይ ላይ እራሱን ያጠፋው ምን ሊነግረን አስቦ ነው?›› እያሉ እንደ ሮበርትላንግዶን ሲመራመሩ ነበር፡፡

የሆነው ሆኖ የኢንጂነሩን ሞት ማንሳት ያስፈለገኝ በአሁኑ ሰዐት መስቀል አደባባይ ላይ እያየናቸው ስላሉ ተጨማሪ ጥፋቶች ለመጻፍ ሳስብ ቀድሞ የመጣልኝ ያ አሳዛኝ ክስተት በመሆኑ እንጂ የዚህ ጽሑፌ ዋነኛ ትኩረት በመሆኑ አይደለም፡፡ (በመስቀል አደባባይ በኩል ሳልፍ ኢንጂነሩ የሞተባትን ቦታ ሳላይ እንደማላልፈው ሁሉ ስጽፍም ይሄው አጀንዳ ቀድሞ ከተፍ በማለቱ ነው፡፡)

ይሄን ብዬ ወደ ዋናው ርዕሴ ስገባ ኢትዮጵያዊው መሐንድስ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ከተገኘበት አደባባይ ላይ በቅርቡ የተጀመረው ፕሮጀክት በሰፊው እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ይሄውም ፕሮጀክት መስቀል አደባባይን ከሥር የመኪና ማቆሚያ ቦታ ያለው ዘመናዊ አደባባይ የማድረግ ሥራ ሲሆን ለዚህም ተግባር 2.4 ቢሊዮን ብር መመደቡን ሰምተናል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሥራው ባለ ድርሻ አካላት ሳይመክሩበት በጥድፊያ የተጀመረ በመሆኑ የኢትዮጵያ አርቲቴክቶች እና የከተማ አጥኚዎች ማሕበር ዲዛይኑ ላይ ባለመሳተፉ ቅሬታውን ሲያቀርብ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ደግሞ ከመሥቀል በዓል ጋር ተያይዞ ዩኔስኮ ላይ የተመዘገበው አደባባይ ላይ ስለሚሠራው አዲስ ፕሮጀክት ምንም እውቅና እንደሌላት በደብዳቤ ገልፃ የግልጸኝነት ጥያቄ ማንሳቷ ይታወቃል፡፡

ከዚያ በኋላ የወጡት መረጃዎች ግን ኢንጂነሩ በተሰዋበት አደባባይ ላይ ሌላ ዓይነት ጥፋት እየተፈጸመ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል Addis Fortune ‹‹የመሥቀል አደባባዩ ፕሮጀክት ያለ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ጨረታ ለቻይናው CCCC ኩባንያ መሠጠቱን›› ጽፎ አስነብቦናል፡፡ ይሄውም ሁኔታ ባንድ ወቅት የሜቴክ ባለሥልጣናት ፕሮጀክቶችን ያለ ጨረታ በመሥጠት ጥፋተኛ ተብለው የተከሰሱበት ተግባር ባሁኑ ሰዓት ትክክለኛ አሠራር ሆኖ እየተተገበረ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን የከተማ መሥተዳድሩም በአባይ ሚዲያ በኩል የነገረን ‹‹አቅም ያለው ተቋራጭ ሲገኝና ሥራው አጣዳፊ ሲሆን ያለ ጨረታ የሚሠጥበት አሠራር መኖሩን›› የሚያስገነዘብ ነው፡፡

እርግጥ ነው የዘርፉ ባለሙያ ባንሆንም አንዳንድ ግዥዎች/ ሥራዎች ከብዙ ቅድመ-ሁኔታዎች ጋር ያለ ጨረታ የሚሠጡበት አሠራር መኖሩን በጥቂቱም ቢሆን እናውቃለን፡፡

በሌላ መልኩ ግን ማንኛውም ማሰብ የሚችል ሰው በዚህ ሰዓት የመኪና ማቆሚያ ቦታ ግንባታና የአደባባይ ማስዋብ ሥራ ለአዲስ አበባ አጣዳፊ ተግባር አለመሆኑን ያውቃል፡፡ ከበሽታ ክስተት ጋር ተያይዞ የሀገራችን ኢኮኖሚ በዳሸቀበት፣ በርካታ ዜጋ የሚላስ የሚቀመስ አጣለሁ ብሎ በሚጨነቅበት፣ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ተማሪዎች የሚቀጥራቸው ቢሮ አጥተው የሥራ ቦታቸውን ጫት ቤት ባደረጉበት፣ የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አፋቸውን ከፍተው በተቀመጡበት፣ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ የውጭ ተጽዕኖ በበረታበት… በዚህ አስከፊ ጊዜ በ2.4 ቢሊዮን ብር አንድ አደባባይ ማዘመን አጣዳፊ ሥራ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡

ሲቀጥል ደግሞ ይሄ አጣዳፊ ያልሆነ ተግባር መሠራት አለበት ቢባል እንኳን ከቀጥታ ይልቅ ጨረታ ለመንግሥት አዋጭ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ሐቁ ይሄ ቢሆንም ታዲያ የተግባሩ ባለቤቶች አደባባዩ ለሕዝቡ ያለውን ጥቅም በመረዳትም ይሁን እራሳቸው የሚያገኙትን ያልተገባ ጥቅም በማስላት ‹‹ፕሮጀክቱ አጣዳፊ ነው›› ብለው ጀምረውታል፡፡

በሌላ መልኩ ግን እንደ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ይቅርና መስቀል አደባባይ ላይ ‹‹ገዳ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ›› ከሚል ጽሑፍ ጋር የውሃ ቦቴ አዝላ የታየችው መኪና ብዙ መዘዝ እያመጣች ነው፡፡ በዚህም ጉዳይ የተደናገጡ አመራሮች የግለሰብን (የሹፌርን) መታወቂያ በገጻቸው ላይ በመለጠፍ ተገቢነት የሌለው ማስተባባያ ሲያቀርቡ… ‹‹የገዳ ኮንስትራክሽን›› ሕጋዊ ባለቤት የሆነው ሰውዬ ደግሞ ከበቂ ማስረጃ ጋር ‹‹እኔ ሳላውቅ በኩባንያዬ ሥም እየተነገደበት ነው›› በማለት ለክስ መዘጋጀቱን ሶሻል-ሚዲያ ላይ ተለጥፎ አንብበነዋል፡፡ ቦቴዋ ላይ የተለጠፈው የካምፓኒ ሥምም በቻይንኛ ፊደል ለመሸፋፈን ሲሞከር ታዝበናል፡፡

እነዚህም ነገሮች ባንድ ላይ ሲደማመሩ በጓሮ በኩል ሲካሄዱ የነበሩ የሙሥና ወንጀሎች አደባባዮች ላይ መፈጸም መጀመራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ስለሆነም አገሪቱን የሚመራው መንግሥትም ሆነ የጸረ-ሙሥና ኮሚሽኑ ይሄንን ጉዳይ በትኩረት በመያዝ ትልቁ አደባባይ ላይ በፕሮጀክት ሥም የተሠራውን አስነዋሪ ጥፋት አጣርቶ እርምጃ መውሰድና ለሕዝብ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top