Connect with us

በለውጡ የተገኘ ፍቅር

በለውጡ የተገኘ ፍቅር
Eritrea's President Isaias Afwerki is welcomed by Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed upon arriving for a three-day visit, at the Bole international airport in Addis Ababa, Ethiopia July 14, 2018. REUTERS/Tiksa Negeri

ጥበብና ባህል

በለውጡ የተገኘ ፍቅር

በለውጡ የተገኘ ፍቅር
አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ከሄለን ሽሮ ቤት ተቀምጬ የኮሮና መድሃኒት የተገኘ ይመስል በኮምቢሽታቶ ጎዳና ላይ የሚርመሰመሰውን ሕዝብና የሄለንን ገላ በየተራ እቃኛለሁ፡፡

ይህ ጎዳና ኮምቢሽታቶ የተባለው አብዛኞቹ ተከራዮች ኤርትራውያን ስለሆኑ ነው፡፡ ግራውንድ ላይ ያሉትን የንግድ ቤቶችም ሆነ የኮንዶሚንየም መኖሪያ ቤቶች በብዛት የተከራዮቸው እነሱ ናቸው፡፡ ይሄንንም ስመለከት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከቻይናው ባለሃብት የተላከለትን ማስክና ጓንት ሳይወስድ የቀረው ‹‹ይቅርብኝ›› ብሎ ሳይሆን ‹‹እዚያ ላሉት ዜጎቼ ስጡልኝ›› በማለት ይመስለኛል፡፡

ሄለንም ከእነዚህ ኤርትራውያን መሃከል አንዷ ስትሆን በቀን ሶስት ጊዜ እየተመላለስኩ አቦል፣ ቶና እና በረካ ሳንጫልጥ የምውለው ቡናዋ ስለሚያረካኝ ሳይሆን ፍቅር ቢጤ ስለያዘኝ ነው፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ የምበላውን ሥጋ ትቼ የእሷን ሽሮ መብላት የጀመርኩትም ውበቷ ስለማረከኝ እንጂ ወጧ ስለሚጣፍጠኝ አይደለም፡፡ ሄሉ ከላይና ከታች ስትታይ ፊቷም ሆነ ቁርጭምጭሚቷ እንደ ቡናዋ ነው፡፡ ቀጠን ያለ….

የቆዳ ቀለሟ ደግሞ በመቆላት ሂደት ላይ እንዳለ ቡና ጠየም ያለና ወዝ ያቸፈቸፈበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የጡቷን ውድረት፣ የዳሌዋን ስፋትና የመቀመጫዋን እብጠት ስንመለከት ግን የባድሜ መሬት ወደ ኤርትራ ሳይሆን ወደ እሷ ገላ የተካለለ ይመስለናል፡፡ የምግብ ፍላጎታችን ተዘግቶ የሌላ ነገር ፍላጎታችን ይቀሰቀሳል፡፡

ሄሉን ስተዋወቃት እንደ አብዛኛው ኤርትራውያን አማርኛ የማትችል በመሆኗ ከደንበኞቿ ጋር የምትግባባው በምልክት ቋንቋ ነበር፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባንድ ወቅት ‹‹የጠላት ቋንቋ ነው›› ብለው የረሱትን አማርኛ ‹‹የሥራ ቋንቋ›› ሊያደርጉት ሲፈልጉ መሰወሩ ነው፡፡

በመሆኑም ሄለን አዲስ አበባ መጥታ ሽሮ ቤት ስትከፍት በተወሰነ መልኩ አማርኛ መስማት ብትችልም በመናገሩ በኩል ግን ‹‹ቡና እና ሽሮ›› ከሚሉት ቃላቶች ውጭ ምንም አታውቅም ነበር፡፡ እናም በምልክት ቋንቋ እንደ ምንም ከተግባባኋት በኋላ አንዳንድ ቃላቶችን ስላስጠናኋት ብዙም ሳትቆይ ደንበኞቿን ‹‹ምን ልታዘዛችሁ?›› እኔን ደግሞ ‹‹እወድኻለሁ›› ማለት ቻለች፡፡

ከዚህ ባለፈም ‹‹ሥልክ ቁጥርሽን ስጪን›› ወይንም ደግሞ ‹‹እንትን ስጪን ›› ለሚሏት ወንዶች መስጠት ያለባትን መልስ በነገርኳት መሠረት ልቅም አድርጋ በመሸምደድ ‹‹እኔ ትዳርና ዓላማ ያለኝ ሴት እንጂ ሴተኛ አዳሪ አይደለሁም›› እያለች ስትመልስ ከርማለች፡፡

ብዙም ሳትቆይ ግን ከአንዳንድ ውርጋጥ ደንበኞቿ ቋንቋውንም ሆነ ብልግናውን ተምራ ስልኳን ለሚጠይቋት ደንበኞቿ ‹‹09›› እያለች ትናገር ያዘች፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ‹‹እወድኻለሁ›› ማለት ያለባት ፍቅረኛዋን እንጂ ደንበኛዋን አለመሆኑን ነግረዋታል መሰል ይሄን ቃል ትታ ‹‹በጣም ጥሩ ሰው ነህ›› ማለት ብትጀምርም… እኔ ግን በደንበኝነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነታችንን ወደ ባልና ሚስት ለማሳደግ ጥረት ማድረጌን ልተው አልቻልኩም፡፡

እውነት ለመናገር ለሄሉ የማደርገው እንክብካቤ ዶክተር አቢይ ለኢሳያስ ከሚያደርገው እንክብካቤ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከንፈሯን ለመሳም ያደረግኩትን ጥረት ለአገራዊ ጉዳይ አውየው ቢሆን ኖሮ የኤርትራን የባሕር በር ለመጠቀም የሚያስችል ነበር በማለት አስባለሁ፡፡

በሄለን እና በኢሳያስ መሃከል ያለውን መመሳሰል ሳስበው ሰውዬው ፕሬዝዳንቷ ሳይሆን አባቷ ይመስለኛል፡፡ አኩራፊነቷ፣ ወረተኝነቷ፣ ገንዘብ ወዳድነቷ፣ ግትርነቷ፣ ስልክ አለማንሳቷ፣ ሁሉ ከኢሳያስ ጋር ያመሳስላታል፡፡

ጠብ እርግፍ ማለቴ፣ ፈገግታና እንክብካቤ ማብዛቴ፣ ከቤቷ አለመጥፋቴ፣ በቀን አሥር ጊዜ ስልክ መምታቴ፣ ቻይነቴ፣ ደግሞ ከጠቅላያችን ጋር ያመሳስለኛል፡፡

ቀኑን ሙሉ ቤቷ ተቀምጦ ሲያቃጥር የሚውለው፣ እኔና ሄለንን አጣልቶ እሷን ለመጥበስ የሚመኘው፣ ኢትዮጵያዊነቱን ትቶ ኤርትራዊ ለመሆን የሚሞክረው ‹‹ተክሉ‹‹ ደግሞ ሁሉ ነገሩ ህውሓትን የሚያስታውስ ነው፡፡

እናም እኔ ወደ ሽሮ ቤቷ ስሄድ ከእሱ ቤት የሄድኩ ይመስል ፊቱን በሳኒታይዘር ይዘፈዝፈዋል፡፡ እርሷ የምትናገረውን ቋንቋ ስለተናገረ ብቻ እራሱን ባል አድርጎ እኔን ማግለል ያምረዋል፡፡

ደስ ያለው ቀን ደግሞ በፈገግታ ይቀበለኝና የሄለንን መጥፎ ባሕሪዎች ሲዘረዝርልኝ ከቆየ በኋላ ‹‹እንዲህ ያለችው ሴት ለሚስትነት ቀርቶ ለደንበኝነት አትበቃም›› በማለት እንዲጠላት ሊያደርገኝ ይሞክራል፡፡

እኔ ከአጠገቧ ራቅ በምልበት ሰዓት ደግሞ እራሱን የውጭ ዜጋ አድርጎ ‹‹የዚህ አገር ወንዶች ለትዳራቸው ቀርቶ ለፈጣሪያቸው የማይታመኑ እንዴት ያሉ ባለጌዎች መሰሉሽ! የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ ስልካቸውና እንክብካቤያቸው አያባራም! ጭንሽን ካገኙ በኋላ ግን በአካል ቀርቶ በስልክ አይገኙም›› እያለ በባለፈው ሕይወቱ ሴት ሆኖ የተፈጠረ ይመስል አዲስ አበባ ውስጥ ከእሱ ውጭ ጨዋ አለመኖሩን ይነግራታል፡፡

የሆነው ሆኖ ግን እኔና ይህ ሰው በልጠን ለመገኘት የምናደርገው ፉክክር ለሄለን ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላታል፡፡ ገቢዋንም ሆነ ጋቤናውን በእጥፍ አሳድጎላት ሰንብቷል፡፡

በዚህ መሃከል ታዲያ ሄሉ ወደ እሱ የማዘንበል አዝማሚያ አሳይታ የነበረ ቢሆንም የጋብቻ ጥያቄውን ከመቀበሏ በፊት አንዳንድ መረጃዎችን ስታሰባስብ ሁለት ሴት አግብቶ መፍታቱን ሰማች፡፡ ከዚያም አቋሟን ለውጣ ‹‹የአብረን እንኑር›› ጥያቄውን ውድቅ አደረገችበት፡፡

ተክሉ ግን ‹‹የጋብቻ ጥያቄየን ከመቀበልም አልፋ የምንጋባበትን ቀን ተነጋግረን ጨርሰናል›› ባይ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ይሄን ያህል ጊዜ ስንከባከባትና እንጋባለን ብላኝ ከፍተኛ ዝግጅት ሳደርግ ከከረምኩ በኋላ የጋብቻ ጥያቄየን ውድቅ ማድረግ ቀርቶ ማራዘም አትችልም›› ብሎ ገገመ፡፡

አልፎ ተርፎም ‹‹አስቀድመን በያዝነው ቀን መሠረት ሰርጉ ይካሄዳል›› በሚል አቋም የሰርግ መጥሪያ ወረቀት አባዝቶ በመምጣት ለአንዳንድ ደንበኞቿ ማደል ሲጀምር ‹‹ከዚያ በፊት ሄለን ጋር ብትግባቡ አይሻልም?›› በማለት ጠይቀውት ነበር፡፡

ተክሉ ግን ሰርጉን ያሰበው እንደ ህውሓት ምርጫ ነው፡፡ ማለትም አገራዊ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ካልተካሄዴ የራሴን ምርጫ አካሂዳለሁ›› እንደተባለው ሁሉ እሱም ‹‹ሰርጉ አይቀሬ መሆኑን አውቃ የራሷን ድግስ ማዘጋጀትና ሚስት ሆና መገኘት ከቻለች እሰየው! ካልሆነ ግን በሌለችበት አገባትና ባልነቴን እንዲትቀበል አደርጋታለሁ›› ባይ ነው፡፡ ይሄንንም ስሰማ እራሴን እንደ ምርጫ ቦርድ በማድረግ ‹‹ትዳር በሁለት ጥንዶች ፍላጎት የሚመሠረት ተቋም እንጂ በአንድ ሰው ምርጫ የሚካሄድ አይደለም›› በማለት ልነገርው ስሞክር ከጌታቸው ረዳ የሰማውን ንግግር ወደ እንደ ወረደ በመጠቀም‹‹የምርጫ ቦርድ ሥራው ወረቀት መበተን መሆኑን አልሰማህም እንዴ?›› ብሎኝ የሰርግ መጥሪያውን መበተኑን ቀጠለ፡፡

የሆነው ሆኖ በእኔና ሄሉ መሃከል ያለው ግንኙነት እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራ መሆን ችሏል፡፡ ለስሙ በሁለት ቤት ብንኖርም በመንፈስ ግን አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነናል ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በባለፈው ‹‹ቤቴን የምትጎበኝልኝ መቼ ነው?›› ስላት ‹‹ቅዳሜ እመጣለሁ›› ብላኝ ነበር፡፡

በእለቱም ከቤቷ ተቀምጦ መጥሪያ የሚበትነውን ሰውዬ ‹‹ኮሮናን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ ድርጅቴን ዘግቼ ወደ ደንበኛየ ቤት ልሄድ ስለሆነ ውጣልኝ›› ስትለው የሰጣት መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡፡
‹‹አይሻልሽም አንበጣን በጋራ ለመከላከል?››

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top