Connect with us

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ መግለጫ
22 Nov, 2016 in Ethiopian Airlines tagged Frankfurt / Free Baggage allowance / Frequent flyer / Germany by Editor

ህግና ስርዓት

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠ መግለጫ

በጥቂት ማህበራዊ ድረ-ገፆች በተደጋጋሚ ውሸትን እውነት አስመስለው በማቅረብ ላይ የተሰማሩ ጥቂት ሰዎች ማህበረሰቡን የሚያሳስቱ ከእውነት የራቁ ዘገባዎች ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የአፍሪካ ህዝቦች እንዲሁም የአለማችን ጥቁር ህዝቦች ኩራትና የስኬታማነት ልዩ ምልክት በመሆን ለአለማችን በተለይም ለአፍሪካ መተኪያ የሌለው አገልግሎት ላለፉት 74 ዓመታት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት ራዕይ 2025 የተባለውን የስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ በ2025 እጅግ በጣም የተለጠጡ በአለም አቀፍ ባለሞያዎች ግምገማ በፍፁም አይደረስባችውም የተባሉ ግቦችን አውጥቶ በማከናወን ላይ እያለ ከዕቅዱ በፊት 7 ዓመት አስቀድሞ በማሳካቱ አለም በሙሉ ያደነቀው ውጤታማ አየር መንገድ፣ በአፍሪካ ብቸኛ አትራፊ እና በፈጣን እድገት ላይ የሚገኝ አየር መንገድ በመባል ከፍተኛ አድናቆት እና በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።

በዚሁም መሰረት በ126 አውሮፕላኖች ወደ 127 አለምአቀፍ መዳረሻዎች በ5 አህጉራት እና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች በመብረር ከአፍሪካ 1ኛ ለመሆን ችሏል። ይህም አየር መንገዱ ከ10 ዓመት በፊት ከአፍሪካ አየር መንገዶች 4ተኛ ደረጃ ይዞ የነበረ ሲሆን በቅርብ አመታት ጠንክሮ በመስራት ወደ 1ኛ ደረጃ ከፍ በማለት የአንፀባራቂ ድል ባለቤት ሆኗል።

ከላይ የተጠቀሱት ስኬቶች አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት (Socio Economic Development) ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አድርጎታል። በቱሪዝም፣ በኤክስፖርት ድጋፍ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት፣ የሀገራችንን እና የአህጉራችንን መልካም ገፅታ በመገንባት እና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለአለም በማብሰር እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፍ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖረት ማህበር (IATA) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የአቪዬሽን ኢንዳስቱሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ለ1.2 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል። አየር መንገዱ ከሀገሪቱ አጠቃላይ GDP 5% ድርሻ አለው።

ይህንን አንፀባራቂ ድል እና ስኬታማነት የኢትዮያውያን ሁሉ ኩራት አና አለኝታነት ሲሆን፤ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅማቸው ስለተነካባቸው በድርጅቱ እና በአመራራቸው አለም ያደነቃቸው የድርጅቱ መሪዎች ላይ በስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራታችው አየር መንገዱን በጣም አሳዝኖታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህ ጥቂት ሰዎች እንደሚያወሩት ሳይሆን በአለም አቀፍ ኦዲተሮች፣ በሀገር ውስጥ ኦዲተሮች፣ በአበዳሪ ድጅርቶች ኦዲተሮች አንዲሁም በአለም አቀፍ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ድርጅቶች ኦዲተሮች እየተረጋገጠ የሚሄድ ግልፅነት የተሞላበት አለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ ከምንም አይነት ሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዳ ፖሊሲ፣ መመሪያ እና የስራ ሂደት ያለው አለም አቀፍ ድርጅት ነው።

አየር መንገዱ የUN Global Compact አባል ሊሆን የቻለው UN የሚፈልገውን የግልፀኝነት እና የመልካም አስተዳደር መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ በሟሟላቱ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሲበር እንደ ድርጅት ተመዝግቦ ስራዎችን ሲሰራ የእያንዳንዱ ሀገር የግልፀኝነት ደረጃዎችን (Transparency Standards) ያሟላል። ሀቁ ይሄ ሆኖ ሳለ የበሬ ወለደ እና የውሸት ጋጋታ እየደረደሩ የድርጅቱን እና የአመራሩን ስም ለማጥፋት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።

1. አቶ ሳሙኤል የተሻወርቅ የተባለ ግለሰብ አሸር የሚባል የጉዞ ወኪል የግል ድርጅት በጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ አቋቁሞ እንደማንኛውም የጉዞ ወኪል ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ትኬት በመሸጥ ሲሰራ ነበር። እ.ኤ.አ ከኦገስት 2015 እስከ ዲሴምበር 2015 ትኬት የሸጠበትን ገንዘብ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳይከፍል በመቅረቱ አየር መንገዱ ቀሪ ሂሳቡን እንዲከፍል ሲጠይቀው ቢሮዬ ውስጥ ትሰራ የነበረች ሰራተኛ ገንዘብ አጭበርብራኛለች ኢትዮጵያ ውስጥም ቤት ሰርታበታለች በማለት አየር መንገዱ ገንዘቡን በማስመለስ እንዲተባበረው ጠይቋል። ነገር ግን አየር መንገዱ ባደረገው ማጣራት ግለሰቡ የሰጠው ምክንያት በፍፁም ከአውነት የራቀ እና ውሸት መሆኑን አረጋግጧል። በመቀጠልም በታክስ ምክንያት የጀርመን መንግስት የባንክ ሂሳቤን ስለዘጋብኝ ነው እንጂ የታክስ ጉዳዩን አስተካክዬ ሂሳቤ ሲከፈትልኝ እከፍላችኋለሁ በማለት ሌላ የተጭበረበረ ምክንያት ሰጥቷል።

አየር መንገዱ ገንዘቡን ለመሰብሰብ ባካሄደው ጥረት ሁለቱም ምክንያቶች ሀሰት መሆናቸውን አጣርቶ በድጋሚ እንዲከፍል ሲጠይቀው በየወሩ እንድከፍል ፕላን አውጡልኝ በማለት በየወሩ መክፈል የጀመረ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ቀሪ ሂሳቡን ግን መክፈል ስላልቻለ የቀረበትን 510,421.09 (አምስት መቶ አስር ሺ አራት መቶ ሀያ አንድ/09) ዪሮ እንዲከፍል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጀርመን ፍርድ ክስ መስርቷል። ይህንን ተከትሎ ድርጅቴ ከስሯል በማለት ኪሳራውን (Bankruptcy) በፍርድ ቤት አሳውጇል። አየር መንገዱም ክሱን በመከታተል አሁን በቅርቡ ፍርድ ቤቱ ሙሉ የቀረበትን ሂሳብ እና የአየር መንገዱን የጠበቃ ወጪ እንዲከፍል ውሳኔ አሳልፏል። የፍርድ ቤቱ ትእዛዝም በእጃችን ላይ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንጎላ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲያጋጥማት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትኬት ሽያጭ የተሰበሰበውን የውጪ ምንዛሬ ለተወሰነ ጊዜ ለማስወጣት ስለተችገረ ከአንጎላ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሬ አስወጣላችኋለሁ በማለት ሌላ የማጭበርበር ሙከራ ሲያደርግ አየር መንገዱ ደርሶበት አስቁሞታል።

ግለሰቡ ከላይ የተዘረዘሩትን በርከት ያሉ የማጭበርበር ስራዎችን ከፈፀመ በኋላ የጉዞ ወኪል ድርጅቴ ያለአግባብ ተዘጋብኝ በማለት እንዲሁም ኮሚሽን ማግኘት ይገባኛል በሚል ቅሬታ አቅርቧል። ቅሬታውንም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ አመራር እና ለሌሎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ማቅረቡን ተረድተናል። ያቀረበው ቅሬታ እና ውንጀላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የውስጥ ኦዲት ተመርምሮ ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑ ተረጋግጦ ለቦርድ እና ለሌሎች ለሚመለከታችው አካላት ሪፖርት ተደርጓል። የኦዲተሮች ሪፖርትም በድርጅቱ ውስጥ ይገኛል።

በአሁኑ ሰዓት ግለሰቡ በጀርመን ፖሊሰ ስለሚፈለግ ከዛ ሸሽቶ ኢትዮጵያ ወስጥ ተደብቆ ይገኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኢትዮጵያ ውስጥ ክስ መስርቶ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሀቁ ይሄ ሆኖ ሳለ ግለሰቡ አሁንም ማለቂያ የሌለው የማጭበርበር ስራው ወደ ተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ጋር እየሄደ በድርጅቱና በአመራሩ ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ላይ ስለሚገኝ ለደንበኞቻችን እና ለማህበረሰቡ የዚህ ግለሰብ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

በጀርመንም ሆነ በኢትዮጵያ ህጎች የተፈረደበትን የ 510,421.09 (አምስት መቶ አስር ሺ አራት መቶ ሀያ አንድ/09) ዩሮ መክፈል ሲገባው ወይም ደግሞ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅሬታ ካለው ቅሬታውን በይግባኝ ማቅረብ ሲገባው ይህንን ህጋዊ አካሄድ ወደ ጎን በመተው የበቀል እርምጃ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራቱን ለደንበኞቻችን እና ለህብረተሰቡ በድጋሚ እናሳውቃለን።

2. በሰራተኛ አያያዝ ቅሬታዎች ድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ችግር እንዳለ በማስመሰል በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ቃለመጠይቅ በመስጠት ጥቂት የቀድሞ ሰራተኞች እና አዲስ የተቋቋመው የሰራተኛ ማህበር አመራር አባላት የሚያወጧቸው ውሸት እና የተሳሳቱ መረጃዎችን በዚህ አጋጣሚ ለማስተካከል እንወዳለን።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሁለት የሰራተኛ ማህበራት የሚገኙ ሲሆን አብላጫ ሰራተኛ አባል የሆነበት ወይም ከ6000 (ስድስት ሺ) በላይ አባል ያለው ከ59 አመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ሲሆን፤ ድርጅቱ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ በተቀመጠው ህግ እና ደንብ መሰረት ከዚህ ማህበር ጋር በመቀራረብ እና በመመካከር በህብረት ስምምነቱ ውስጥ የሚገኙ የሰራተኛ ጉዳዮችን ከቀዳማዊ ማህበሩ ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።

ሁለተኛው ማህበር ከ 7 ወር በፊት የተቋቋመ ሲሆን ህግ እና ስርዓት ተከትሎ ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ ስላልሆነ የድርጅቱ እና የድርጅቱ አመራርን በተለያዩ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ስም በማጥፋት ዘመቻ ላይ የተሰማሩ ጥቂት የስራ አመራር አባላት ያሉት ማህበር ነው።

ድርጅቱ ከዚህ ማህበር ጋር አብሮ ለመስራት በ3ተኛ ወገን ሸምጋይነት በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች፣ በአሰሪዎች ማህበር ኮንፊደሬሽን እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለማነጋገር ቢሞክርም አሻፈረኝ በማለት ድርጅቱን ቀውስ ውስጥ ለመክተት እና ሰራተኛውን አደጋ ላይ ለመጣል ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት እና የውሸት ጋጋታ እና የድርጅቱ ፖሊሲ እና ደንቦችን በመጣስ ድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱ ድርጅቱ በሃገሪቱ ውስጥ ባሉ ህጎች እና ደንቦች መሰረት አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ይህንንም ለደንበኞቻችን እና ለህብረተሰባችን ለማሳወቅ እንወዳለን።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኮርፖሬት አስተዳደር (corporate Governance) የሰራተኛ እና የማኔጅመንት አስተዳደር ፖሊሲ እና ፕሮሲጀር ያለው እና ሰራተኛውን አስተባብሮ የድርጅቱ ግቦች እና አላማዎችን በማሳካት አለም ያደነቀው ዝናና ስም ያተረፈ ድርጅት ነው። ለስኬታማነቱም ዋና ሚስጥሩ የሰራተኛው ታታሪነት፣ የማኔጅመንቱ እና የሰራተኛው አብሮ መስራት (team work) የኢንዱስትሪ ሰላም እና በአጠቃላይ በመልካም አስተዳደር ምሳሌ መሆኑ እየታወቀ ከዚህ ውጪ የሚደረገው ማለቂያ የሌለው ውሸት እና ውንጀላ ድርጅቱን ለማዳከም እና የሀገርን እና የህዝብን ሀብት ለመጉዳት ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጪ ሊሆን አይችልም።

አሁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው አለም ባጋጠመው የ COVID-19 የጤናና የኢኮኖሚ ቀውስ ክፍኛ የተጎዳ ቢሆንም ያለምንም የውጪ ድጋፍ እንደተለመደው በማኔጅመንት እና በሰራተኛው ትብብር ሌተቀን በመስራት ይህንን በአለማችን ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ለመሻገር በከፍተኛ ጥረት ውስጥ ይገኛል። በዚህ መሰረት ቀውሱን በተለመደው ስኬት እንደሚወጣ ሙሉ እምነት አለን።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top