Connect with us

መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት 78 ቢሊዮን ብር ሊያሳጡት ….

መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት 78 ቢሊዮን ብር ሊያሳጡት የሚችሉ የድጋፍ ዕርምጃዎችን ይፋ አደረገ
Photo: Reporter | የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

ኢኮኖሚ

መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት 78 ቢሊዮን ብር ሊያሳጡት ….

መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት 78 ቢሊዮን ብር ሊያሳጡት የሚችሉ የድጋፍ ዕርምጃዎችን ይፋ አደረገ

~ የ50 በመቶ የሠራተኛ ደመወዝ ግብር ዕፎይታ ተሰጥቷል

~ የሁለት ወራት የቤት ኪራይ ለማያስከፍሉ የአንድ ዓመት የኪራይ ግብር ተነስቶላቸዋል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፋቸው ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የሚደርሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ለመቀነስ ያስችላሉ የተባሉ አራት ዋና ዋና ዕርምጃዎችን ይፋ አደረገ፡፡ ታክስ ተኮር የሆኑት ዕርምጃዎች መንግሥትን የ78 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያሳጡት እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ይፋ ካደረጓቸው ዕርምጃዎች መካከል፣ ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም. በልዩ ልዩ ምክንያት ሳይከፈሉ የቆዩ ውዝፍ የታክስ ዕዳዎች በምሕረት እንዲቀሩ መወሰኑ አንደኛው ነው፡፡ በምሕረት የተተውት ዕዳዎች በፌዴራል ደረጃ ብቻ የሚገኙት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የግብር ዕዳቸውን በማሳወቅ ሒደት ላይ የሚገኙ፣ ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም. ሳይከፍሉ ነገር ግን በኦዲት ተረጋግጦባቸው እንዲከፍሉ የሚጠበቁ፣ በግብር ይግባኝ ሰሚና በፍርድ ቤት እየታዩ የሚገኙ የታክስ ዕዳዎች ላይ የተጣሉ የወለድና የመቀጫ ክፍያዎች እንዲቀሩ ተወስኗል፡፡

የ25 በመቶ ፍሬ ግብራቸውን የከፈሉ ቀሪውን በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚያመቻቸው ሁኔታ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በሚደረግ ስምምነት እንዲከፍሉ ሲወሰን፣ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት መቋጨት የሚፈልጉ ከሆነም ፈቃዳቸው እንደሚከበርላቸው ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ ፍሬ ግብራቸውን ወዲያውኑ መክፈል ለሚፈልጉም መንግሥት የአሥር በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርግላቸው ተጠቅሷል፡፡

ሌላው ከወጪ መጋራት አኳያ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ በተለይ የኪራይ ግብር ዕዳ መክፈል ለሚጠበቅባቸው በወረርሽኙ ምክንያት የንግድ ሥራቸው የተቀዛቀዘባቸውና የተቋረጠባቸው ተቋማትን ይመለከታል የተባለው ይህ የኪራይ ወጪ መጋራት ዕርምጃ፣ እስከ 50 በመቶ የኪራይ ገቢ ግብር ተቀናሽ ይደረግበታል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአራት ወራት ያህል መክፈል የሚጠበቅባቸውን የኪራይ ግብር ለሠራተኞቻቸው የደመወዝ ክፍያ እንዲያውሉት በማሰብ ሳይሰበስቡ እንዲጠቀሙበት ይደረጋል ተብሏል፡፡ በዚህ ዕርምጃ ተጠቃሚ የሚደረጉት የትምህርት ተቋማት፣ ሆቴሎችና ሌሎችም በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገመቱ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ናቸው፡፡

ግለሰብ ቤት አከራዮችም ታሳቢ የተደረጉበት የወጪ መጋራት ዕርምጃ ከ10,000 ብር በታች ወርኃዊ ኪራይ የሚያስከፍሉ ሆነው ለሁለት ወራት የኪራይ ገቢያቸውን ለተከራዮች መልቀቃቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ከሆነ፣ የአንድ ዓመት የኪራይ ገቢ ግብር ዕፎይታ ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ ይህ ከፍተኛ የኪራይ ግብር የሚሰበስቡትን እንደማይመለከት ሚኒስትር ዴኤታው አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

በሌላ በኩል በየወሩ የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታክስም ለሥራ ማስኬጃና ለልዩ ልዩ የገንዘብ ፍሰት ፍላጎታቸውን እንዲውል ታስቦ፣ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ሳይሰበሰብ በኩባንያዎች እጅ እንዲቆይላቸው መወሰኑን ኢዮብ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ እያራመደው ለሚገኘው ብሔራዊ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ በፈቃዳቸው አስተዋጽኦ ለሚያደርጉና እያደረጉ ለሚገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ካዋጡት ገንዘብ ላይ እስከ 20 በመቶ ተቀናሽ ተደርጎ በወጪ መልክ እንደሚያዝላቸው ተገልጿል፡፡

ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጡ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ለማገዝ የሚረዳ ብድር በአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢዎች በኩል በአፋጣኝ እንዲያገኙ ለማገዝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሚሰጠው ገንዘብ ብድር እንዲያገኙና ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡም ተወስኗል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም ከምርት ሥራ እንዳይስተጓጎሉ ለማገዝ 1.5 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ መመቻቸቱም ተወስቷል፡፡

በሌላ በኩል ለውጭ ገበያ የሚያመርቱ ኩባንያዎች ባጋጠመው ችግር ምክንያት ለሁለት ወራት ብቻ የሚቆይ፣ እንደ ሁኔታው የሚመለከታቸው ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ከፍተኛ ጫና ያጋጠማቸው የግል ድርጅቶች ከሠራተኞቻቸውና ከራሳቸው የሚያዋጡት የጡረታ መዋጮ ክፍያ ለሦስት ወራት ሳይከፈል እንዲጠቀሙበት፣ በዚህ ወቅት ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ሪፖርት የሚያደርጉ ካሉም ታሳቢ እንደሚደረግላቸው ተብራርቷል፡፡

በጉምሩክ በኩል የተከማቸ ዕዳ ያለባቸው ተቋማትም ታሳቢ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሲገዙ ቅድመ ክፍያ ክፈለው ቀሪውን ለመክፈል ረዥም ጊዜ የወሰደባቸው፣ ከግብር ነፃ መብት ተሰጧቸው ያስገቧቸውን እንደ መኪና ያሉ መገልገያዎች ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው ምክንያት ከፍሬ ግብር ባሻገር ወለድና ቅጣት የተጠራቀመባቸው ድርጅቶች ተለይተው፣ ፍሬ ግብር ብቻ እንዲክፍሉ መወሰኑን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡

እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በመወሰዳቸው መንግሥት የዜጎችን ወጪና ኪሳራ ለመጋራት፣ እንዲሁም በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች እስከ 78 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገቢ ሊያጣ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

(ምንጭ:- ብርሃኑ ፈቃደ ~ ሪፖርተር)

Continue Reading
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top