Connect with us

የድድ በሽታ መንስኤ፣ የሚያስከትለው ጉዳትና ሕክምና

የድድ በሽታ መንስኤ፣ የሚያስከትለው ጉዳትና ሕክምና
Peter Dazeley/Getty Images

ጤና

የድድ በሽታ መንስኤ፣ የሚያስከትለው ጉዳትና ሕክምና

የድድ በሽታ በዓለም ላይ ካሉ በጣም የተለመዱ የአፍ በሽታዎች አንዱ ነው። ሆኖም የበሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ላይታይ ይችላል። ከድድ በሽታ ባሕርያት አንዱ የሕመም ምልክቶቹ ወዲያው አለመታየታቸው ነው። ኢንተርናሽናል ዴንታል ጆርናል የድድ በሽታን በማኅበረሰቡ ላይ ከባድ የጤና ችግሮች ከሚያስከትሉ የአፍ በሽታዎች መካከል መድቦታል። አክሎም የአፍ በሽታ “ሕመምና ሥቃይ በማድረስ፣ ምግብ መመገብ አስቸጋሪ እንዲሆን በማድረግና የኑሮን ጣዕም በማሳጣት ረገድ በግለሰቦችና በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብሏል። ብዙ ሰዎችን የሚያጠቃው ይህን የጤና ችግር በተመለከተ ከታች የተሰጠውን ማብራሪያ ማንበብ በድድ በሽታ የመያዝ አጋጣሚን ሊቀንሰው ይችላል።

ስለ ድድ በሽታ ማወቅ ያለብን ነገር

የድድ በሽታ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ደረጃ ጅንጀቫይትስ(Gingivitis) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም የድድ መቆጣት ነው። የድድ መድማት በዚህ ደረጃ ከሚታዩ ምልክቶች አንዱ ሊሆን ይችላል። ድድ የሚደማው ጥርስ ሲቦረሽ ወይም በጥርስ መሃል የገባን ነገር ለማውጣት ሲሞከር አሊያም ያለምንም ምክንያት ይሆናል። በተጨማሪም የድድ ምርመራ በሚካሄድበት ጊዜ ከደማ የጅንጀቫይትስ ምልክት ሊሆን ይችላል።

ይህ ደረጃ እየተባባሰ ሲሄድ ፔርዮዶንታይትስ(periodontal) ወደሚባለው የድድ በሽታ ይሸጋገራል። በሽታው እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ጥርሶችን ደግፈው የሚይዙት የአጥንትና የድድ ሕዋሳት መበላሸት ይጀምራሉ። ይህ ዓይነቱ የድድ በሽታ የባሰ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ምንም የሕመም ምልክት ላያሳይ ይችላል። አንዳንዶቹ የፔርዮዶንታይትስ ምልክቶች በድድና በጥርስ መካከል የሚፈጠር ክፍተት፣ የጥርስ መነቃነቅ፣ የጥርሶች መዘርዘር፣ መጥፎ የአፍ ጠረን፣ ድዱ በመሸሹ የተነሳ ጥርሶች የረዘሙ መስለው መታየታቸውና የድድ መድማት ናቸው።

የድድ በሽታ መንስኤና የሚያስከትለው ጉዳት

ለድድ በሽታ የሚያጋልጡ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ዋነኛው ልማም ነው፤ ልማም ብዙውን ጊዜ ጥርስ ላይ ባክቴሪያ በስሱ ሲጋገር የሚፈጠር ቢጫነት ያለው ነገር ነው። ልማሙ ካልጸዳ ባክቴሪያዎቹ ድዱ እንዲያብጥ ያደርጋሉ። ይህ ሂደት እየቀጠለ ሲሄድ ድዱ ከጥርሶች መለያየት ይጀምራል፤ ይህ ደግሞ በድዱና በጥርሱ መጋጠሚያ ላይ የሚጋገሩት ባክቴሪያዎች እየጨመሩ እንዲሄዱ ያደርጋል። ባክቴሪያዎቹ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሰውነታችን ባክቴሪያዎቹን ለመከላከል በሚወስደው እርምጃ ጥርሳችንን ደግፈው የሚይዙትን የአጥንትና የድድ ሕዋሳት ማጥቃት ይጀምራል። በድድና በጥርስ መጋጠሚያ ላይ ያለው ልማም ሲደድር ሻህላ(የደረቀ የጥርስ ልማም) ይፈጠራል። ሻህላው ራሱ በባክቴሪያዎች የተሸፈነ ነው፤ እንዲሁም ጠንካራና ከጥርሶች ጋር በጣም የተጣበቀ በመሆኑ እንደ ልማም ለማጽዳት ቀላል አይደለም። በዚህ ምክንያት ባክቴሪያዎች በድዱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ይቀጥላሉ።

ለድድ በሽታ የሚያጋልጡ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ከእነዚህ መካከል የአፍ ንጽሕናን አለመጠበቅ፣ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚቀንሱ መድኃኒቶች፣ የቫይረስ ኢንፌክሽን፣ ውጥረት፣ የስኳር በሽታ ቁጥጥር ሳይደረግበት ሲቀር፣ ከመጠን በላይ አልኮል መውሰድ፣ ትንባሆ መጠቀም እና በእርግዝና ምክንያት የሚመጣ የሆርሞን ለውጥ ይገኙበታል።

የድድ በሽታ ሌሎች ጉዳቶችም ሊያስከትልብን ይችላል። ለምሳሌ የድድ በሽታ የሚያስከትለው ሕመም ወይም የጥርስ መነቀል ምግብ እንደ ልብ እንዳናኝክና እንዳናጣጥም ሊያግደን ይችላል። አነጋገራችንና የፊታችን ገጽታ ሊለወጥ ይችላል። በተጨማሪም የአፍ ጤንነት በአጠቃላይ ከሰውነታችን ጤንነት ጋር በቅርብ የተቆራኘ እንደሆነ በምርምር ተረጋግጧል።

የድድ በሽታ ምርመራና ሕክምና

የድድ በሽታ እንዳለብን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

በዚህ ጽሑፍ ላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች አንዳንዶቹን አስተውለን ይሆናል። ከሆነ ወደ አንድ ጥሩ የጥርስ ሐኪም ዘንድ ሄደን መታየት የተሻለ ይሆናል።

የድድ በሽታ ሊታከም ይችላል?

የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ያለ ከሆነ ሙሉ በሙሉ እንዲድን ማድረግ ይቻላል። በሽታው ፔርዮዶንታይትስ ወደተባለው ደረጃ ላይ ከደረሰ ግን ሊደረግ የሚችለው ነገር በሽታው በጥርሶቹ ዙሪያ ያሉትን ነገሮች ለምሳሌ አጥንቱንና ሌሎች ሕዋሳትን ከማበላሸቱ በፊት እድገቱን መግታት ነው። የጥርስ ሐኪሞች በድድና በጥርስ መጋጠሚያ ላይ የሚገኘውን ልማም እና ሻህላ የሚያስወግዱባቸው ልዩ መሣሪያዎች አሏቸው።

በዚህ ስውር ሆኖም ጎጂ በሽታ የመያዝ አጋጣሚን ለመቀነስ ቁልፉ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለውን ብሂል መከተል ነው፤ ጥሩ የጥርስ ሐኪም የማግኘት አጋጣሚ ጠባብ ወይም ጨርሶ ማግኘት የማንችል ቢሆንም እንኳ ይህን ማድረግ አያቅትም። የድድ በሽታን ማስወገድ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ደግሞ አዘውትሮ ለአፍ ጤንነት ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ነው።

የአፍ ንጽሕና አጠባበቅ

በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ መቦረሽ። አንዳንዶች በድድ በሽታ እንዳይያዙ ከዚህ የበለጠ ጊዜ ምናልባትም ምግብ በተመገቡ ቁጥር መቦረሽ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ ለስለስ ባለ ብሩሽ በቀስታ ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ላይና ወደ ታች በማንቀሳቀስ መቦረሽ፡፡ በየቀኑ በጥርሻችን መካከል ያለውን ቆሻሻ ቀስ አድርገን ማውጣት፤ ይህን ለማድረግ ለዚህ ዓላማ ተብሎ የተዘጋጀ ክር ወይም ቀጭን ብሩሽ አሊያም ስንጥር መጠቀም ይቻላል፡፡

ሼር በማድረግ አጋርነትዎን ያሳዩ!

ምንጭ:- ሰርቫይቫል 101

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top