Connect with us

ስለ አርበኛ አባቶቻችን ክብር አርበኝነትን እንዘክራለን

ስለ አርበኛ አባቶቻችን ክብር አርበኝነትን እንዘክራለን፤

ባህልና ታሪክ

ስለ አርበኛ አባቶቻችን ክብር አርበኝነትን እንዘክራለን

ስለ አርበኛ አባቶቻችን ክብር አርበኝነትን እንዘክራለን፤
ከኡጋዴን እስከ ማይጨው፤ የእናት ሀገር ጥሪን ምላሽ፡፡

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የአርበኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ ስለ አባት አርበኞች ተከታታይ ትረካውን ጀምሯል፡፡ የጎፋ ዘማቾችን ታሪክ ከጎፋ እስከ ማይጨው ሲል እንዲህ ይተርከዋል፡፡
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

አዲስ አበባ ለምን ጎፋ ሰፈር አለች? እነኛ ከአልባ ተራራ ግርጌ ያሉ ብርቱዎች አቤት ብለው የእናት ሀገር ጥሪን ለመቀበል ሲመጡ ያረፉበት ስለኾነ ነው፡፡ ዛሬም እያንዳንዱ ጎፋ ልብ ውስጥ ያ የአባቶቹ የአርበኝነት ጉዞ እንደ ዘጸአቱ መንገድ በክብር ይተረካል፡፡

የጎፋ ሠራዊት ከአድዋ እስከማይጨው እልፍ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ዛላዎች ከጋሞ ጋር ኾነው በማይጨው ያደረጉት ተጋድሎ በአባቶቹ በሚኮራ ትውልድ ዛሬም ድረስ በምድራቸው ስፍራ ያለው ታሪክ ነው፡፡

ጎፋ በኡጋዴን ያደረገው ተጋድሎ ደግሞ ገናና ነው፡፡ ከጎፋ ሰፈር በባቡር ድሬዳዋ ሄዶ ወደ ጅግጅጋ የገሰገሰው ሠራዊት በደጃዝማች አበበ ዳምጠው መመራቱን ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል ጽፈውልናል፡፡

የኡጋዴኑ ጦርነት የከፋ ነበር፡፡ ብዙ የጎፋ ሠራዊት ለእናት ሀገሩ በእናት ምድሩ ወድቆ የቀረበት መኾኑን በተመለከተ ታሪክ ጸሐፊው በላይነህ አሰጉ የመርዶው ሥርዓት ምን ይመስል እንደነበር ከጻፉት መረዳት ይቻላል፡፡ በኡጋዴን የሞተውን የጎፋ ሠራዊት ቤተሰቡ የተረዳው በየገበያዎች መኾኑን ከዘመኑ ሰዎች ከቀዱት ታሪክ ይነግሩናል፡፡

ተድላ ዘ ዮሐንስ ከኡጋኤን የተፈታው ሠራዊት በጎፋ ቡልቂ ያደረገው ተጋድሎ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በሚለው የአርበኞች የተጋድሎ ታሪክ ድርሳኑ ጽፎታል፡፡ ያ ብዙ መከራን አልፎ ቡልቂ ደረሰው ሠራዊት በጽናት ነበር የተዋደቀው፡፡

አስፋው እንግዳዬ ጣሊያን ሁሉን ድል አድርጎ ጎፋ ሊገባ ሲል “እንዴት ተደርጎ?” ያለ ብርቱ አርበኛ ነበር፡፡ ይኼ ጀግና ቀዬው ደብረ ፀሐይ ነው፡፡ ከዚያ ጦሩን ይዞ ጋላጻ ላይ መጣ፡፡ እስከአፍንጫው ከታጠቀ የጣሊያ ወታደር ጋር ተጋፈጠ፡፡ ህይወቱን እስከመስጠት ቅኝ ገዢን እንቢ አለ፡፡ ተሰዋ፡፡ ጎፋ ክብሩን አወደሰ፡፡
“አስፋው እንግዳዬ አስፋው እንግዳዬ
ቡልቂ ላይ ነው ሲባል ደብረ ፀሐይ ታዬ” ተባለ፡፡

ጎፋዎች ዛሬ በባህላዊ ልብሳቸው ቀይን ቀለም ምን ትርጉም ይሰጣል ሲባሉ ምላሻቸው ደም የሚያሞቅ ነው፡፡ “የጎፋ ህዝብ ለነጻነት ለሀገር የከፈለው ዋጋ ምልክት ነው” ይላሉ፡፡ የአባቶቹን የደም ዋጋ የክብሩ ምልክት ከሚያደርግ በላይ የታደለ ትውልድ የለም፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top