ክፉኛ በኮሮናቫይረስ በተመታችው የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ ትሰራ የነበረችው ዋነኛ ዶክተር እራሷን አጠፋች።
ዶክተር ሎርና በሬን ኒው ዮርክ ማንሐተን ውስጥ በሚገኘው ፕሪስቢቴሪያን አለን ሆስፒታል ውስጥ የድንገተኛ ክፍል ሜዲካል ዳይሬክትር የነበረች ሲሆን እሁድ እለት እራሷ ላይ ባደረሰችው ጉዳት ህይወቷ እንዳለፈ ፖሊስ አስታውቋል።
ከ49 ዓመቷ ዶክተር ሞት በኋላ አባቷ ዶክተር ፊሊፕ በሬን ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገሩት “ሥራዋን ለመስራት ስትጥር ቆይታለች ነገር ግን ሥራዋ ለዚህ አበቃት” ብለዋል።
አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከሞቱት 56 ሺህ ሰዎች ውስጥ 17500ው የሚገኙት በኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ ነው።
የዶክተሯ አባት እንዳሉት ልጃቸው ከዚህ በፊት ለዚህ ሊያበቃት የሚችል የአእምሮ ህመም አልነበረባትም። ዶክተሯ የሞተችው ከቤተሰቦቿ ጋር በምትኖርበት ሻርለትቪል ውስጥ ነው።
ዶክትር ሎርና የህክምና ሥራዋን በምታከናውንበት ጊዜ በኮሮናቫይረስ ተይዛ ታማ የነበረ ሲሆን፤ ለአንድ ሳምንት ከግማሽ እራሷን ለይታ ካቆየች በኋላ አገግማ ወደ ሥራዋ ተመልሳ እንደነበር አባቷ ተናግረዋል።
ነገር ግን ወደ ቤተሰቦቿ ከመመለሷ በፊት ትሰራበት የነበረው ሆስፒታል እረፍት እንድትወስድ አድርጓት ነበር።
አባቷ በመጨረሻ ባናገሯት ጊዜ በልጃቸው ላይ “የመነጠል” ሁኔታ እንደተመለከቱና የኮሮናቫይረስ ህሙማን ከመጡበት አምቡላንስ ሳይወርዱ እንዴት ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር እንደነገረቻቸው አስታውሰዋል።
“በእውነትም ልጄ በበሽታው የፍልሚያ ቦታ ላይ ከፊት ለፊት ተሰልፋ ነበር” ሲሉ አባት ስለልጃቸው አስተዋጽኦ ተናግረዋል። እንደ ጀግናም እንድትታሰብ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ዶክትር ሎርና ለቤተሰቦቿ ቅርብ የነበረች ሲሆን የበረዶ ሸርተቴና ዳንስ የምትወድ እንዲሁም በሳምንት አንድ ቀን አረጋዊያን እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ማዕከል በመሄድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትሰጥ ነበረ ተብሏል።
ትሰራበት የነበረው ሆስፒታልም ዶክተሯን “ጀግና” በማለት የገለጻት ሲሆን በሙያዋ የድንገተኛ ክፍሉን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በብቃት ስታገለግል እንደነበር በመግለጽ አድናቆቱን ገልጿል።(BBC)