“የዋስትና መብት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት በመሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ሊከበር ይገባል” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን
ሚያዝያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም የሚታሰበውን ‹‹በአፍሪካ ከክስ በፊት የሚደረግ እስራትን የመከላከል ቀን›› ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ከኮሮና ቫይረስ መረጃ ጋር በተያያዘ በተወሰዱ እርምጃዎች የታሰሩት የህግ ባለሙያ ኤልሳቤጥ ከበደ እና ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን ጉዳዮች ጨምሮ የዋስትና መብት አለመከበርና እና ከክስ በፊት ለረጅም ጊዜ የሚያዙ ሰዎች ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ዘንድሮ ለ5ተኛ ጊዜ ሚያዚያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. (25 April 2020) የሚታሰበው ‹‹ከክስ በፊት የሚደረግ እስራትን የመከላከል ቀን (Africa Pre-Trial Detention Day)››፤ የወንጀል ክስ ከመቅረቡ በፊት በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በማረሚያ ቤቶችና በሌሎች የማቆያ ስፍራዎች ለረጅም ጊዜ በእስር የሚማቅቁ ሰዎችን በሚመለከት የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ሰብዓዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ማስቻልን ያለመ ነው፡፡ በተለይም የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝባዊ መብቶች ኮሚሽን ያፀደቀው የሉዋንዳ የእስር አያያዝ ሁኔታ፣ የፖሊስ ማቆያ እና ከክስ በፊት የታሰሩ ሰዎች መመሪያ ሀሳብ (Luanda Guidelines on the Conditions of Arrest, Police Custody and Pre-Trial Detention in Africa) በግልጽ እንደሚያስቀምጠው በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሰረት ከክስ በፊት በእስር ላይ መቆየት በልዩ ሁኔታ ብቻ የሚፈቀድ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝባዊ መብቶች ቻርተር አባል ሀገራት በሙሉ ከክስ በፊት ሰዎችን በእስር ከማቆየት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን በመተግበር ተገቢ ያልሆነ እስርን በማስወገድ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን እንዲያሻሽሉ ያሳስባል፡፡
በዓለም ዓቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 9(1)፣ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር አንቀጽ 6 እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 መሰረት የተመለከተው የነጻነት መብት ከሚጠበቅባቸው መንገዶች አንዱ የዘፈቀደ እስርን ማስወገድና የዋስትና መብትን ማክበር ነው፡፡
ይሁንና በኢትዮጵያ ውስጥ ከክስ በፊት የሚደረግ እስራት እያደገ መምጣትና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገለት የዋስትና መብት በተሟላላ መንገድ አለመከበሩ አሳሳቢ ነው፡፡ ለማሳያነት ከላይ እንደተጠቀሰው በቅርቡ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተፈፀሙት እስሮች የዋስትና መብትን በሚመለከት ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው፡፡
• ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በእስር በቆየባቸው 27 ቀናት ውስጥ ሁለት ጊዜ የዋስትና መብቱ በፍርድ ቤት ተረጋግጦለት የነበረ ቢሆንም የህግ አስፈፃሚ አካላት የክሱን ሁኔታ በመቀያየር እና አስተዳደራዊ ምክንያቶችን በመፍጠር በእስር እንዲቆይ አድርገዋል፡፡ ጋዜጠኛው ከእስር ለመለቀቅ የቻለው በተጠረጠረበት ወንጀል ክስ ከቀረበበት በኋላ በፍርድ ቤት ለ3ተኛ ጊዜ በተረጋገጠለት የዋስትና መብት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ያየሰው ‹‹ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለሚሞቱ ሰዎች መንግሥት 200,000 የቀብር ቦታ እንዲዘጋጅ መመሪያ ሰጥቷል›› በሚል በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት የተነሳ በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀል ተጠርጥሮ ተከሷል፡፡ ሆኖም ከመነሻውም ቢሆን ጋዜጠኛው ከተጠረጠረበት ወንጀል አንጻር የዋስትና መብት የሚያስከለክል ምክንያታዊ እና አስፈላጊ ሁኔታ መኖሩ አልተረጋገጠም ነበር፡፡
• የህግ ባለሙያ የሆነችው ኤልሳቤጥ ከበደ በተመሳሳይ ሁኔታ በኮሮና ቫይረስ ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ ሰዎችን ስም በማሕበራዊ ሚዲያ ከመግለጽ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በፖሊስ ተይዛ ወደ ሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወስዳ በሀረር ከተማ በእስር ላይ የምትገኝ ሲሆን በዋስትና መብት ጥያቄዋ ላይ እስከ አሁን ድረስ ውሳኔ አልተሰጠበትም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኤልሳቤጥ ከበደ ከተጠረጠረችበት ወንጀል አንጻር የዋስትና መብት የሚያስከለክል ምክንያታዊ እና አስፈላጊ ሁኔታ መኖሩ አልተረጋገጠም፡፡
ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ እንዳሳሰበው የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የሚወስዷቸው የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች በሕገ መንግሥቱና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎችና መርሆች መሰረት መመራት እንዳለባቸው እና ከሕጋዊነት መርሕ አንፃር በነጻ ፍርድ ቤት የመዳኘት እና ይህንኑም የማረጋገጫ ሕጋዊ ሥነሥርዓቶች (Judicial and Procedural Remedies) አስፈላጊ በመሆናቸው ሊቋረጡ ወይም ሊገደቡ እንደማይገባ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከእነዚህ የሕጋዊነት ሥርዓት ማረጋገጫዎች አንዱ የዋስትና መብት የሚከበርበት ሥነ ሥርዐት ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 19(6) መሰረት በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች በፍርድ ቤት ዋስትና ካልተከለከለ በስተቀር ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ የዋስትና መብት የተጠረጠሩ ሰዎች እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብታቸውን ጨምሮ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት “የፍትሕ አካላት የመመሪያ መርህ የዋስትና መብትን ማረጋገጥ ሆኖ፤ ዋስትና ሊከለከል የሚችለው በሕግ በተመለከተው ልዩ ሁኔታ ብቻ ምክንያታዊና የግድ አስፈላጊ ሲሆን ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ‹‹በተለይም በዚህ ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና የበሽታውን ተጋላጭነት ለመቀነስ በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ በፌዴራልና የክልል መንግሥታት አበረታች እርምጃ እየተወሰደ ባለበት ጊዜ፤ ያለ ምክንያታዊነትና የግድ አስፈላጊ ሳይሆን ተጨማሪ ሰዎችን ወደ እስር ማስገባትና የተለያዩ መሰናክሎችን በመፍጠር የዋስትና መብትን ማደናቀፍ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም›› ብለዋል፡፡
በተለይ በዛሬው ዕለት የሚታሰበውን ከክስ በፊት የሚደረግ እስራትን የመከላከል ቀንን መሰረት በማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት በተለያዩ እስር ቤቶች ከክስ በፊት ተይዘው የሚገኙ ሰዎችን እስር ህጋዊነት፣ ምክንያታዊነትና አስፈላጊነት እየመረመሩ የዋስትና መብትን በማረጋገጥ፤ በሕገ መንግሥቱ፣ በዓለም ዓቀፍ እና በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የተረጋገጡ ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩና እና እንዲያስከብሩ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡