Connect with us

“ባጎረስኩ ተነከስኩ” ይሉኋል ይኸ ነው!

“ባጎረስኩ ተነከስኩ” ይሉኋል ይኸ ነው!
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

“ባጎረስኩ ተነከስኩ” ይሉኋል ይኸ ነው!

“ባጎረስኩ ተነከስኩ” ይሉኋል ይኸ ነው!
(መረር፣ ቆፍጠን ያለ ፅሑፍ ነው፤ ካልተመቸህ አትጀምረው።)
(ጫሊ በላይነህ )

“Stay at home” ቤት የመቆየት ድንጋጌ እየተገበርኩኝ ነው። ሰሞኑን ቴሌቭዥን ላይ ባፈጠጥኩበት ደቂቃዎች አንድ ዜና እንደዋዛ ሲነገር ሰማሁ። ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሚልኒየም አዳራሽ ለኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች 1ሺ የሕክምና መስጫ አልጋዎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተዘጋጀውን ጎበኙ ይላል። በቃ የዜናው ጭብጥ ይኸው ነው።
ዕድሜ ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ!!..ይኸ የሚልኒየም አዳራሽ ምን ያልሆነው አለ?

ከጥቂት ዓመታት በፊት አገራችን የአለምአቀፉን የኤችአይቪ እና የአባላዘር በሽታዎች ኮንፈረንስ ታዘጋጅ ነበር። የጉባኤው አዘጋጆች ሁለት ነገር ተቸገሩ። አንድ:- በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያስተናግድ አዳራሽ የአፍሪካ መዲና በምትባለው አዲስአበባ አልነበረም።

ሁለት:- በ10ሺ የሚቆጠሩ እንግዶች ማደሪያ አልነበራቸውም። ለምን ቢሉ የአዲስአበባ ይኸ ሁሉ ትላልቅ መሳይ ሆቴል አልጋቸው ተደምሮ 10ሺ መጠጋት አልቻለምና ነው።

ደጉ፣ ሩህሩሁ ሼህ ሙሐመድ የአዳራሹን ነገር ለእኔ ተውት አሉ። በቃላቸው መሠረት እጅግ አጭር በሚባል ጊዜ በሚልየን ዶላር የሚገመት ገንዘባቸውን አፍስሰው የሚልኒየምን አዳራሽ ደረጃውን ወደጠበቀ የኮንፈረንስ አዳራሽነት ቀየሩት። ስብሰባው ያለችግር ተካሄደ። በሼሁም ልግስና ትልቅ የመንግሥት ችግር ተቃለለ።

ዛሬም እነሆ የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት በወጠረን በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት “አለሁ” ያሉት እኚህ ደግ እና አንድ ለእናቱ ባለሀብት ሼህ አልአሙዲ ናቸው።

ጠቅላዬ ኮራ ብሎ የሚጎበኘው፣ መመሪያ የሚሰጠው በሼህ ሙሐመድ ልግስና ላይ ቆሞ ነው። የሚገርመው ግን አንድም ሰው፣ አንድም ሚድያ እኚህን ታላቅ ሰው አመሰግንኖ አለማየቴ ነው። በግሌ አዝናለሁ።

ሼህ አልአሙዲ ለወገን ደራሽ ባለሀብት መሆናቸውን ለማስታወስ በለውጡ ማግስት ያደረጉትን፣ የሰጡትን ልግስና አይቶ ማመን ብቻ ይበቃል።

ትላንት ለብልፅግና ፓርቲ ማጠናከሪያ ተጠይቀው የለገሱት የ 100 ሚልየን ብር ፊርማ ሳይደርቅ እንደገና ለኮሮና ወረርሽኝ 120 ሚልየን ብር በስማቸው ለግሰዋል።ሌሎች የእሳቸው ኩባንያዎች በተናጠል የሰጡት ገንዘብ ሲደመር ድጋፉን የትየለሌ ያደርገዋል።

እነታከለ ኡማ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ግዙፍ የዳቦ ፋብሪካ የመገንባት ህልም በአፋጣኝ ለማሳካት ቆርጠው የተነሱት እኚሁ ባለሀብት ናቸው። የምግብ ዘይት ፋብሪካው ግንባታውም እንዲሁ።

በተቃራኒው ኢንጅነር ታከለ ኡማ ምን አደረጉ? ሼሁ ከ400 ሚልየን ብር በላይ ያፈሰሱበትን የፒያሳ ግንባታ ቦታ “የታጠሩ ቦታዎች” በሚል መቀማታቸውን ያበሰሩት “ልማታዊ” አርቲስቶችን በማስጨብጨብ ነበር።

አሁን እኚህ ደግ፣ሩህሩህ አባት በኢትዮጵያ የለውጥ መንግሥት የተበደሉ ናቸው ቢባል ግን ማን ያምናል? ብዙ ነገሮችን ትቼ አንዱን ነጥብ ብቻ ላስታውስ?

የለገደንቢ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በመንግሥት ትዕዛዝ ከምርት ከታገደ ሁለት ዓመት ሊደፍን ነው። ኩባንያው የተዘጋው በአካባቢና በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል በተደራጀ ሁኔታ በተደረገ ተቃውሞ እና በአክራሪ የብሔርተኝነት ካባ ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ባለሀብቶች የሰው ሐብት ለመዝረፍ ክፉኛ ከመቋመጣቸው ጋር የተያያዘ ነበር። ሲጀምር ኩባንያው የተወነጀለበትን ጉዳይ እየሰራ ማጣራት ይቻል ነበር። ግዴለም፤ በእገዳ ውስጥም ሆኖ በገለልተኛ ወገን መጠናቱም መጥፎ ውሳኔ ልነበረም። ነገርግን የጥናቱን ውጤት በወቅቱ ከመግለፅና ውሳኔ ከመስጠት ማፈግፈግ ግን ጭካኔ ነው፤ ኢ ሰብአዊነት ነው።

በመንግሥት ግብዣ መሠረት ጥናቱን ያካሄደው የውጭ አገር ተቋም፤ በሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ኬሚካል ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ወገኖችን አግኝቶ ለማነጋገርና የጉዳቱን ሁኔታ ለማየትና በተጨባጭ ለማጣራት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች የነገሩኝ በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ሆነው ነው።

ለምን?
እነዚያ በአንድ ወቅት በአንቀሳቃሾቻቸው አበል ተከፍሏቸው “ተጎድተናል” ያሉ ግለሰቦች የት ገቡ? ለምንስ የአጥኚውን ምርመራ ሸሹ? የሚለው ራሱን የቻለ አነጋጋሪ ጥያቄ ሆኖ መንግሥት ከዚህ ሁሉ በሀላ ለኩባንያው ቁርጥ ያለ መልስ አለመስጠቱ፣ ዝምታን መምረጡ ያሳዝናል፣ ያስደነግጣልም። ውሳኔን በማዘግየት ኩባንያን ሆን ብሎ ማክሰር በሌሎች አለማት ቢሆን በሕግ የሚያስጠይቅ ራሱን የቻለ ወንጀልም ነው።

እጅግ የሚገርመው፤ በሼህ አልአሙዲ እና በእነዶ/ር አረጋ ይርዳው ውሳኔ ከኩባንያው መዘጋት ጋር ተያይዞ አንድም ሠራተኛ አለመባረሩ ነው። ይኸ ሁሉ በደል ተፈፅሞም “ሠራተኛ ማሰናበት በመንግሥት ላይ ያልተገባ ጫና ማሳረፍ ነው” በሚል አርቆ አሳቢነት ኪሳራ መሸከምን መምረጥ ምን አይነት የአገር መውደድ ልክፍት ነው?
በደልን፣ ከባድ ኪሳራን ከእነሕመሙ በታላቅ ትግዕስት እያስታመሙ መቆየትስ ቢሆን?

መቼም ጠቅላዬ በሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ጉዳይ ጥናቱን መሠረት አድርጎ እንዲወስን ማስታወስ ተገቢ የሚሆነው ኮቪድ 19 ለመከላከል ውጤታማ የሆኑ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ስለሚያስፈልገንም ጭምር ነው።

በተቃራኒው ውሳኔን ከማዘግየት ኩባንያውን እስከእነአካቴው ይዘጋ ማለትም ራሱን የቻለ ውሳኔ መሆኑን ማስታወስ ይገባል።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top