Connect with us

ለመኾኑ በሀገራችን በአዋጅ የጸደቀ ብሔራዊ እንስሳ አለን?

ለመኾኑ በሀገራችን በአዋጅ የጸደቀ ብሔራዊ እንስሳ አለን?
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ለመኾኑ በሀገራችን በአዋጅ የጸደቀ ብሔራዊ እንስሳ አለን?

ኢትዮጵያ-ብሔራዊ እንስሳ፣ ብሔራዊ ወፍ፣ ብሔራዊ አበባ የሌላት ቀደምት ሀገር፤፤
የቡና መገኛ ኾነን ብሔራዊ ፍሬ የሌለን ሀገር መኾናችንን ሳስብ እገረማለሁ፡፡

ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ለመኾኑ በሀገራችን በአዋጅ የጸደቀ ብሔራዊ እንስሳ አለን? ብሔራዊ ወፍስ? ብሔራዊ አበባስ አምጡ ብንባል የቱ ነው? እንዲኽ ያለው ውክልና በዓለም ሀገራት ዘንድ በብዙ የተለመደ ነው፡፡ ሀገራቱ ከራሳቸው ጋር የሰፋ ቁርኝት ያላቸውን፣ ከታሪካቸው የሚዛመድን፣ ከእሴታቸው የሚቆራኝን፣ ከትውፊታቸው የሚጋመድን፣ ከሥነ ልቦናቸው የሚተሳሰርን መገለጫ ከተፈጥሮ ይቀዳሉ፤ በተፈጥሮ ይወከላሉ፡፡

በኢትዮጵያስ የሚለውን ብዙው ሰው ሲያነሳ ሰምቼ አላውቅም፡፡ የቦታኒካል ጋርደኑ ዶክተር ብርሃኑ በላይ ግን ያልተሰራ ትልቅ ክፍተት መኾኑን ሲያነሳ ሰምቻለሁ፡፡ በራሱም ይኽንን በተመለከተ እያከናወነ ያለው ነገርና ሀሳብ እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡

በሀገራችን ባለፉት አመታት ይህ ዓይነት ባህል እንዲሁ በተለምዶ ይታይ ነበር እንደ ህግ በአዋጅ የጸደቀ ብሔራዊ ምልክት ግን እውን ኾኖ አያውቅም፡፡ በእርግጥ እንደ አንበሳ ያሉ እንስሳት በመንግስታዊና ተቋማዊ መለያ ምልክቶች ላይ አገልግሎት ሲሰጡ ኖረዋል፡፡

ለምሳሌ አየር መንገዳችን፣ ቴሌ፣ የአዲስ አበባ አውቶቢስ፣ የከነማ ፋርማሲው፣ የዳርማር ጫማ፣ የገንዘብ ሳንቲሞቻችን አንድ ገጽ በመሳሰሉት ዘንድ አንበሳ ለመለያ ምልክትነት አገልግሏል፡፡

ብዙ ሰዎች አንበሳ በህግ ማዕቀፍ የሀገራችን ብሔራዊ ወካይ ዱር እንስሳ የተደረገ ይመስላቸዋል፡፡ ያን እድል ግን አላገኘም፡፡ አንበሳ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ባለው ግዙፍ ስፍራ ከፍ ያለ ምልክት ኾኖ ኖረ እንጂ አንበሳን በህግ የማንነታችን ምልክት የማድረግ ስራ አልተሰራም፡፡

በእኔ እምነት አሁንም አንበሳ በኢትዮጵያ ቤተ መንግስት በክብር የተቀመጠ፣ ስፍራውን ከኢትዮጵያ ታሪክ ያልተነጠቀ ድንቅ እንስሳ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንበሳን በሚመለከት ባህሪው ላይ አነሱት የተባለው የመጻሕፋቸው ሀሳብ ይጠሉታል ብዬ እንድደመድም አያስደፍረኝም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሬ አንበሳ ብላቸው የሚደሰቱ በተቃራኒው በአወደሷት እንስሳ ስም ባሞግሳቸው የሚኾነውን እገምታለሁ፡፡ አንበሳም ኾነ ጦጣ ሳይንሳዊና መርህ የተከተለ ሥርዓትን አልፎ ኢትዮጵያ ብሔራዊ እንስሳ እንዲኖራት ማድረግ፣ ብሔራዊ ወፍ እንዲወክላት መቅረጽ፣ በብሔራዊ አበባ እንድትገለጽ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የቡና መገኛ ኾነን ብሔራዊ ፍሬ የሌለን ሀገር መኾናችንን ሳስብ እገረማለሁ፡፡

የብሔራዊ ምልክት አሰራር እንደ ህዝብ መዝሙር በህገ መንግሥት የሚገለጽ ኾኖ ጽኑ ይኾናል፡፡ ሂደቱ በሰለጠነ መልኩ ከተተገበረ ደግሞ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይቀየር የሀገር ዘለዓለማዊ ጌጥ ኾኖ ይኖራል፡፡ ይኼ በህዝቦች ሥነ-ልቦና፣ በዓለም ዘንድ በመወከል ክብር፣ የሀገርን ታሪክ በፍጥረት በመግለጽ ምስጢር ውጤታማ የሚያደርገን ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ቀን ሲያልፉ የሚመለከታቸው ቢያስቡበት ሸጋ ይመስለኛል፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top