በመጋቢት 5፣ 1520 አነስተኛ የስፔናውያን ጦር መርከቦች ከኩባ ደሴት ወደ ሜክሲኮ አመሩ፤ መርከቦቹ 900 የሚሆኑ የስፔን ወታደሮችን ከፈረሶች፣ ከጦር መሣሪያዎችና ጥቂት የአፍሪካ ባሮች ጋር ይዘው ነበር፤ ከባሮቹ አንዱ፣ ፍራንቼስኮ ድ ኤጋ፣ ከሁልጊዜውም የከፋ ጭነት በሰውነቱ ተሸክሞ ነበር፤ ምንም እንኳን ፍራንቼስኮ ባያውቀውም፣ በትሪሊዮን ከሚቆጠሩ ሕዋሶቹ መካከል የሆነ ባዮሎጂያዊ ቦምብ ተጠምዶ ጊዜውን እየቆጠረ ነበር – የፈንጣጣ ቫይረስ፤ ፍራንቼስኮ ወደ ሜክሲኮ ከገባ በኋላ ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ እንደአሸን መራባት ጀመረ፤ በመጨረሻም በቆዳው ላይ ሁሉ እየፈነዳዳ ፈጦ ወጣ፤
በትኩሳት እየተቃጠለ የነበረው ፍራንቼስኮ ሴምፖአላን በምትባል አንድ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የቀደምት አሜሪካዊያን ቤተሰብ ውስጥ እንዲተኛ ተደረገ፤ እርሱ ወደዚህ ቤተሰብ በሽታውን ሲያስተላልፍ፣ እነርሱም ጎረቤቶቻቸውን ለከፉ፤ በዐስር ቀናት ውስጥ ሴምፖአላን የመቃብር ስፍራ ሆነች፤ ስደተኞች በሽታውን ከሴምፖአላን ወደ ጎረቤት ከተሞች አስተላለፉት፤ ከከተማ ከተማ በወረርሽኙ እየተለከፉ በሄዱ ቁጥር፣ በሁኔታው የተሸበሩ ሰዎች ልክ እንደ መዐበል ወደ ሜክሲኮና ከዛም ባሻገር በመሰደድ በሽታውን አዛመቱት፡፡
በዩካታን ባሕረ ገብ መሬት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ማያዎች ሦስት እርኩስ አማልክት – ኢክፔትዝ፣ ኡዛንካክ እና ሶጃካክ – በሌሊት መንደር ከመንደር እየዞሩ ሰዎችን በበሽታው እየለከፉ ነው ብለው አመኑ፤ አዝቴኮች በቴዝካትሊፖካ እና በሲፕቶቴክ አማልክት ላይ በምናልባት ደግሞ በነጭ ሰዎች ጥቁር አስማት ላይ አላከኩ፤ ካህናትና ሐኪሞች ምክር ተጠየቁ፤ እነርሱ ግን ጸልዩ፣ በቀዝቃዛ ገላችሁን ታጠቡ፣ ሰውነታችሁንም ቅጥራን(ሬንጅ) ቀቡ እንዲሁም ጥቁር ጥንዚዛ ዳምጣችሁ በቁስሉ ላይ ቀቡ አሉ፤ ምንም የረዳው ነገር ግን አልነበረም፤ ወደ እነሱ ለመቅረብ እና ለመቅበር የሚደፍር ማንም ባለመኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖች በጎዳናዎች ላይ በሰበሱ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ መላው ቤተሰቦች እንደዋዛ ተጠራርገው ጠፋ፣ ባለሥልጣናት ቤቶች በሙታኖች ላይ እንዲደረመሱ አዘዙ፤ በአንዳንድ ሰፈሮች ውስጥ ግማሽ ሕዝቡ አለቀ፡፡
በመስከረም 1520 መቅሰፍቱ ወደ ሜክሲኮ ሸለቆ ደረሰ፤ በጥቅምት ወር ደግሞ የአዝቴክ ዋና ከተማ ወደሆነችው እና እስከ 250,000 ሰዎች ወዳስጠለለችው አስደናቂ ከተማ – ቴኖችቲትላን ሰተት ብሎ ገባ፤ በሁለት ወራት ውስጥም የአዝቴክ ንጉሠ ነገሥት ኩዊትላዋክን ጨምሮ ቢያንስ ሢሶውን ፈጀ፤ በመጋቢት 1520፣ የስፔን መርከቦች ወደ አካባቢው ሲደርሱ፣ ሜክሲኮ 22 ሚለየን የሚሆኑ ነዋሪዎች የነበሯት ሲሆን፣ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ 14 ሚሊየን ሰዎች ብቻ በሕይወት ነበሩ፤ ፈንጣጣ የመጀመሪያው ማዕበል ነበር፤ አዲሶቹ የስፔን ጌቶች ራሳቸውን በማበልጸግ እና የአገሪቱን ተወላጆች በመበዝበዝ ሥራ ላይ ተጠምደው እያሉ እስከ 1580 ድረስ ፍሉ፣ ኩፍኝና ሌሎች ተዛማች ገዳይ የበሽታ ማዕበሎች የሜክሲኮን ሕዝብ ቁጥር ከ2 ሚሊየን በታች አውርደውት ነበር፡፡
ከሁለት ምዕተ ዓመታት በኋላ፣ በጥር 1878፣ ብሪታንያዊው አሳሽ ካፒቴን ጄምስ ኩክ ሀዋይ ደረሰ፤ የሃዋይ ደሴቶች ተፋፍገው በሚኖሩ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች የተሞሉ ነበሩ፤ እነኝህ ሕዝቦች ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ሙሉ በሙሉ ተነጥለው የሚኖሩ ነበሩ፤ እናም በዚህ ምክንያት ለአውሮፓ እና ለአሜሪካ በሽታዎች በጭራሽ ተጋልጠው አያውቁም፤ ካፒቴን ኩክ እና አብረውት የነበሩ ሰዎች የመጀመሪያውን የፍሉ፣ የሳንባ ነቀርሳ እና የቂጥኝ በሽታ አምጪ ተሕዋሲያንን ለሃዋይ አስተዋወቁ፤ ተከታይ የአውሮፓ ጎብኝዎች በዚህ ላይ ታይፎይድ እና ፈንጣጣን ጨመሩበት፤ በ1853 በሃዋይ ከመዐቱ የተረፉት 70000 ብቻ ነበሩ፡፡
እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የበሽታ ወረርሽኝ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉን ቀጠለ፤ በጃንዋሪ 1918 በሰሜናዊ ፈረንሣይ ምሽጎች ውስጥ ወታደሮች በአንድ ልዩ በሆነ ለካፊ ቫይረስ – በቅጽል ስሙ የስፓኒሽ ፍሉ – በሺዎች መረፍረፍ ጀመሩ፤ ይህ የጦር ግንባር ዓለም ከዚያ ቀደም አይታ የማታውቀው ቀልጣፋ የዓለማቀፋዊ አቅርቦት መረብ መዳረሻ ነበር፤ ወንዶችና ወታደራዊ ቁሳቁሶች ከብሪታንያ፣ ከአሜሪካ፣ ከሕንድ እና አውስትራሊያ እንደጉድ ይፈሱ ነበር፤ ዘይት ከመካከለኛው ምስራቅ፣ እህልና ሥጋ ከአርጀንቲና፣ ጎማ ከማላያ እና መዳብ ከኮንጎ ይጓጓዝ ነበር፤ በምላሹ ሁሉም በስፓኒሽ ፍሉ ተለከፉ፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች – ከዓለም አንድ ሥስተኛው ህዝብ – በቫይረሱ ተያዘ፤ በሕንድ ከሕዝቡ 5 ከመቶ (15 ሚሊየን ሰዎች) የሚሆነው አለቀ፤ በታሂቲ ደሴት 14 ከመቶ የሚሆኑት ሞቱ፤ በሳሞአ 20 ከመቶ የሚሆኑት፣ በኮንጎ የመዳብ ማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ደግሞ ከአምስት ሠራተኞች መካከል አንደኛው በዚሁ ቫይረስ ሞቱ፤ በአጠቃላይ ወረርሽኙ አንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ50 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት አጠፋ፤ የአንደኛው ዓለም ጦርነት ከ1914 እስከ 1918 ድረስ 40 ሚሊዮን ሰዎችን ገድሏል፡፡
ምንጭ፡ ሆሞ ዲዮስ(የመጪው ዘመን አጭር ታሪክ)