Connect with us

ህወሓትና ይቅርታ

ህወሓትና ይቅርታ | በኦሀድ ቤንአሚ
Photo: Social media

ፓለቲካ

ህወሓትና ይቅርታ

ህወሓትና ይቅርታ
(ኦሀድ ቤንአሚ)

የሙስጠፌ መግለጫ መቀሌ አካባቢየሚፈጥረው ንዝረት ቀላል አይሆንም፤ በሕወሓት የትግል መዛግብት ውስጥ በክብር ስማቸው የተጻፈው ጀነራል ስም ከንጹሃን ደም ጋር ሲነሳ ለህወሓት የሃፍረት ግርዶ መጨመሩና ቁጣ መቀስቀሱ አይቀርም፤ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ግን ታሪኩ አዲስ አይደለም፡፡ ሲባል የኖረ ጉዳይ ነው፡፡

ከመግለጫው በላይ ግን ከባዱ ነገር ሙስጣፌ ያስቀመጡት የይቅርታ ካሳ ነው፡፡ ህወሓት ይህን ካሳ የመክፈል የሞራል አቅም እና አቋቋም ያለው እይመስለኝም፤ እንደተለመደው ወደ ጸረ-ተጋሩ የቅስቀሳ አጀንዳ ሊለውጠው ይችላል፤ “ራሳቸው ፈጥረውና በደርግ ጊዜ የተቀበረ አስከሬን አውጥተው የህወሓትን ስም ያጠፋሉ፤ የደርግ ልጆች እና ……” የሚል መግለጫ አውጥቶ የበለጠ የትግራይን ሕዝብ አንጀት መብያ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በተኣምር በትግራይ ሕዝብ ፊት ይህን ሊቀበል አይችልም፤ የማይታሰብ ነው፤

በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጃፓን ከኮሪያ እና ከቻይና እንዲሁም በቁጥጥሯ ስር ከነበሩ የኣካባቢው አገሮች አስገድዳ የወሰደቻቸውን ወጣት ልጃገረዶች ለወታደሮቿ ወሲብ እርካታ አገልግሎት አውላቸዋለች፤ የጃፓን ወታደሮች እነዚህን ኮሪያውያን እና ሌሎቹን ፍጹም ሰብዓዊነት በጎደለበት ሁኔታ ወሲባዊ ግፍ ፈጽመውባቸዋል፤ አንዳንዶች እነዛን የጦርነት ዘመን ሳይልፉ ቀርተዋል፤ የተረፉትም አሰቃቂውን የስነልቦና ጠባሳ ተሸክመው ኖረዋል፤ ቀሪው ዘመናቸው ምን ሊመስል እንደሚችል የማንኛውም ስነልቦና ሀሁ አንባቢ ግምት ጉዳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ጃፓኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ይቅርታ እንዲጠይቁና ካሳ እንዲከፍሉ ቢነዘነዙም አንገታቸው እንደደነደነ አሰርታት ተቆጥረዋል፤

ህወሓት ይህን ስህተት ተቀብሎ ይቅርታ መጠየቅ የማይችልባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉት፤ እነሱም አንደኛ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ያለውን መሰረት መሸርሸር ስለማይፈልግ ሲሆን ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ከሶማሌ ክልል በላይ በደል እንደተፈጸመባቸው የሚያምኑ ክልሎች ሊያነሱት የሚችሉትን ጥያቄ ስለሚፈራው ነው፤ ከዚህ በተረፈ ደግሞ ሊነሱ የሚችሉ የሕግ ጥያቄዎች ናቸው፤ ይህን ካመነ ጀነራሉ በአካል ሄደው ሳይሆን የሚፈጽሙት ሰዎችን ልከው ነው፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ይታወቃሉ፤ ስሞቻቸው የየምርቃናው በርጫ፣ የውስኪ ቤቶች ባንኮኒ እና የመንግስት ከፍተኛ መስሪያ ቤቶች ኮሪደሮች የዕለት ተለት የሃሜት አጀንዳዎች የሆኑ ሰዎች ናቸው፤ ስለዚህ ይቅርታ መጠየቁ ወንጀሉን ማመን ሲሆን ይህን ተከትሎ ደግሞ ለሚነሱ የፍትሕ ጥያቄዎች ተጠርጣሪ አካላትን አሳልፎ መስጠት ግዴታ ሊሆን ይችላል፤ ህወሓትን እንዲህ አይነት ድፍረት አይመቸውም፤

በሌላ በኩል ግን ለህወሓት ደጋፊ በተለይም የፓርቲውን ኃጢአቶች እንደ ስህተት አይቶ ሚዛናዊ ድምዳሜ መውሰድ ለሚፈልጉ የህወሓት ደጋፊ ምሁራን ተጋሩ አንገት መድፊያ ሲሆን ለጠላቶቹ ደግሞ የሞራል ልዕልናን ማሳያ ይሆናል፤ በዚሁ አተያይ በስመ- ፌዴራሊስት ኃይሎች በህወሓት ምህዋር ለሚሽከረከሩ የሌሎች ክልሎች ፓርቲዎች ክንድ ሰባሪ ነው፤ ነገር ግን ህወሓት ይህን ሁሉ ተጋፍጦ ይቅርታ የመጠየቁን ውሳኔ ካልተቀበለም የድርጊቱ ባለቤትነቱን ከጀነራሎቹ ራስ የሚወስደው እሱ ራሱ ነው፡፡ ፓርቲው እጁ እንዳለበት የሚያሳይ ሆኖ ነው የሚቀረው፤

የፕሬዚደንት ሙስጣፌ መግለጫ ባለፈው አስራምስት ቀን አካባቢ ተሞከረ ለተባለው መፈንቅለ-ክልላዊ መንግስት እጁ አለበት ተብሎ ለሚታማው ህወሓት የመልስ ምት ከሆነም ሌላ ኪሳራ ነው፤ በዚህ ሁሉ ግን ህወሓት የማይሸሻቸው ነገሮች እየበዙ እየሄዱ ነው፤ ለዚህ ነው የህወሓት ጉዳይ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ የማይሆነው፤ እንደዚህ አይነት በደሎች ከየአካባቢው እየወጡ የሚነዙበት ፋሽን ከተጀመረ ለፓርቲው ሌላ መውጊያ ጦር፣ የፓርቲውን መገለል የሚያባብስ እና በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚጠብቁት ተግባራት እንቅፋት አስቀማጭ ነው፤

እንደኔ እንደኔ ምክር ስጥ ቢሉኝ ይቅርታውን ጠይቆ ወንጀል የሰሩትን አሳልፎ መስጠቱ የበለጠ የሚያስከብረው ይመስለኛል፡፡ ህወሓት ጠላት በመፍጠር የሚወዳደረው እንደሌለ ዘመናት አሳየተውናል፤ አላስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ያልሆኑ እርምጃዎችን እየወሰደ ብዙዎችን አጥቷል፤ ማጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ጠንካራ ተገዳዳሪ ጠላትነት ለውጦኣቸዋል፤ በሶማሊያ ክልል የተፈጠረውም ከዚህ ብዙ የተለየ ላይሆን ይችላል፤

በዘመነ ኃይለሥላሴ ጊዜ የቀረ አንድን አስቸጋሪ አካባቢ እንዲገዛ ያገኘውን ሁሉ የቅጣት ስልትን ህወሓት በብዛት ይጠቀምበት ነበር፤ የአንድ አካባቢ ሰዎች በአመራሩ ካላመኑ እንደጠላት አይቶ መቀጣጫ ፈልጎ መበቀል እና አንዳንዴም አካባቢውን እንዳለ በመሰረተ-ልማት እና በሌሎች ከዛ ባለፉ መንገዶች መቅጣት የህወሓት መለያው ነበሩ፡፡ አሁን ተመልሶ ያን ማስተካከል የሚችልበት አቅም የለውም፤ ነገር ግን ይቅርታው ብዙ ነገር ሊፈውስ ይችላል፤ ሕዝብ ይቅር ባይ መሆኑን በተደጋጋሚ ያየነው ጉዳይ ነው፤ የተቀየመ ሕዝብ ግን አድፍጦ የተቀመጠ ጠላት መሆኑን አለመርሳቱ ጠቃሚ ነው።

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top