ዕለተ ዐርብ/ዓርብ/
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር» (፩ቆሮ.፩፣፲፰) በማለት እንዳስተማረው ዕለተ ዐርብ የአይሁድ ካህናት ያለበደል፣ ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ ዐደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው (ማቴ.፳፯፣፴፭-፸፭)፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ። የተቀበለውን ሠላሳውን ብርም ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተ ለራስህ ዕወቅ አሉት፡፡
ይሁዳ ተቀብሎት በየነበረውን ብር በቤተ መቅደስ በትኖ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባዕ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ (ማቴ.፳፯፣፫-፱) የሰው ልጆች አባታችን አዳም በመበደሉ ምክንያት በኃጢአት ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት፣ ፍጹም ድኅነት ያገኙለት ታላቅ ዕለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን የሚያስቡበት ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለክርስቲያኖች ግን ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት ነው። በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘንበት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡ጌታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ሰባት ነገሮችን ተናገረ። እነዚህም ሰባቱ ” አጽርሐ መስቀል ” በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦
” አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ማቴ 17፦46
” አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሉቃ 23፦34
” ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሀለሁ” ሉቃ 23፦4
” አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ሉቃ 23፦ 46
” እነሆ ልጅሽ፤ እነኋት እናትህ” ዮሐ 19፦26
” ተጠማሁ” ዮሐ 19፦28
” ሁሉ ተፈጸመ ” ዮሐ 19፦ 30
ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የተፈጸሙ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤
በሰማይ የተፈጸሙ
1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ
በምድር የተፈጸሙ
1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ
2. ምድር ተናወጠች
3. መቃብሮች ተከፈቱ
4. ብዙ ሰዎች ከሙታን ተነሡ
(ምንጭ:-ማኀበረ ቅዱሳን)