Connect with us

ትህትና ሁሉን ድል የሚያደርገው ምስጢር

ትህትና ሁሉን ድል የሚያደርገው ምስጢር
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ትህትና ሁሉን ድል የሚያደርገው ምስጢር

ትህትና ሁሉን ድል የሚያደርገው ምስጢር
የእኘ ዘመን ፈተና ትልቁ ትንሽ አለመኾኑ ብቻ ሳይኾን ትንሹ ትልቅ ነኝ ማለቱ ነው፡፡
ጸሎተ ሐሙስና ትህትና
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

ዛሬ ጸሎተ ሐሙስ ነው፡፡ በተለይም ለኦርቶዶክሳውያን ተዋህዶ ክርስቲያኖች ይህ ዘመን በየዓመቱ ታላላቆች በታናናሾች እግር ስር ወድቀው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተግባር እጽበተ እግር ሥርዓትን ያከናውናሉ፡፡ የትህትና ምሳሌ እንደ ሆነው ክርስቶስ ሁሉ ዝቅ ማለት ትልቅ ክርስቶስን የመምሰል ተግባር ነው ብላ የምታስተምረው ቤተ ክርስቲያን በዚህ ቀን የምታደርገው የእግር እጥበት ሥርዓት የትህትናን ታላቅነት በተግባር የምታሳይበት አንዱ ትውፊት ነው፡፡

ዓለም በዚህ ዘመን ከባዱ ፈተናዋ ትልቁ ትንሽ አለመኾኑ አይደለም፡፡ ትልቅ ሊኾን የሚወድ ይነስ ከሚለው ቃል የከፋ ልምምድ እያየን ነው፡፡ ያነሰው ትልቅ ነኝ ብሎ አደባባይ ይወጣል፡፡ ትንንሾች ትልቅ ነን ብለው ከፊት መጥተዋል፡፡ የእኛ ዘመን ፈተና ትልልቆቹ ክርስቶስን ለመምሰል ትንሽ ለመሆን አለመፈለጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ከትህትና ባለፈ ዓይነ አውጣነት ትሁት ያለመሆን የገዘፈ ችግር ሆኖ ታይቷል፡፡

ትንሹ ትልቅ ነኝ ብሏል፡፡ ትንሹ ከኔ የሚበልጥ የለም ብሎ ትህትናን ብቻ ሳይሆን እውነትን ቀርጥፎ በሚበላበት በዚህ ዘመን ትንሹ ችግር ከብዶ የሰው ልጅ አበሳ ኾኗል፡፡ ሰው ልቡ ደንድኗል፡፡ ሁሉም እኔ ተሰሚ ነኝ ወይም እኔ ነኝ መሰማት ያለብኝ ብሏል፡፡ የራሱን ማነስ ሲነግሩት የብሔሩን መግዘፍ የገንዘቡን መብዛት የሚናግር ትህትና ጠል ትውልድ እንዲህ ብዙ ፈተናዎች ሲገጥሙት ማየቱ የስራው ውጤት ነው ብቻ ብለን አናልፈውም፡፡ ይልቅ ሁላችን በትህትና እንሄድ ዘንድ ትህትና ከፍ ብትል እንዴት ሸጋ ነበር፡፡

ትህትና ሁሉን ድል ያደርጋል፡፡ እኛ እንደ ሀገር ትሁት አይደለንም፡፡ በደለኞች ነን አንልም፡፡ ይልቁንስ ዓለም በደለኛ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከባድ ጥፋት በመጣ ቁጥር ዓለም በሐጢአቱ ሞቷል ብለን እራሳችንን ከፍ እናደርጋለን፡፡ ውጤቱ ግን ይለያል፡፡

ትህትና ለሁሉ መፍትሔ ነው፡፡ ወደ ፈጣሪ ከሚወስዱ ፈጣን ጎዳናዎች አንዱ ትህትና ነው፡፡ የአብረሃም ልጆች እምነቶች ለትህትና ትልቁን ስፍራ ይሰጣሉ፡፡ ትህትና በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ትልቅ ቦታ ያላት ምስጢር ናት፡፡ ትሁት መኾን ሌላውን ማስቀደም፣ ለሌላው ቦታ መስጠት፣ ሌላው ትልቅ ነው ብሎ ክብርን መቸር እንጂ መበለጥና መሞኘት አይደለም፡፡
ዓለም ትህትናን ብልጥ እንዳአለመሆን ይቆጥረዋል፡፡ በርካታ የስነ ልቦና ጠበብት ነን የሚሉ ሰዎች ትሁት መሆን የስነ ልቦና ችግር አልያም በራስ ያለመተማመን ጉዳይ አድርገው ትውልድን ይሰብካሉ፡፡ መንፈሳዊ እሴቶች በስራ መብለጥን የሚደግፉ ኾነው እበልጣለሁ የሚለውን ቅስቀሳ ግን ይነቅፍታል፡፡

ይህን ጸሎተ ሐሙስ በሁሉ ነገር ትሁት የምንሆንበትና ዝቅ የምንልበት ያድርግልን፤ በሁሉ ነገር ዝቅ ስንል በሁሉ ነገር ከፍ እንላለንና፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top