” የተኩስ አቁም እርምጃ ያሻል… “ሻለቃ ዳዊት ው/ጊዮርጊስ | በታምሩ ገዳ
በቀድሞው መንግስት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ተቋቁሞ የነበረው የእርዳታ እና ማስተባበሪያ ኮሚሽንን የመሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ በአሀኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና፣ የሳምባ ቆልፍ ወረርሺኝ የተቀናጀ፣ፈርጣማ ፣ አስቸኳይ እና ሙያዊ ምላሽ ያሻዋል ፣አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነትም ሊደርግ ይገባል አሉ።
የወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካው ቦስትን የኒቨርስቲ በምርምር ስራ የተሰማሩት ሻለቃ ዳዊት በሰሞነኛው ዘለግ ያለ መጣጥፋቸው ላይ”በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁሉም አቅጣጫ በእቅድ እና በቅንነት ሊመራ ይገባዋል። በዚህ አጣዳፊ ወቅት ምንም አይነት የመረጃ እና የቅንጅት ክፍተት ላለመፍጠር ተግቶ መስራት ይጠበቃል”ሲሉ ወገናዊ እና ሙያዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የጸረ ኮሮና ወረርሽኝ ዘመቻውን እንዴት እና ማን ይምራው ?ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሻለቃ ዳዊት ሲመልሱ”ይህ ዘመቻ በፖለቲካ ካድሬዎች እና በአቀንቃኞች(አክቲቪስቴች)የሚዘወር ሳይሆን ፣የነጠረ ሙያ ያላቸው፣ጠንካራ ሰራተኞች፣በተማሩ እና ህይወትን ለማዳን ፍቅሩ ባደረባቸው ሰዎች ሊካሄድ ይገባዋል”ብለዋል።
የወረርሽኙ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዩች በቀር ከእንቅስቃሴ መታገድ(loced down) እና እራስን ከማራራቅ(Self distance) ውጪ አለማቀፋዊ እና ወቅታዊ መፍትሔ አለመገኘቱን ያሰመሩት የቀድሞው የእርዳታ እና ማስተባበሪያ ከፍተኛ ሹሙ ሻለቃ ዳዊት በተለያየ ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ አስከፊ ችግሮችን በድል አድራጊነት ያለፉት የኢትዮጵያ ህዝቦች ያ የቆየ ተሞክሮ ለተቀረው የአፍሪካ ህዝብ በገንቢ ጎኑ ሊጠቅም ይችላል” ግልጽ መመሪያ እና የማቴሪያል አቅርቦት ማፋጠን ፣ፖለቲካውን ግን በሁሉም አቅጣጫ ወደጎን ማድረጉን አንዘንጋ ።ዘመቻው በፌደራል እና የ ክልል ፖለቲከኞች ብቻ የሚካሄድ ከሆነ በህዝባችን ላይ ከወረርሽኙ የከፋ ኪሳራ እና አደጋ ሊከሰት ይችላል”ብለዋል።
በዚህ ፈታኝ፣እና አስጨናቂ ወቅት የህዝብ አመኔታ ማግኘት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን የጠቀሱት ሻለቃ ዳዊት “መንግስት በተቻለ መጠን ማንኛውንም መረጃ ለህዝቡ በግልጽነት እና በፍጥነት በማድረስ ተአማኒነትን ማግኘት እና አጋርንትን ማጠናከር የግድ ይለዋል” ያሉት ሻለቃ ዳዊት የጸረ ኮሮና ዘመቻው ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ” መንግስት ከአኮረፉ እና ዱር ቤቴ ካሉ ከማንኛውም ቡድኖች ጋር የሚያደርገውን ህጋዊ ያልሆኑ (unwarranted)ውጊያዎችን ሙሉ በሙለ እና በአስቸኳይ ማቆም፣ ጊዜያዊ የእርቅ ሰላም ስምምነት ማድረግ የሁሉም ተፋላሚ እና ወገኖች በተለይ ደግሞ የመንግስት ቀዳሚ ድርሻ ሊሆን ይገባል፣የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይደር፣አንጻራዊ ሰላም ሳይኖር የሰብአዊ አገልግሎትን በተሟላ መንገድ ማከናወን በጭራሽ የማይታሰብ ነው።” በማለት ሻለቃ ዳዊት የቀደመ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
በዚህ የመከራ እና የጭንቀት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ መከራው እና ችግሩ እንዲወገድ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ በመንግስት ላይ ትልቅ እምነት ጥሏል ያሉት ሻለቃ ዳዊት “ማንኛውም ባለጊዜ እና የመንግስት ሹማምንት አጋጣሚውን እና ስልጣኑን አላግባብ በመጠቀም ምስኪን ወገኑን እንዳያሳዝን” አደራ አዘል ተማጽኖአቸውን ፣ ወገናዊ ፣እና ሙያዊ አዘል ምክራቸውን አቅርበዋል።