Connect with us

ጅቡቲ ግን ምነው ‹‹ግብጽ ነኝ›› አለች

ጅቡቲ ግን ምነው ‹‹ግብጽ ነኝ›› አለች
Photo: Social media

ህግና ስርዓት

ጅቡቲ ግን ምነው ‹‹ግብጽ ነኝ›› አለች

ጅቡቲ ግን ምነው ‹‹ግብጽ ነኝ›› አለች | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ከወራት በፊት በአሜሪካ ድጋፍና አጋርነት የልብ ልብ የተሰማት ግብጽ የአረብ ሊግን ድጋፍ በጠየቀችው መሠረት ከሱዳን ውጭ ያሉት አገራት ተሰባስበው ፍርዴ ገምድል ውሳኔ ሲያሳልፉ ጅቡቲም አንዷ ነበረች፡፡ በጋራ ተጠቃሚነት ፈንታ የአንድ አገር የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ‹‹ከኢትዮጵያ ምድር በሚፈልቅ ወንዝ ግብጽ ትዘዝ›› አይነት ውሳኔ ሲተላለፍ ጅቡቲም እጇን አውጥታ ነበር፡፡ በዚህም የአረብ ሊግ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግሥትን ማዘኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አማካኝነት ገልጧል፡፡

ዛሬ ደግሞ ከሸገር የተገኘው መረጃ ‹‹በብድር ብር ተገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ ጅቡቲ ጋር ሲደርስ ‹‹በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ የእኔም ሕዝቦች የሚበሉት ሊያጡ ስለሚችሉ የተወሰነውን እቀቅለዋለሁ›› ብላ ጅቡዬ ማገቷን ያመለክታል፡፡ የዚቺን ብጣቂ አገር ወደብ ለመጠቀም እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚከፍለው የኢትዮጵያ መንግሥትም ‹‹ጅቡቲዬ እባክሽን እንደ ጅብ ማሰቡን ተይና በብድር የገዛሁትን መኮሮኒና ፓስታ ልቀቂልኝ›› እያለ በመማጸን ላይ መሆኑ ተገልጧል፡፡

እኛም ይሄንን ስንሰማ ከወራት በፊት የራሳችንን ወንዝ መገደባችንን የኮነነች አገር የራሳችንን መኮሮኒ አግታ ከመንግሥት ይቅርና ከህጻናት የማይጠበቅ ጨዋታ መጀመሯን ስንሰማ አሰብን ከማስታወስ ውጭ የምናኮርፍበት ወደብ ባይኖረንም ሹካችንን በመወርወር ብስጭታችን ገልጸናል፡፡ ብሎም የጅቡቲ ድርጊት ነገረኛ ሰውን ለመግለጽ የምንጠቀምበት አንድ አገራዊ አባባል አስታውሶናል፡፡
‹‹ጠብ ያለሽ በዳቦ!››
‹‹ጠብ ያለሽ በፓስታ››

ምክንያቱም ጅቡዬ ይሄን ያደረገችው መኮሮኒውን ሳይሆን ጠቡን ፈልጋ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ፓስታው የታገተው ለምግብ ተፈልጎ ሳይሆን ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ገሌ ፈርኦን ሆኖ ማዕቀብ እየጠላብን ነው፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በታች ሕዝብ ያላት ሚጢጢ አገር የ110 ሚሊዮን ሕዝብ እናት የሆነችውን ኢትዮጵያን ‹‹ከህዝብሽ ህዝቤ ይበልጣል›› ብላ የምትሳፈጣት ከግብጽ ጋር ሆና ነው፡፡

ይሄንንም ስታደርግ እንደ ድሮው ቢሆን ኖሮ ‹‹ካገትሽው መኮሮኒና ፓስታ በቁጥር የሚበልጥ ወታደሬን ልኬ ከፓስታው በፊት ቀቅዬ ቁርሴ ሳላደርግሽ ያገትሽውን ንብረቴን ልቀቂ›› ማለት ይቻል ነበር፡፡ በአድዋና በማይጨው ለነጻነታችን እንዳደረግናቸው ጦርነቶች ‹‹የፓስታውና የመኮሮኒው ጦርነት›› ተብሎ የሚጻፍ ታሪክ መፈጸም እንችል ነበር፡፡
ግን ልብ እና ሕዝብ ወደብ አይሆኑም፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ አገር በመሆኗ ኢንፖርት ከምታደርጋቸው የውጭ ምርቶች መሃከል ከ90 ፐርሰንት የሚበልጠውን የምታስገባው በጅቡቲ በኩል ስለሆነ ያለን አማራጭ አንድም በድርድር ለማስመለስ መሞከር፣ ሁለትም ‹‹ከጠቀመሽ ብዪው›› ብሎ መተው ብቻ ነው፡፡

በሌላ መልኩ ግን ይህ ጉዳይ ከጅቡቲ በኩል የሚጠብቀን የመጀመሪያው ፈተና እንጂ የመጨረሻው ስለማይሆን መንግሥታችን እራሱን መገምገም አለበት፡፡ ‹‹ጎረቤት አገራት ላይ ኮሽ ባለ ቁጥር ገላጋይ ሆኜ መድረሴ፣ እንደ አህጉር እያሰብኩ ከአገር አገር መመላለሴ ተጽእኖ ፈጣሪነቴን ማሳደግ ሲገባው እንዴት ሊያጠፋው ቻለ?›› ብሎ እራሱን መፈተሸ ግድ ይለዋል፡፡

ትናንት ኮሮናን ለመቆጣጠር ጃክ ማ ለአፍሪካ ያበረከተውን ቁሳቁስ የኢትዮጵያ መንግሥት ተረክቦ በአየር መንገዳችን በኩል ሲያከፋፍል የድርሻዋን የወሰደችው ጅቡቲ ዛሬ በባሕር በሯ የመጣን የምግብ ቁሳቁስ አግታ ንቀቷን ስትገልጽ፣ ኤርትራ ደግሞ ‹‹ለእኔ በተላከው ማስክና ኪት እናቴ ኢትዮጵያ ትጠቀምበት›› በማለት ከእንቢታዋ ጋር ጥርጣሬዋን ይፋ አድርጋለች፡፡ ይሄም ሁኔታ ዲፕሎማሲያችን ልፋት እንጂ እድገት እያመጣ አለመሆኑን ገላጭ ነውና መንግሥታችን ‹‹ከጎረቤት አገራት ጋር ያለኝ ግንኙነት ልቅ ነበር ወይንስ ልክ?›› ብሎ መገምገም አለበት፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ጅቡቲ ከወደብ አልባዋ አገራችን የምታገኘውን ዶላር ከማስቀጠል ይልቅ ለግብጽ ስትል አሰብን የመሆን አዝማሚያ እያሳየች ነውና… አማራጭ የባሕር በር የምናገኝበትን መንገድ ማመቻቸት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top