ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በመከራ ሰዓት የተፈተ ማህበረሰባዊ አጋርነትን ያሳየ ድንቅ ተቋም፡፡
የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ መስጂዶች፣ ሆስፒታሎች፣ አውራምባ ማህበረሰብና አረጋውያን መርጃዎች የንጽህና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
ለስምንት ሆስፒታሎች የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ደጋፊ ለሌላቸው ከሃምሳ ስምንት ሺህ በላይ እንጀራ ድርቆሽ አዘጋጅቷል፡፡
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
እንዲህ ያለው የዩኒቨርሲቲ ጠባይ በሀገራችን የተወለደው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተክኖበታል፡፡ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ እንደ እድሜው አይደለም፤ ብዙ ርቀት ፈጥኖ ተጓዘ፤ ብዙ ርቀት ስኬትን ተጎናጸፈ፡፡ ከሽልማቶቹ በላይ ከህዝብ ልብ “የእኛ ነህ” የሚል የድል ጽዋን አነሳ፤ ኮራሁበት፡፡ በተለይ የዚህ ሰሞን ተግባሩን ዓለም ይሰማው ዘንድ ወደድሁ፡፡
አካላዊ ርቀትን እውን በማድረግና ህዝብን በማስተማር የቀደመው አልነበረም፡፡ ያኔ ሀገር እየተጋፋችሁ ታጠቡ በሚል ስሜት ውስጥ ሆና ደብረ ታቦር የተማሪ መመገቢያው ርቀት እንዲጠብቅ አደረገ፡፡ መታጠብ ከርቀት ጋር እንዲሆን በተግባር አሳየ፡፡
ደብረ ታቦር ከዩኒቨርሲቲዋ ቀድሞ ሀገር የሰራ ቀደምት የአብነት ትምህርት ቤት ዩኒቨርሲቲ ያላት የነ ተክሌ አቋቋም የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ናት፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ሁኔታ ሀገር ከመረዳቱ ቀድሞ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በከተማዋ ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች 2000 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና በስጦታ ለግሷል፡፡ በከተማው የሚገኘውን ሰናይ የነዳያን መርጃንና የአውራምባ ማህበረሰብንም በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ የንጽህና መጠበቂያዎች ድጋፍ አለኋችሁ ብሎ ነበር፡፡
መጋቢት 15 ቀን ደግሞ እንዲሁ በደብረ ታቦር መስጂድ ለንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ፈሳሽ ሳሙናዎችን በስጦታ ለግሷል፡፡ በዚህ ሳያቆም ለከተማው ማረሚያ ቤትም ተመሳሳይ የፈሳሽ ሳሙናዎችን አበርክቷል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችም እንዲሁ በዩኒቨርሲቲው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በስጦታ ተብርክቶላቸዋል፡፡ በዞኑ የሚገኙ ስምንት ሆስፒታሎችም ለኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ የሚውል መሳሪያ በመግዛት ድጋፍ ማድረጉ አጋርነቱን አድምቆ ያሳየበት ነው፡፡ ለለይቶ ማቆያም ህንጻዎቹን ዝግጁ አድርጓል፡፡
ከዚህ ሁሉ መባተል በኋላ 58500 እንጀራዎችን በማስጋገር የድርቆሽ ዝግጅት ማድረጉንና እስከ ቀበሌ በሚወርድ ስልት ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች እገዛውን ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑ የሚመሰገን ብቻ ሳይሆን ልምዱ ሊወሰድ የሚገባ ተቋም ያደርገዋል፡፡