Connect with us

ካነበብኩት

ካነበብኩት
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ካነበብኩት

ካነበብኩት
ተረፈ ወርቁ

“… የእውነት ንጋት በልቤ ውስጥ ያበራ ዘንድ ዕድሜዋን ሁሉ በፍቅር፣ የእምነት እንባ ላነባችልኝ እና በጸሎቷ ለተጋደለችልኝ ውድ እናቴ፣ የዛሬውን የአንድ ቀን እንባዬን አደራ ማንም እንደ ከንቱ እንዳይቆጥርብኝ…፤”
[የሰሜን አፍሪካ/የሂፖው ሊቀ ጳጳስ፣ የሥነ መለኮት ሊቅና ፈላስፋ፣ ቅዱስ አውግስጢኖስ በእናቱ በቅድስት ሞኒካ እረፍተ-ሞት ምክንያት ከተናገረው የተወሰደ ከ360-440 ዓ.ም.]

በኮረና፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መስሪያ ቤታችን ሠራተኞችን ከሥራቸው ባሕርይና አስፈላጊነት አንፃር እንደየሁኔታው እየታየ በየተራ ቢያንስ ለጊዜው የሳምንት ጊዜ እረፍት እንድንወስድና በቤታችን እንድንቆይ ዕድሉን አመቻችቶልናል። በዚህ መሠረትም ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ከሥራ ገበታዬ እረፍት ወስጄያለሁ። እናስ እረፍቱ እንዴት እያለፈ ነው ለምትሉኝ የኀልዮተ አምባ ወዳጆቼና ቤተሰቦች የእረፍት ጊዜዬ እንቅስቃሴዬን በተመለከተ ከዘወትር ማስታወሻዬ በጥቂቱ ላጋራችሁ ወደድኹ።

ይህ ማስታወሻ አንድም ሌሎቻችሁም በዚህ ፈታኝና አስጨናቂ ወቅት፣ ለራሳችሁም ሆነ ለሌሎች ወገኖችልችሁ እየወሰዳችሁት ካለው ጥንቃቄ ጀምሮ በቤት ውስጥ ቆይታችሁን፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችሁን፣ የግል ተሞክሮአችሁንና ትዝብታችሁን…ወዘተ. እንድታጋሩን ለማንቃት፣ ለማነሳሳትም ጭምር ነው።

እንደሚታወቀው መንግሥትና የጤና ባለሙያዎች፤ “በቤት ውስጥ በመቀመጥ የኮረና ቫይረስን ወረርሽኝ እንከላከል!” በሚል ባስተላለፉት መመሪያ መሠረትም አብዛኛው እንቅስቃሴዬን በመገደብ አብዛኛውን ጊዜዬን የቢሮ ሥራዎችን በቤት ውስጥ በማከናወንና እንዲሁም በዋናነት ደግሞ ወቅቱ ወርኻ ጾም/የሱባኤ ወቅት በመሆኑ በጸሎት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በንባብ በማሳለፍ ላይ ነኝ።

እናም በዚህ የእረፍት ጊዜዬ ከበርካታ ዓመታት በፊት ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከልም፤ በሂፖው ሊቀ ጳጳስ፣ የሥነ መለኮት ሊቅ፣ ፈላስፋ፣ ጸሐፊ፣ ንግግር አዋቂ እና ሰባኪ ወንጌል- በቅዱስ አውግስጢኖስ፣ ከዛሬ 1600 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፈውን፤ “Confession/ኑዛዜ” የሚለውን ግሩም መጽሐፍ ዳግመኛ እያነበብኩ ነበር።

የሰሜን አፍሪካ ምድር ካፈራቻቸው የክርስትና ሥነ-መለኮት ምሁራን፣ ፋላስፎች፣ ጸሐፍትና ሰባኪያን መካከል የሂፖው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አውግስጢኖስ ስሙ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቅስ አባት ነው። ሊቀ ጳጳስ አውግስጢኖስ በምሥራቃውያኑ (በኦርቶዶክስ እና በካቶሊካውያን) ሆነ በምዕራባውያኑ ክርስቲያኖች (በሉተራውያንና በፕሮቴስታንት) ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትንና ተቀባይነትን ያገኘ ታላቅ፣ መንፈሳዊ አባት ነው።

አውግስጢኖስ ወደ ክርስትና ሃይማኖት ከመምጣቱ በፊትም በዘመኑ ከነበሩት የተለያዩ እምነቶች እየተዘዋወረ እውነትን ፍለጋ ብዙውን ጊዜውን አሳልፏል፤ ማስኗል፣ ደክሟል። በንግግር ችሎታውና በፍልስፍና እውቀቱ እጅግ ላቅ ያለ አእምሮ ያለው ይህ ሰው በሰሜን አፍሪካ፣ በሮምና በግሪክ ባሉ ትልልቅ ትምህርት ቤቶች የንግግር ችሎታ እና ፍልስፍና መምህር በመሆን ሠርቷል።

በዘመኑ ካሉ ፈላስፎች እና ንግግር አዋቂዎች መካከል ብዙ ክብርን እና ዝናን የተቸረው አውግስጢኖስ በግል ሕይወቱ ግን አብዝቶ ደስታ የራቀው፣ በምድር ላይ በሚያየውና በሚሰማው ክሥተት ሁሉ የሚጨነቅና አብዝቶ የሚጠይቅ፣ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?፣ እውነትስ የትኛው ነው? የክፋት ምንጩስ ምንድን ነው… ወዘተ በሚሉ የሕይወት እንቆቅልሾች ነፍሱ አብዝታ የምትጨንቅበት፣ የምትዋትትበት ሰው ነበር።

ታዲያ ይህን የልጇን አውግስጢኖስን ጭንቀትና እውነትን ፍለጋ ድካሙ ያሳዘናት እናቱ ሞኒካ ለበርካታ ጊዜያት ለውድ ልጇ፤ ፈጣሪ አምላክ እውነትን ይገልጽለትና ወደ ክርስትና ሃይማኖት ፊቱን ያቀናለት ዘንድ ሁልጊዜም በጸሎትና በእንባ ወደ አምላኳ፣ ወደ ጌታዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ትማጸንለት ነበር።

ልጇ ዘላለማዊ የነፍስ የእረፍትና ሰላምን ወደሚሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለስላት ዘወትር በጸሎት የምታፈሰውን እንባዋን የታዘበው የሮማ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ቅዱስ አምብሮስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሏት ነበር። “ሞኒካ ሆይ ይህን ያህል እንባ ያፈሰስሽለትና በጸሎት የተማጸንሽለት ልጅሽ አይጠፋም። አንድ ቀን አንቺ ወደገባሽበት ሰላምና ዘላለማዊ እረፍት መምጣቱ አይቀርም… እናም አይዞሽ ተጽናኚ፤ ተስፋሽን በአምላክሽ ላይ ይሁን!” በማለት ያበረታትና አጽናናቷት ነበር።

እግረ መንገድ እንዲል ደራሲ ጋሼ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፤ እግረ መንገዴን የሮማው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አምብሮስ ከመንፈሳዊ አባትነቱ እና ከሥነ መለኮት እውቀቱ ባሻገር አንድ የሚጠቅስበት ታሪክ አለው። ይኸውም በአንድ ወቅት በሮም ግዛት ረኻብ በመከሰቱ በአብያተ ክርስትያናት ውስጥ የተከማቹ ወርቁንና ብሩን ከግምጃ ቤት እያወጣ በግዛቱ ላሉ ድሆች እህል እየገዛ እንዲከፋፈል ያደረገበት መንፈሳዊ ቆራጥ ውሳኔው ስሙ ይነሳል።

“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ አበው ወእመው፤ የእኛው ሊቅ አለቃ ገብረ ሃና የአቡነ ሃራ ገዳም መምህርና አለቃ በነበሩበት ዘመን በአካባቢው ክፉ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት በገዳሙ የተከማቸውን እህልና ብር እያወጡ በሙሉ ለድኃው አደሉት። በዚህ ያዘኑት የገዳሙ አባቶች ክፉው ቀን ሲያልፍ አለቃ ገብረ ሃናን ዐጤ ምኒልክ ችሎት ድረስ መጥተው እንዲህ ሲሉ ከሰሷቸው። “ጃንሆይ ሆይ! ሺሕ ዓመት ይንገሡ! ለክፉ ቀን ያስቀምጥነውን የገዳማችንን እህል፣ ገንዘብ/ሀብት አለቃ አባከኑብን፣ ፍርድዎን ይስጡን?!” በማለት ከሰሷቸው።

አለቃም፤ “ጃንሆይ! ክርስቶስ ያመልክትዎ፣ መቼም አቡነ ሃራ ከሰማይ ቤት መጥተው በገዳማቸው የተከማቸውን እህል አይበሉት፣ ገንዘቡን አይጠቀሙበት… ልጃቸውን አይድሩበት እናም ቃል ኪዳናቸውን ተስፋ አድርገው በምልጃቸው ለሚማጸኑ የመንፈስ ልጆቻቸው በረኻብ አለንጋ ሲገረፉ እያየው ዝም ማለት ይገባኝ ነበር እንዴ?! እናም የአቡነ ሐራ ገዳምን እህልና ገንዘብ፤ ታላቁ መጽሐፋችን:- ‘ለድሆች ሰጠ፤ ለምስኪኖች በተነ፣ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።’ እንዲል ነው በስማቸው የተከማቸውን ሀብት ንብረት አውጥቼ ለድሆች ማደሌ፤ ይህን ማድረጌ፤” የሚል ምላሽ ሰጡ።

ዐጤ ምኒልክም ግራ ቀኙን ከሰሙ በኋላ አለቃ ገብረ ሃና ከዚህ ክስ ነጻ መሆናቸውን በመናገር ለአቡነ ሐራ ገዳም አባቶችና መነኮሳት ገንዘብና ከብት በመስጠት አሰናበቷቸው። የሮሙ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አምብሮስና አለቃ ገብረ ሃናን የታሪክ ተመሳሳይነት እየተደንቅን፤ ከሰሞኑን ቅዱስ አውግስጢኖስ በጻፈው መጽሐፍን መሠረት አድርጌ የጀመርኩትን መጣጥፌን ከሰሞኑን እንድምመለስበት ተስፋ በማድረግ ልሰናበት።

የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር በተግባር ላይ በማዋል ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከኮረና ወረርሽኝ የመታደግ ኃላፊነታችንን በትጋት እንወጣ! የፈጣሪ አምላክ ፍቅር፣ ምሕረትና ቸርነት አይለየን!!

N.B. ሌሌቻችሁም የኀልዮተ-አምባ ወዳጆች ከንባብ ትሩፋታችሁ፣ ከበጎ አገልግሎታችሁ፣ ከዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴያችሁ- ገጠመኞቻችሁንና ትዝብታችሁን ታካፍሉን ዘንድ አደራ እላለኹ።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top