Connect with us

ክህደትን ከተንበርካኪነት ሲያዛንቅ የኖረ ስብዕና!? ግልጽ ምላሽ ለአይተ ስዩም መስፍን

ክህደትን ከተንበርካኪነት ሲያዛንቅ የኖረ ስብዕና!? ግልጽ ምላሽ ለአይተ ስዩም መስፍን
Photo: Social media

ፓለቲካ

ክህደትን ከተንበርካኪነት ሲያዛንቅ የኖረ ስብዕና!? ግልጽ ምላሽ ለአይተ ስዩም መስፍን

ክህደትን ከተንበርካኪነት ሲያዛንቅ የኖረ ስብዕና!? ግልጽ ምላሽ ለአይተ ስዩም መስፍን

ከነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል እስከ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረው የዘመናዊ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ የደለበ ታሪክ እንደ አቶ ስዩም መስፍን የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሰጠና በሕዝብ እና በሀገር ላይ አይን ያወጣ ክህደት የፈፀመ ዋሾ በዲያጎን ፋኖስ እግር እስኪቀጥን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ቢፈለግ አይገኝም።የትህነግ/ሕወሀት መስራች ታጋይና የፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ‘ ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ‘ በተሰኘው ማለፊያ መፅሐፋቸው ፣ ” የሄጉ የድንበር ኮሚሽን ኢትዮጵያንና ኤርትራን ካከራከረ በኋላ ሚያዚያ 5 ቀን 1994 ዓ ም ብይኑን ሲሰጥ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ከ70 ኪሎ ሜትር ካሬ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ግዛት ለኤርትራ ለመስጠት ወሰነ። ለኤርትራ በተሰጠው መሬት ውስጥ ለጦርነቱ ኃጢያት ተሸካሚ ( ስኬፕጎት ) የሆነችው ባድመ ስትካተት ፤ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በታሪክ ምንም የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቶበት የማያውቀውን የኢሮብ መሬት በከፊል … እነ ዓይጋን ፣ ወርዓትለን ፣ ዘገልባን ፣ ለኤርትራ ተወሰነ። ” ከዚህ ውሳኔ በፊት የነበረውን ሒደት መለስ ብለው ለገመገሙት አቶ ገብሩም ሆኑ ሌሎች የዘርፉ ልሒቃንና ፖለቲከኞች የድንበር ክርክሩን በበላይነት ያስተባብሩ የነበሩት የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም ቢያንስ የሚከተሉትን አምስት ዋና ዋና ሀገራዊ ክህደቶችን ፈፅመዋል ለማለት የሚያስደፍር መሰናዘሪያ ያነሳሉ።

የእርሳቸውና የጓዶቻቸው ልጆች ከሀገር በተዘረፈ ሀብት በአሜሪካና በአውሮፓ ውድ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ተንደላንቀውና ተቀማጥለው እየተማሩ በአንጻሩ እናቱ ነገ ያሳልፍልኛል ይጦረኛል ብላ በከፋ ድህነት እንጨትና ውሃ ሽጣ ያሳደገችው በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠር ሩጦ ፣ ዘሎ ያልጠገበ ሀገር ወዳድ ወጣት መስዋዕት ሆኖ በቢሊዮኖች የሚገመት የሀገር ሀብት ወድሞ በውድ ዋጋ የተገኘን የኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ድል እንደ መደራደሪያ አቅም ( ሌቬረጅ) በመጠቀም የሀገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያስከብር ድርድር ማድረግ ሲገባው የአልጀርሱን ስምምነት በግዕብታዊነትና በተንበርካኪነት መንፈስ ተጣድፎ የሀገሪቱን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት ሰውተው ለመደራደር መስማማታቸው የመጀመሪያው የክህደቱ ዘፍጥረት (ጄነሲስ) ነው።

ይህ አልበቃ ብሎአቸው አቶ ስዩም በሔጉ የድንበር ኮሚሽን ለመሟገት ብቃት ያላቸውን አለማቀፍ ጠበቆች አቁሞ ፣ የታሪክ ልሒቃንንና ታሪካዊ ሰነዶችን አደራጅቶ መከራከር ሲገባቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ ጠበቆችን ይዘው እና ተገቢውን ክብደት ሳይሰጡ ወደ ሙግቱ መግባታቸው በዜጎቿ አጥንትና ደም ተከብሮ የኖረውን ድንበር ሳይቀር ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ ማድረጋቸው የክህደቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ነው ። የክህደቱ መፅሐፍ መቼ በዚህ ይቋጭና። አቶ ስዩም በወቅቱ ትኩረታቸው የትህነግን ዘባተሎ አይዶሎጂ በአሮጌ እራፊ መጣፍ ፣ መስፋት እና ማምሻም እድሜ ነው ብለው ስልጣናቸውን ማሰንበት እንጂ እንደ ትላንቱ ታሪካቸው የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳያቸው አልነበረም። ለይምሰል ፣ ለታይታ ፣ ከአንገት በላይ ፣ “ምን ይሉን! ? ” በሚል የድንበር ኮሚሽኑን ፍርደ ገምድልነት ተቃውመው ይግባኝ እንኳ እንዳይሉ የኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ማቅማማትና ማንገራገር ለመቀበል በአልጀርሱ ስምምነት አስቀድመው በጡት አባታቸው አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መፈራረማቸው የክህደቱ ሶስተኛ ምዕራፍ ነው።

አቶ ገብሩ ድርጅታቸው ሀፍረትና አዘኔታ ያውቅ ይመስል አሳፋሪና አሳዛኝ ያሉትን አራተኛውን የክህደት ምዕራፍ አብረናቸው እንግለጥ ፣የሔጉ የድንበር ኮሚሽን በ1900 ዓ.ም ውል መሰረት ጸሮናንና ሌሎች በኤርትራ ግዛት ስር ያሉ ቀበሌዎች ወደ ኢትዮጵያ መካለል አለባቸው ብሉ ሲወስን ኢትዮጵያን ወክለው የቀረቡ የአቶ መለስና ስዩም ተሟጋቾች ” ይህ የእኛ መሬት አይደለም። መሬቱ የኤርትራ ነው ። ” ብለው የኮሚሽኑን ዳኞች ሳይቀር ኩም አድርገዋቸዋል። መቼም በእግር ኳስ እንኳ አጥቂዬ አቋቋሙ ኦፍ ስለነበር በ” ፌር ፕሌይ ” ጎሉ ይሻር የሚል ማናጀር በሌለበት ሔግ ላይ በኢትዮጵያ ጠበቆችና ተደራዳሪ ተብዬዎች የተመዘዘው የ”ፌር ፕሌይ” ካርድ በሔግ ችሎት ታሪክ ታይቶ አያውቅም። ለነገሩ የኤርትራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል” ህዝበ ውሳኔ ” ከሻዓብያ በላይ ልጁን እንደሚድር አባ ፣ እማ ወራ አደግድጎ ሽር ጉድ ፣ ጠብ እርግፍ ብሎ አዋክቦ ያለ ሻዓብያ ፍላጎት ያስፈፀመ ቡድን ጸሮና ጉዳዩ ባትሆን አይደንቀንም። ቡድኑ በአልባንያ ሶሻሊዝም ተጠምቆ በቀዩ የማኦ መፅሐፍ ጸሎቱን ስለሚያደርስ ታላቁን መፅሐፍ ስለማያውቀው ጥቅሱን ገልብጠን ” በትልቁ ያልታመነ በትንሹ አይታመንም። ” ብለናል። በኤርትራ፣በሱዳን ድንበርና በክልል ወሰን መታመን ያልፈጠረበትን በባድመ ፣ በጾረና እንዴት እናምነዋል ። ሰውየው የክህደቱን ቅጥልጥል ቀጥለውበት አምስተኛ ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል።

በፓርላማዊ ቀርበው በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቀርበው ቀኝ እጃቸውን አንስተው የፈፀሙትን ቃለ መሀላ አፍርሰው እና የተናገሩት ከሚጠፋ ፣ የወለዱት ይጥፋ ከሚል ኩሩ ሕዝብ የተገኙ የቀደሟቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጠብቀውት የኖረን ተቋማዊ የሀቀኝነት ባህል ጥሰው የውሸት ነጭ ላብ በራ ራሳቸው ላይ እየተንቆረቆረ፣ በጭንቀት ቁና ቁና እየተነፈሱ መግለጫ ይሰጡበታል ከተባለው ሶስትና አራት ሰዓት ዘግይተው ፣ አይናቸውን በጥሬ ጨው ታጥበው በአንድ ለእናቱ ኢቲቪ ቀርበው ፣ “ባድመ ብቻ ሳይሆን ፣ ሌሎች በኤርትራ ስር ሰፊ ግዛቶችን ጭምር ያካተተ መሬት ለኢትዮጵያ ተሰጥቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦር ሜዳ ያስመዘገበውን ድል በዲፕሎማሲውና በሕጉ ሜዳ በማረጋገጡ እንኳን ደስአላችሁ። ” በማለት የ20ኛው መክዘ ክህደት የውሸቶች ሁሉ ቁንጮ የሆነውን ነጭ ውሸት አንደበታቸው እየተሳሰረ ፣ ድምጻቸው እየተርገበገበ ከሀዛኑ በቅጡ ባላገገመ መልክዓ ነዙት።

ሰሞኑን የበሰበሰ … ዝናብ አይፈራም እንዲሉ በአናቱ የለቀቁት ነጠላ እንጉርጉሮ ደግሞ በምልሰት (ፍላሽ ባክ) ከሀዲና ተንበርካኪ የሆነውን ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕናቸውን ተመልሰን እንድናጠነጥን ፣ እንድንገርብ መግፍኤ ሆኖናል። በነገራችን ላይ አንባሻ ሳይቆርሱ አቶ ስዩምንና መሰሎቻቸውን ” ተንበርካኪ ” ያሏቸው ከልጅነት እስከ እውቀት ፣ ከበርሀ እስከ አዲስ አበባ ፣ ከበርሀው የውጭ ጉዳይ ኮሚቴነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ፣ ከቻይና አምባሳደርነት እስከ አማካሪነት ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል እንደጅ መዳፋቸው ጠንቅቀው ልቅም አርገው የሚያውቋቸው የትግል አጋራቸው አቶ ገብሩ አስራት ናቸው። ተንበርካኪነት አጎብዳጅነት ፣ ተሸናፊነት፣ ወኔ ቢስነት ፣ አቋመቢስነት ፣ አለቃው ምንዝሩ ዝለል ሲለው ለምን የሚል ሳይሆን ስንት ጊዜ የሚል ፣ በአለቃው አእምሮ የሚያስብ ፣ በሳንባው የሚተነፍስ ፣ አለቃ አምላኪ ፣ በአለቃ ጥላ የሚውል ፣ በራሱ እምነት የሌለው ፣ ወዘተ ማለት ነው። በዚህ ተንበርካኪ ተክለ ሰብዕና ውሸት ክህደት ሲጨመርበት ሰው የመሆን የቅስም ልዕልናን ያሳጣል። ከሰውነት አእማዶች ወሳኝ የሆነውን ራስን የመሆን የመታመን አምዱን ካጣ ሰብዕ ሙላት ጎድሎታል። ከሰውነት ተራ ወርዷል። እንዲህ ባለ ቀውስ፣ ውድቀት ፣ ክስረትና ልምሻ ያለ ሰው ደግሞ አይደለም እንደ ኢትዮጵያ ላለች ትልቅ ሀገር ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ላለ ሕዝብ ለልጁ ለቤተሰቡ ምንም የማለት የቅስም ልዕልና የለውም።

በክህደትና በተንበርካኪነት የሀፍረትን የውርደትን ሸማ የተከናነበ ስለ ሀፍረት ፣ ስለ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ትንፍሽ የማለት ሞራላዊ ወኔ የለውም ። ሰውየው የቅስም ልዕልና ባይኖራቸውም አብሮ ባደገ ግብዝነትና እብሪት ተገፋፍተው ሰሞኑን ከወደ መማጸኛ ከተማቸው ያየሰው ሽመልስ በተባለ  ጋዜጠኛ ፣ በመማጸኛ ቴሌቪዥን ቀርበው የቅስም የ(ሞራል) ልዕልና እንዳለውና ታማኝ ሀገር ወዳድ ፖለቲካዊ ተክለ ሰብዕና እንዳነጸ ዜጋ” የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አሳፋሪ ነው። …” ብለዋል። እንግዲህ አሳፋሪ ነው የተባለው ንግግር በአንድ መድረክ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” የህዳሴው ግድብ የተጀመረው ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። ” ብለዋል በሚል መነሻ ነው። ሆኖም የቃለ መጠይቁ አላማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እንዳልሆነ ልብ ይሏል። አላማው የአቶ ስዩምን ክህደት በታላቁ የህዳሴ ግድብ አበረክቸዋለሁ በሚሉት አስተዋፅዖ ማጣፋትና ማወራረድ ነው። የከሰረን ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕናን አፈር ልሶ እንዲነሳ ታኮ የማድረግ ያልተሳካ ጥረት ነው።

ይሁንና ቃለ መጠይቁ በተቃራኒው የሕዝብ ቁስል እንደገና እንዲያመረቅዝ ፣ የተፈፀመበትን ክህደት መልሶ እንዲያንሰላስል እና በልጆቹ ከንቱ መስዋዕትነት እንዲብከነከን ፣ እንዲቆዝም አድርጎታል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርግጥ “የህዳሴው ግድብ የተጀመረው ለፖለቲካ ፍጆታ ነው።” ብለው ከሆነ የፖለቲካዊ ትክክለኝነት (ፖለቲካል ኮሬክትነስ ) ጥያቄን ከማጫር ባለፈ ምንም ስህተት የለውም ።ሁልጊዜ ደግሞ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን ማስታመም አይጠበቅም። እውነት በፖለቲካዊ ትክክለኝነት ስም መኮስመን የለባትም ። የአህጉሩን ፣ የመካከለኛው ምስራቅን ፣ የአለማቀፍ ማህበረሰቡን እና የምዕራባውያንን ጂኦ ፖለቲካ እንደ አዲስ የሚበይን ፤ ለዘመናት ተከብሮ የኖረውን የግብፅን የ”ተፈጥሮአዊ” ባለመብትነት የማንአህሎኝነት ትርክት በተግባር የሚያስቀይር ፤ 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታበረክት ባለመብት ሀገር መሆኗን የሚሞግት ፤ የ110 ሚሊዮን ሕዝብን የመልማት መብት ለማረጋገጥ የተነሳ ግራንድ ፕሮጀክት ፤ በጨለማ የሚኖር ከ30 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የህዳሴው ግድብን ያህል ሕዝባዊ ምልክት የሆነ ( ፍላግሽፕ ፕሮጀክት) ይቅርና በእያንዳንዱ ጎጥ የሚገነባ ጤና ኬላ ፣ ክሊኒክ ፣ ምንጭ ማጎልበት ከጀርባው ፖለቲካዊ ፍጆታን ታሳቢ ማድረጉ አጠያያቂ አይደለም።

እንደ ትህነግ/ኢህአዴግ ያለ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በተመለከተ ሕዝባዊ አመኔታ የሌለው ድርጅት የሚያቅዳት እያንዳንዷን ፕሮጀክት ከፖለቲካዊ ፍጆታ አኳያ ማየት ትክክለኛ ግምገማ እንጂ የሚያሳፍር ምንም ነገር የለውም። ለሀገር ጥቅም ቢያስብ ኖሮ ድሀ እናት ከልጆቹ ጉሮሮ ቀምታ የለገሰችውን ፣ ቦንድ የገዛችበትን ሀቅ በጠራራ ባላዘረፈው። የኤፈርት ፣ የጥቂት የትህነግ ቤተሰቦች መበልጸጊያ ባላደረገው። ለሜቴክ ሰጥቶ ባልቀለደበት ፣ የሞሰቦ ሲሚንቶ ማራገፊያ ባላደረገው። አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ቀውስ ላይ ባልጣለው። በግሌ የትህነግ ቤተሰባዊ ቡድን የህዳሴውን ግድብ እንደ ሕዝቡ፣ እንደ ሀገሪቱ በእዳ መያዣነት የተጠቀመበት እንጂ ለሕዝብ ጥቅም ብሎ የጀመረው ፕሮጀክት አይደለም። አንድን ሕዝብና አካባቢ ነጻ ለማውጣት በተሳሳተ ትንተናና መደምደሚያ በርሀ የወረደ ፤ በአጋጣሚ እጁ ላይ የወደቀችን ሀገር እንደ ደም ካሳ የሚያይ ፣ የእርዳታ እህልን ሽጦ ሕዝቡን እያስራበ ጠመንጃ የሚገዛ አረመኔ ፣ 80 ብሔር ብሔረሰብ እየመራ ከወርቅ ሕዝብ መፈጠሬ ያኮራኛል ፣ አክሱም ለወላይታ ምኑ ነው ? ስንቶች በአድዋ፣ በዶጋሌ ፣ በመተማ ፣ በማይጨው፣ በናቅፋ፣ በካራማራ፣ በባድመ ፣ በጾረና ፣ በቡሬ ፣ በዱር በገደሉ ደማቸውን ያፈሰሱለትን አጥንታቸውን የከሰከሱለትን ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነው ብሎ የሚያዋርድ ጠባብ መሪ፣ ድንገት ከመሬት ተነስቶ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ ሕዝቡ በሀገሩ ጉዳይ የመወሰን መብትና ነጻነት እንዳለው ለማረጋገጥ የተወጠነ ፕሮጀክት ነው ቢል ማን ይሰማዋል? ማንስ ያምነዋል ?በምንስ ሒሳብ ነው ለሀገር ተቆርቋሪ የሚሆነው። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው መስሪያ ቤቱን በአብዛኛው በአንድ ብሔር አባላት መሙላታቸውን፣ በየኤምባሲው የሚሾሙ አምባሳደሮችን ከሀገራዊ ተልዕኮ ይልቅ የኤፈርትን አላማ እንዲያሳኩ ማሰማራታቸውን፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር እያሉስ የትህነግን የኤፈርትን ተልዕኮ ማሳካት ላይ መረባረባቸውን ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑን እሳቸው ቢዘነጉትም እኛ ትላንት የሆነ ያህል እናስታውሰዋለን።

ለነገሩ ይህን ጥሬ ሀቅ አይደለም እኛ ሀገሬዎች የውጭ ሀገር ጸሐፍት፣ ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች በየኮሪደሩ በየኮክቴሉ የሚያነሱ የሚጥሉት እውነት እንደነበር አይዘነጋም። በዋቢነት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንን ብናነሳ ፣ ” አቶ መለስ ታላቅ መንግስት ለመምራት ቢታደሉም ከጠባብዋ የአድዋ መንደር አስተሳሰባቸው መውጣት ግን አልቻሉም። ከዚህ የጎሳ ዛጎል ( ሼል ) መቼ ሊወጡ እንደሚችሉ አይገባኝም። “ሲሉ ግርታቸውንና ስጋታቸውን ማጋራታቸውን ትንታጉ ፣ ደማሙ ጋዜጠኛ ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ በአንድ ሸጋ መጣጥፎ ማድረሱን አልዘነጋም። የሚያሳዝነው አቶ መለስ አፈሩ ይቅለላቸውና ከጎሳ ዛጎላቸው ሳይወጡ ማለፋቸው ሳያንስ በሙት መንፈስ የሚታመሱት ቋሚ ጭፍራዎቻቸውም (ሌጅንስ) ከዛጎሉ እንዳይወጡ የሚስጥር ቁልፉን ሳይነግሯቸው ወደ ማይቀሩበት መውረዳቸው ነው።

እንደ መቋጫ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጀመረው ለፖለቲካዊ ፍጆታ ነው ማለታቸው ምንም ስህተት እንደሌለው ሊሰመርበት ይገባል። በእያንዳንዱ የመንግስት እንቅስቃሴ ፣ የልማት ስራ ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ በውስጠ ታዋቂነትም ሆነ በግላጭ ፖለቲካ አለ ። ፖለቲካ ባለበት ፖለቲካዊ ፍጆታ እንደ ጥላ ይከተለዋል ። ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ውሳኔ ፊትም ሆነ ጀርባ ፖለቲካ አለ። ነበር። ማርሽ ቀያሪ ከሆነው ልማታዊ ፋይዳው ባልተናነሰ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ውሏል ። ወደፊትም ይውላል። የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ይፋ እንደሆነ፣ የመሰረት ድንጋይ እንደተጣለ ለአቶ መለስም ሆነ ለሚመሩት ድርጅትና መንግስት ቅቡልነት ( ሌጅትሜሲ ) የተጫወተውን ክቡድ አስተዋጽኦ ማንም ሊክደው አይችልም ። አይደለም ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ፕሮጀክት ፣ ለሸማቾች የሚቀርብ ስንዴና ዘይት ፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ አለው። ይህ አለማቀፍ ልምምድ ፣ አሰራር ነው።

የአሜሪካ ሴኔትና ኮንግረስ ሰሞኑን ትራምፕ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የጠየቀውን 2 ትሪሊዮን ዶላር ለማፅደቅ ሪፐብሊካኖችና ዴሞክራቶች በዚህ ቀውጢ ሰዓት እንኳ ፖለቲካን ታሳቢ አድርገው ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገቱ የነበረው የየፓርቲያቸውን ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ( ኮንስቲቲዎንሲ ) ታሳቢ አድርገው ነው። ቀራጮች ( ሪፐብሊካኖች ) ከአስቸኳይ ጊዜ በጀቱ ከፍ ያለው ለ1 በመቶው ባለጠጋ ታላላቅ ኩባንያዎችና ለአየር መንገዶች እንዲውል ሲሟገቱ ዴሞክራቶች ደግሞ ለዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል ፣ ለአነስተኛ ንግድና ስራ ፈጣሪዎች ከፍ ያለ በጀት እንዲመደብ ተፋልመዋል። እንዲህ ባለ ክፉ ቀን እንኳ ፖለቲካ ከፊት መሰለፉ ፤ የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታሳቢ መደረጉ አልቀረም። በነገራችን ላይ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስት የኖቨል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርጉት አኩሪ ርብርብ እና እየሰጡት ያለ በሳል አመራር ውጤታማ ከሆነ ከፈጣሪ ጋር ውጤታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ ፣ አወንታዊ ፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ ሲኖረው አያድርገውና ካልተሳካ ደግሞ አሉታዊ ፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ ይኖረዋል ። የሰው ልጅ መንግስት የሚባል ተቋም መስርቶ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጥንተ ጊዜ አንስቶ ፣ በአሶር በባቢሎን ይሁን በፐርዥያ አልያም በሮማን ወይም በቤዛንታይን አልያም በኦቶማን አጠቃላይ አሰራር ከፖለቲካ ተለይቶ አያውቅም። ወደ ፊትም መንግስታዊ አሰራር ከፖለቲካዊ አንድምታና ፍጆታ ተነጣጥሎ ከቶ ሊታይ አይችልም።

አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top