Connect with us

የአላዋቂነታችን ሸማ ሲገለጥ

የአላዋቂነታችን ሸማ ሲገለጥ
Face masks are the new fashion in central Milan © MARCO OTTICO/EPA-EFE/Shutterstock

ዜና

የአላዋቂነታችን ሸማ ሲገለጥ

የአላዋቂነታችን ሸማ ሲገለጥ | (ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

ትላንት ማታ በአሜሪካን ድምፅ በጣልያን በኮሮና ቫይረስ የተያዘች አንዲት ኢትዮጵያዊት ልብ የሚነካ ቃለምልልስ እያዳመጥኩኝ ከፊል ልቦናዬ የእኛን አገር ሁኔታ እያብሰለሰለ ነበር። ኢትዮጵያዊቷ የጤና ባለሙያ ስትሆን የኮሮና ቫይረስ የያዛት በሥራ ባህርይዋ የተነሳ ነው። ኢትዮጵያዊቷ በቫይረሱ መያዟ እንደታወቀ ከባለቤትዋና ከአንድ ልጅዋ ጋር በቤትዋ ውስጥ ራሷን አግልላ እንድትቆይ ተደርጋለች። በቫይረሱ መያዝዋን በምርመራ ከማወቋ በፊት ምንም አይነት የህመም ምልክት እንዳልነበራት ተናግራለች። የጤና ተቋማት በበሽተኞች በተጨናነቁባት ጣልያን እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በቤት ውስጥ በአንድ ክፍል ራስን ለ14 ቀናት ከቤተሰብ ጭምር አግልሎ መቆየት ወይንም ራስን ማስታመም የግድ ሆኗል።

ቫይረሱ በአንድ ሰው ላይ ቢገኝም የቤተሰብ አባላት በሙሉ (በቫይረሱ ቢያዙም፣ ባይይዙም) ለ14 ቀናት ከቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም። አንዳንድ የተጓደሉ ነገሮች ሲኖሩ የሚያቀርብ ተቋም ደውሎ ማስመጣት እንጅ ከቤት ለሰከንድም ቢሆን መውጣት በህግ የሚያስጠይቅ ድርጊት ነው። እንግዲህ ይህቺ ሴት የምትወዳቸውን ቤተሰቦችዋን በቅርብ ርቀት እያየች፤ የገዛ ልጅዋን ቀረብ ብሎ መሳም፣ መጨበጥ… እንኳን ተከልክላ መቆየት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመረዳት ነብይ መሆን አይጠይቅም።

በዚህ ላይ የጤና ሙያተኛ ሆኖ የሌሎች ባልደረቦች ሞት ጭምር በአይን አይቶ በሽታን ማስታመም እጅግ ከባድ እና ድርብ ድርብርብ ጉዳት ነው።

የታማሚዋ ባል ለቪኦኤ ሲናገር በሽታው በራቸውን አንኳኩቶ እስኪገባ ድረስ ያን ያህል ትኩረት ሰጥተውት እንዳልነበር ፣ ችግሩን ሲያዩት ግን ከባድ መሆኑን አስረድቷል።

አዎ!.. በኢትዮጵያ እንዲህ አይነቱ ክፉ ቀን ከመምጣቱ በፊት ቢያንስ እቤት አርፎ በመቀመጥ፣ የሁለት ርምጃ ያህል ርቀትን በመጠበቅ፣ መጨባበጥና መሳሳምን ለጊዜው እንደጎጂ ባህል በመውሰድ፣ እጅን አዘውትሮ በመታጠብ… የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንደሚቻል እየተሰጡ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች የማይሰሙ ሰዎች በመሀል አዲስአበባ በብዛት ማየት የአላዋቂነታችንን ጥግ የሚያሳብቅ ነው። ከምንም ነገር በላይ አንተ ራስህን ለመከላከል ያደረከውን የፊት መሸፈኛ እና ርቀትህን ለመጠበቅ ያደረከውን ጥረት ከኩራት እና ሌሎችን ከመጠየፍ አንፃር የሚያይ የመሀል ከተማ ሰው በዚህ ሰዓትም በስፋት ማየት ለካስ የአላዋቂነታችን ጥግ ይህን ያህል ነው እንዴ የሚያስብል ነው።

እኔ ያደረኩት ጥንቃቄ አንተንም ለመጠበቅ መሆኑን አለመረዳት የመጨረሻው የድንቁርናችን፣ የአላዋቂነታችን፣ የአለመሰልጠናችን መገለጫ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በዚህስ ሁኔታችን አያድርገውና የጣልያን የከፋ ቀውስ ሩብ ያህሉ እንኳን ቢከሰትብን እንደምን እንቋቋመው ይሆን? ፈጣሪ ይሁነን እንጅ የእኛስ ነገር ታጥቦ ጭቃ መሆኑ፣ የአላዋቂነታችን ውሀ ልክ ከፍ ማለቱ በእውነቱ የሚያሳፍር፣ አንገት የሚያስደፋ ነው።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top