መንግሥት እንደመንግሥት፣ እኛም እንደማኅበረሰብ እንዘጋጅ | (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
በ1911 ዓ.ም በሀገራችን በተከሰተው የኅዳር በሽታ (ስፓኒሽ ፍሉ) የተነሳ የሞተው ሰው እስከ 40 ሺህ እንደሚገመት መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ጽፈዋል፡፡ በሽታው አሁን ዓለማችንን ከገጠማት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ብላታ መርስዔ ሀዘን እንደሚሉት፣ በወቅቱ በሽተኞች በምግብና በውኃ እጦት የተነሳም ይሞቱ ነበር፡፡ ‹‹ በዚያን ወራት በአዲስ አበባ የነበረውን ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ፡፡ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውኃ ሲያድሉ ሰነበቱ፡፡ በእግዚያብሔር ቸርነት ከበሽታው አምልጠን ነበርና እኔና ጎጃሜ ኃይለ ማርያምን ውኃ በገንቦ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከቤቱ ደጃፍ ሲደርሱ እኛን እውጪ አስቀርተው እሳቸው ውኃውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር፡፡›› ይላሉ፡፡
በኮሮና ቫይረስ የተነሳ በዓለም እየደረሰ ያለው መጠኑ አይታወቅ እንጂ እኛ ዘንድም ሊደርስ ይችላል፡፡ ከተማው ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ሁሉም ቤቱ መቀመጥ ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህ ቤትን ዘግቶ መቀመጥ ግን መዳኛ ብቻ ሳይሆን መሞቻም ይሆናል፤ እቤታቸው ውስጥ መሶብ የሌላቸው፣ ይዘውት የሚዞሩት ፌስታል መሶባቸው የሆነ በርካቶች ናቸው፡፡ ለነዚህ ሰዎች ቤት መዋል ከኮሮና ሞት ቢከልላቸውም ለረሀብ ሞት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ተነጥለው የሚዘጉት ቤት የሌላቸው ጎዳና የሚኖሩትም ረሀብ ይጋረጥባቸውዋል፡፡ ለነዚህ ወገኖቻችን መነጠል ከመሞቻ መንገድ ምርጫነት አይዘልም፡፡ የሚበላው ለሌለው 3 ከመቶ የሚገድለው ኮሮና መቶ በመቶ ከሚገድለው ረሀብ ይሻለዋል፡፡
ገንዘብ ያለን ቤታችን እስኪጠብ ቀለባችንን እያከማቸው ነው፤ ካልበዛ መጠንቀቅ ጥሩ ነው፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎችም በሽታውን ከስግብግብነታችን አጣምረው፣ ዋጋ ቆልለው ገንዘብ ይሰበስባሉ፡፡ ይህ ለማንም አይጠቅምም፡፡
በየሰፈራችን የአቅማችንን ያህል ገንዘብና ቁሳቁስ እናሰባስብ፡፡ ይህ በእድር፣ በመኖሪያ ሰፈር ማኅበራት፣ በየኮንዶሚኒየሙ ባሉ የጽዳት ኮሚቴዎች፣ . . . ወዘተ. አማካኝነት ሊከናወን ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት፣ ጠቅላላ ከተማው የሚዘጋ ከሆነ በየአካባቢያችን የሚኖሩ ባለዕለት ጉርሶችን ልንመግብ እንዘጋጅ፡፡ ይህ ደግሞ መከናወን ያለበት ዛሬ ነው፡፡ ጊዜያዊ መመገቢያዎች በኮንቴነርና በቆርቆሮ በየሰፈሩ ይሰራ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር እያሰራው ያለውና ሥራው እየተገባደደ ያለው ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ የሚቻል ከሆነ በከፊልም ቢሆን ማምረት እንዲጀምር ይደረግ፡፡ መንግሥት እንደመንግሥት ይዘጋጅ፡፡ እኛም እንደማኅበረሰብ እንዘጋጅ፡፡