Connect with us

በጎንደር፤ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከለከለ

በጎንደር፤ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከለከለ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

በጎንደር፤ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከለከለ

በጎንደር፤ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከለከለ

ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

የተከበራችሁ የጎንደር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን:-

በአሁኑ ወቅት ከመሠረቱ እየተለወጠ ባለ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዓይነቱ አዲስ የሆነ ሪፎርም በማካሄድ ላይ ናት፡፡ ምክንያቱም የተለየ ታክቲክ ተከትለን ሪፎርም አካሂደን መለወጥ ካልቻልን ልማት ማስቀጠልም ማኅበራዊ ሠላማችንን ማስጠበቅም አንችልም፡፡ ሀገራዊ ሆነ ክልላዊና አካባቢያዊ ለውጡ ሁለት መልክ ያለው ሲሆን እጅግ የሚያማልል ተስፋን የጫረ በተቃራኒውም ከፊት ለፊታችን ፈተናችንን የሚያበዙ ተግዳሮቶችም ያሉበት ነው፡፡

ስለሆነም በሀገራችን፣ በክልላችን ብሎም በከተማችን ከቀውስ የሚያወጣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድሎቻችን የሚያሰፋ የሪፎርም ታክቲክና ስትራቴጅ ተነድፎ እየተተገበረ ነው፡፡

የከተማችንን ሁኔታ ስንመለከት ሀገራዊ ለውጡ ጥሎን እንዳይሄድ ወደ ኋላ ከተጎተትን ሌሎቹ ከደረሱበት መድረስ ስለሚያቅተን በድሮ ስም፣ ክብርና ዝና ብቻ የዘመኑን ፈተና ማለፍ ስለማንችል ለሀገርም ለዓለምም አስደማሚ የሆነ የድሮ አባቶቻችን ክብርና ዝናችንን የሚመጥን ሁለንተናዊ ሪፎርም ውስጥ መግባት ግድ ይለናል፡፡

የጎንደር ከተማን ከሀገራዊ ሁኔታ የሚያመሳስላት በአንፃሩም ደግሞ የተለየ የሚያደርጓት ሁኔታዎች አሉ፡፡

የከተማችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መድከም፣ የደኅንነት ቀውስና አለመረጋጋት እንዲሁም የሠላም መታጣት በከተማችን ባለፉት ወደ 400 የሚጠጉ ዓመታት ያካበትነውን የከተማነት ታሪካችን፣ በእጃችን ያሉትን የከተማችን ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቻችን እያሳጣን ነው፡፡

በከተማችን የፀጥታ፣ የሠላምና የደኅንነት ችግሮች የከተማው ሕዝቦች አንድነት አለመጠናከር ይስተዋላል፤ ይህም የከተማዋን ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና የንግድ እንቅስቃሴ ክፋኛ በመጉዳቱ የዚህን ችግር ምክንያት ማወቅ፣ መተንተንና ከመላው የከተማችን መፃኢ ዕድል እያሳሰባቸው ካሉ ወገኖች ጋር በመቅረብ መለየት፣ መግባባትና ለመፍትሔው መሯሯጥ የግድ የሚልበት ምክንያት ዋነኛ የወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና የኢኮኖሚ ምንጮች ወደ መንጠፍ አቅጣጫ እየሄዱ በመሆናቸው ነው፡፡

ከምንም በላይ የከተማችን የሠላምና ደኅንነት ሁኔታ ኢ-ተገማች በመሆኑና ያልተረጋጋ በመሆኑ መዋከቡ ሲበዛና የከተማ አስተዳደሩ አመራርና ሕዝብ ባልሰከነ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ የከተማዋን የሠላም መታጣት ችግር የበለጠ እያወሳሰበው መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥነትና የጎበዝ አለቅነት እየተበራከተ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በዚህም የከተማችን ቅስም እስከወዲያኛው እንዲሰበር ለሚፈልጉ ለከተማው ክፋ የሚያስቡ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ኃይሎች በሙሉ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርን መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

የጎንደር ሕዝብ አብዛኛው ወጣትና ትኩስ ኃይል ነው፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ አጥነትና የኢኮኖሚ ችግር አለበት፤ በርካታ የጤናና ማኅበራዊ ችግር እንዲሁም የከተማው የሠላምና የደኅንነት መታጣት ችግር ይህንን የብረተሰብ ክፍል የበለጠ ተጎጅ እያደረገው ነው፡፡

ስለሆነም የጎንደር ከተማ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ቅድሚያ የከተማው ሕግና ሥርዓት ሠላም የሰፈነበት በማድረጉ ሂደት መሪ ተዋናይ በመሆን ከተማዋ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል እንድትሆን መሥራት አለበት፡፡

የተከበራችሁ የከተማችን ሕዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን

የአማራ ሕዝብ እየታየ ያለውን ሀገራዊ ክልላዊ ለውጥ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታግሏል፣ ደም ገብሯል፡፡ የጎንደር ከተማ ሕዝብም የመጀመሪያውን የለውጥ ችቦ በመለኮስ ግፍና በደል እንዲቆም፣ ፍትሐዊነት እንዲሰፍን፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እንዲመለሱ የለውጥ ፋና ወጊነቱን ያስመሰከረ ሕዝብ ነው፡፡ ለለውጡም መላው ሕዝባችን ፋኖ ተሰማራ በሚል አኩሪ ገድል ፈፅሟል፡፡ አፋኙ ኃይል ወደ አንድ ጥግ እንዲገፋ አድርጓል፡፡ የክልላችን የለውጥ ሠራዊት የሆነው በክልሉ በተለይም በከተማችን ያለው ሕዝባዊው ፋኖ ከለውጡ በኋላ መላ ቀልቡንና አቅሙን ወደ ልማት በማዞር ፀረ ድህነት ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በተጓዳኝም የመላው የለውጥ ሐዋሪያ የሆነው የአማራ ሕዝብ የወል መጠሪያ የሆነውን ፋኖን በማንገብ በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ የአማር ክልል ሕዝቦችን ጥቅም የሚጎዳ አመለካከትና ተግባርን በሰለጠነ አግባብ በሠላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየታገለ ይገኛል፡፡ እውነተኛው የፋኖ ንቅናቄ የመላው አማራ ክልል ሕዝቦች የለውጥ ንቅናቄ መጠሪያ ሁኖ ለለውጡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ማንም ደፍጥጦት የሚያልፍ ጉዳይ አይደለም፡፡

ነገር ግን አሁን በተለይም በከተማችን እየተፈፀመ ያለው ጉዳይ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ፋኖነት በሕዝብ አእምሮ ውስጥ ያለ በዋናነት የአማራ ክልል ሕዝቦች አስተሳሰብ ነው፡፡ ፋኖነት ሕዝባዊነት ነው፡፡ ፋኖነት ለሕዝብ ፍትሕ፣ ለሠላም፣ ለልማት፣ ለአንድነት በአጠቃላይ ለተገፋ ሕዝብ መቆምና መወገን ነው፡፡ ፋኖነት ለተጎዱ፣ ላልተጠቀሙ ባይተዋርነት ለሚሰማቸው አጋር መከታ መሆን ነው፡፡ ፋኖነት ዘር፣ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቋንቋ አይገድበውም፡፡ ፋኖነት የዓድዋ፣ የማይጨው፣ የካራማራ፣ የ2008ቱ የጎንደር ሕዝባዊ ማዕበል መጠሪያ ስም ነው፡፡ ፋኖነት ለተወሰነ ቡድን የተሰጠ ማዕረግ ወይም ሹመት አይደለም፡፡ ፋኖነት የሕዝብ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሕዝባዊ የማዕረግ ስም እንጅ በሕዝብ ስም የሚምሉ እና የሚገዘቱ የጥቂት ሕገ ወጥ ቡድኖች የግል ጥቅም ማካበቻ ወይም የኑሮ ዘይቤ አይደለም፡፡

ነገር ግን አሁን በከተማችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአካባቢያችን ከትክክለኛው ፋኖ ዓላማ ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጁ የታጠቁ ኃይሎች የተደራጁበት የውሸት ምክንያት የተለየ ከመሆኑም በላይ ጥቅም ማግበስበስ ዓላማ አድርጎ የተሰበሰበ ኃይል ነው፡፡ በዚህ ሕገ ወጥ ቡድን መደራጀት በአሁኑ ወቅት ለሕዝብ መታገል ሳይሆን የኑሮ ዘይቤ የመተዳደሪያ ገቢ ማግኛ ዘዴ ሆኗል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ለትክክለኛ ሕዝባዊ ዓላማ ለመታገል መስሏቸው ተደራጅተው የሕገ ወጡ ቡድን አጠቃላይ አካሄድ የሚፈፅማቸው ፀያፍ ድርጊቶች አልጥማቸው ሲል ራሳቸውን ያገለሉ አካላትን አብነት አድርጎ ማንሳት ይቻላል፡፡

በከተማችን ያለው ከዋናው ፋኖ ዓላማ ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ በቡድን ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለዚህም በቂ የሰው፣ የሰነድ፣ የድምጽ እና የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መረጃዎች አሉ፡፡ ከሚፈፅማቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መካከል ታጥቆና ተደራጅቶ በከተማው ይንቀሳቀሳል፤ ያለምንም ከልካይ ኬላ ጥሶ ከከተማ ይወጣል፤ ይገባል፤ ሰው ያግታል፤ ግድያ ይፈፅማል፤ ዘር ቆጥሮ የግለሰብ ቤት ነጥቆ ካምፕ ያደርጋል፤ ከባለሀብት በግዴታ ገንዘብ ይሰበስባል አንዳንዴም ይቀጣል፤ የከተማ መሬት ታጥቆ አጥሮ በመያዝ ቤት ይሠራል፣ በፖሊስ እጅ ያለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ እስር ቤት ጥሶ ገብቶ ያስፈታል፤ ሕግ ጥሶ የወረደን የጦር መሣሪያ ታጥቆ ፖሊስ ጣቢያ በመውረር ዘርፎ ያመጣል፤ አስከሬን አጅቦ በመምጣት ጎንደርን በተኩስ ይንጣል፤ መሸታ ቤት ገብቶ ጠጥቶ አልከፍልም ይላል፤ በተደጋጋሚ በልዩ ልዩ የከተማው አካባቢዎች ጥይት ይተኩሳል፤ ታዋቂ ግለሰቦችን በቡድን ተደራጅቶ የቡድን መሳሪያ ጭምር ታጥቆ ያጅባል፤ ታጥቆና ተደራጅቶ የመንግሥት ተቋማትን፣ የፓርቲ ቢሮዎችን ይከብባል፤ ያስፈራራል፤ አመራር ለመግደል ያቅዳል፡፡

ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን እያወቀ የክልሉ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ኃይል በሠለጠነና በሠላማዊ መንገድ ያለ ደም መፋሰስ ከዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቱ ታቅቦ የመንግሥት ተገዳዳሪ ኃይል ሳይሆን ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት አድርጓል፡፡ በተለይም የተቀመጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መስፈርቱን የሚያሟሉ ወደ ክልሉ የፀጥታ መዋቅር እንዲካተቱ፣ መተዳደሪያ የሌላቸው በከተማ ብድርና መስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲያገኙ፣ በኢንቨስትመንት አካባቢዎች በእርሻ ለመሠማራት ለሚፈልጉ ደግሞ የእርሻ መሬት እንዲሰጣቸው፣ በቂ መተዳደሪያ ያላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በእነዚህ መፍትሔዎች የማይስማማ ብቻ ለከተማችን ሕዝብ ሠላምና ደኅንነት ሲባል መንግሥት ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድ መፍትሔዎች አስቀምጧል፡፡

በእነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ከቀናት በኋላ ከክልሉ ከፍተኛ አመራር ጋር ውይይት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ በነበርንበት ጊዜ ሁሌም በሕገ ወጥ መንገድ መቀጠል የሚፈልጉ የቡድኑ አባላት አዳዲስ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ፈፀሙ፡፡

እነዚህን የመፍትሔ አማራጮች እያሳየንና ብዙዎቹ ፈቃደኝነታቸውን እያሳዪ ባሉበት ሁኔታ የሕገ ወጡ ቡድን አባላት ጎንደር ከተማ ላይ ሐሙስ መጋቢት 10/2012 ከቀኑ 11፡00 ከአራዳ ክፍለ ከተማ ብጥብጥና ሁከት በማስነሳት ከጀርባው በአካባቢው ባሉ የሕገ ወጡ ቡድን ታጣቂዎች ታጅቦ የመኪና መንገድ በልዩ ልዩ ቁሳቁሶች እየዘጋ ልዩ ልዩ ፅንፈኛ መፎክሮችን እያሰማ ወደ ዞኑ ፖሊስ መምሪያ በመሄድ በሕንጻውና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተሞከረ ሲሆን አመፁንም የከተማችን የፀጥታ ኃይል በፍጥነት ደርሶ በትኖታል፡፡

ይህ ምልክት ማምሻውን ተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ ለማቀጣጠልና ከተማዋን ወደ አጠቃላይ ቀውስ ለመውሰድ የሚደረግ ዝግጅት መኖሩን ያረጋገጠው የከተማችንና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጋራ ኮማንድ ፖስት የሕዝባችን ሠላምና ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ተጨማሪ የፀጥታ መዋቅር በተመረጡ አካባቢዎች ስምሪት አደረገ፡፡ በዚሁ ዕለት ምሽት 1፡00 አካባቢ ማራኪ ክፍለ ከተማ ሸዋ ዳቦ አካባቢ በአካባቢው ሲያልፉ በነበሩ በአካባቢያችን የተሰማሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት ላይ በተከፈተ ተኩስ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል፡፡

ይህ ታጥቆና ተደራጅቶ የሕይወት መሠዋዕትነት እየከፈለ የፀጥታ ኃይላችን በዚህ ሕገ ወጥ ቡድን ተመሳሳይ አፀፋ መሰንዘር አልፈለገም ነበር፤ ይልቁንም የፀጥታ ኃይላችን የሕዝብ ልጅ መሆኑንና ዳግም ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረበት አኩሪ ገድል ነበር፡፡

ይህንን ጉዳት ያደረሰው ሕገ ወጡ ኃይል ይህንን ድርጊት ከፈፀመ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ ወደመሸገባቸው ቦታዎች ሸሽቶ በመደበቁ የክልላችን የፀጥታ ኃይል አባላት የመሸገበትን አካባቢ በፍጥነት ለመቆጣጠርና ጥቃት አድራሹን ቡድን በቁጥጥር ሥራ ለማዋል ፈጥኖ ቦታዎችን ቢቆጣጠርም ቡድኑ ተኩስ ከፍቶ ከአካባቢው ተሰውሯል፡፡

የተከበራችሁ የከተማችን ሕዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን

ችግሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በሚቀጥሉት ቀናትም ሕገ ወጥ ሰልፍና ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ ለማካሄድ ከመሀል አገር አዲስ አበባ ድረስ የተላኩ በተሽከርካሪ የታገዘ የአድማ ወረቀት የመበተንና በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃ በመቃወም አልያም ቡድኑ ጉልበቱ እንደፈረጠመ የፈለገውን ሕገ ወጥ ሥራ እየሠራ መንግሥትን እየተገዳደረ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሌሎች ተላላኪ ኃይሎች በርካታ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሁለቱም ድርጊቶች በሠላም ወዳዱ የጎንደር ሕዝብና በፀጥታ መዋቅራችን የጋራ ጥረት አልተሳኩም፡፡ የጎንደር ሕዝብ ልብ ሊል የሚገባው ጎንደር ቅስሟ እንዲሰበር በውስጥም በውጭም ያሉ ጠላቶቻችን ያለ የሌለ ኃይላቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡

የተከበራችሁ የከተማችን ሕዝቦች በቅርብም በሩቅም ያላችሁ ወገኖቻችን

በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ሕገ ወጥ ቡድን ከመሸገበት አካባቢ እንዲለቅቅና እንዲበተን ከተደረገ በኋላ በዋናነት ሁለት ጎላ ጎላ ያሉ የሕዝብ ስሜቶች በከተማችን ተፈጥረዋል፡፡

የመጀመሪያውና በርካታው የከተማችንም ሆኑ በዙሪያው ያሉ ዞኖችና ወረዳዎች ሕዝቦች በተወሰደው ርምጃ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ‘‘ወደኋላ እንዳትመለሱ ሕግ አስከብሩ፣ አጥፊን ጠይቁ፣ ከመንግሥት ጋር የሚገደደር ኃይል ይበተን፣ ሠላማችንና ደኅንነታችንን መልሱልን፣ የሕዝባችን አንድነት አጠናክሩ’’ የሚሉ የጎሉ ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሕገ ወጥ ቡድኑ እየፈፀመ ያለውን ድርጊት ትክክለኛ መረጃ ካለማግኘት በመነጨ መንግሥት የወሰደውን ሕግ የማስከበር ርምጃ ‘‘ፋኖን ለማጥፋት ነው’’ የሚል የተዛባ ትርክት አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ እየተሰማ ሲሆን ‘‘መንግሥት የተደከመ ስለሆነ ዋስትናችንና የቁርጥ ቀናችን ይህ ቡድን ነው’’ በሚል መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ርምጃውን ለማጣጣል ከተቻለም ለማደናቀፍ የሚጥሩ ጥቂት የውስጥና የውጭ ተላላኪ ኃይሎች ተስተውለዋል፡፡

አሁን በተጨባጭ ያለው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬውን እያረጋገጠ እየመጣ መሆኑ እየታወቀ እንደተባለው የአፈፃፀም ድክመት እንኳን ቢኖር በሕግና በሥርዓት የማይመራ ቡድን የፈለገውን እያደረገ ይቀጥል ከማለት የመንግሥትን ድክመት ፈልጎ ተጋግዞ ማረም በተገባ ነበር፡፡

መላው ሠላም ወዳዱ የክልላችንም ሆነ የጎንደር ከተማ ሕዝብ በተቃራኒው ደግሞ ጥቂቶቹ ለጎንደር ውድቀት ‘ሌት ከቀን’ የሚጥሩ ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ሀቅ ቢኖር በከተማው አስተዳደር እስካለ ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ታጥቆ ተደራጅቶ ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሳሪያ አንግቦና ካምኘ መሥርቶ መኖር አይቻልም፡፡ የክልላችን መንግሥትም ሆነ የከተማችን አስተዳደር የታጠቀን ሕገ ወጥ ቡድን አይታገስም፤ ሕግ ያስከብራል፡፡ የክልላችንም ሆነ የከተማችን የውስጥም ሆነ የውጭ የፀጥታ ችግር የሚፈታው በክልላችን እና በፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ብቻ እንጅ በሌላ በማንም ቡድን ሊሆን አይችልም፡፡

ስለሆነ የከተማችን ፀጥታ ችግር በባለቤትነት መፍታት ያለበት የከተማችን ሕዝብና በተለይም ወጣቱ ከከተማችን ከክልላችንና ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ሕዝባችን ሠላሙ የሚያረጋገጥለት ደግሞ የፀጥታ መዋቅራችን ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት እንጅ በሌላ በማንም ኃይል አይደለም፡፡

የእስካሁኑ ሂደታችንም በከተማችን ከሠላም ወዳዱ ሕዝባችን ጋር ተቀናጅቶ እየሠራው ያለው የፀጥታ መዋቅራችን፣ የከተማችን የፀጥታ ሁኔታ በተለይም ዋና ዋና ወንጀሎች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀንሱ አድርጓል፤ ቀጣይም በእልህና በወኔ ሠላም የማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

የተከበራችሁ የከተማችን ሕዝቦች በተለይም ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች

በቀጣይ የከተማ አስተዳዳራችን ከመላው የጎንደር ከተማ ሠላም ወዳድ ሕዝብ ጋር በመሆን የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

1. በከተማችን የተጀመረውን ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን የክልሉ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያ የጣሰ የያዘውን የጦር መሣሪያ አውርዶ በሕግ የሚጠየቅ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

• በማንኛውም ሁኔታ ሕግ በጣሰ መንገድ የሚካሄድ የጥይት ተኩስ የያዘውን የጦርር መሳሪያ አወርዶ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር እንዲጠየቅ ያደርጋል፡፡

• በከተማችን ሕገ ወጥ ሰልፍ፣ የተዳከመውን የከተማችን ኢኮኖሚ ጭራሽ ይበልጥ እንዲዳከም ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ ለማካሄድ የሚቀሰቅስ፣ የሚያነሳሳ ከዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቱ መቆጠብ ያለበት ሲሆን ተባባሪ የሆነ ሁሉም በሕግ ይጠየቃል፡፡

2. በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ነገር ግን አሁን የተበተነው ቡድን በሠላም እጁን ለመንግሥት እስከ መጋቢት 20/2012 እንዲሠጥ፤ ይህንን አልፈፅምም ካለ ቡድኑን የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ሲሆን ለዚህም ሕዝባችን ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

3. መላው የከተማችን ሕዝቦች በተለይም ወጣቶች አሁን የተፈጠረውን አንፃራዊ ሠላም እና ዕድል ወደ ዘላቂ ሠላምና ልማት እንዲቀየር በማድረግ ጎንደር የሠላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪስት፣እና የንግድ ከተማ እንድትሆንና ወደ ቀደመ ክብሯና ገናና ታሪኳ እንድትመለስ አብረን ሌት ከቀን እንድንሠራ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

4. የከተማችን፣ የክልላችንና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር የከተማችን ሕዝብ ሠላሙ ዘላቂ እንዲሆን እየከፈላችሁት ያለው መሠዋዕትነት ታሪክ የማይዘነጋው መሆኑን አወቃችሁ አስተማማኝ ሠላም ሠፍኖ መላው የከተማችን ሕዝብ በሙሉ ቀልቡ ወደ ልማት እስኪገባ ድረስ ሠላም የማስፈን፣ ሕግና ሥርዓት፣ የማስከበር ሕገ ወጥነትን የመከላከል፣ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ከሠላም ወዳዱ ሕዝባችን ጋር በመሆን የሕግ የበላይነትን እንድታረጋግጡ ጥሪያችን እናሳተላልፋለን፡፡

5. በከተማችን፣ በክልላችንም ሆነ በሀገራችን የምትገኙ ባለሀብቶች ሆናችሁ ዲያስፖራዎች ለከተማችን ልማት እያበረከታችሁ ያላችሁት አስተዋፅዖ እና ሁለንታዊ ድጋፍ ሁሌም እያደነቅን በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ገብታችሁ የከተማዋን ችግር በማወሳሰብ የተጠመዳችሁ ጥቂት የውጭና የውስጥ ኃይሎች ለጎንደር ሕዝብ ስትሉ ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

6. የከተማችን የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች በሙሉ በየተሠማራችሁበት መስክ ሕዝብ በፍፁም ታማኝነት፣ ከመድሎ ከሙስና በፀዳ መንገድ የአገልጋይነት መንፈስ እንድታገለግሉት የሕዝብ ጥያቄ እንድትመልሱ የአደራ መልእክታችን እናስተላልፈለን፡፡

7. ከዚህም ሌላ በከተማችን፣ በሀገራችንም ሆኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምትገኙ የዲያስፖራ አባላት የማኅበራዊ ሚዲያ እንቂዎች እና የኮሙዩኒኬሸን ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች፣ አልሚ ባለሀብቶች ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር በመሆን በቅርቡ በከተማችን ለልማት ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን እያበሰርናችሁ ለከተማችን የገፅታ ግንባታ እጅና ጓንት ሆነን እንድንሠራና ለጎንደር ትንሳኤ የበኩላችን አስተዋፅኦ እንድናበረክት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

8. በመጨረሻም መላው የከተማችን የሃይማኖት አባቶች እንደወትሯችሁ ከሃይማኖታዊ አስተምህሯችሁና ከእምነት ተልኳችሁ አንፃር በተቃኘ አግባብ ሠላምን ልማትን አንድነትን ፍቅርንና መተሳሰብን እንድትሰብኩ የአደራ መልእክታችን እናደርሳለን፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት

መጋቢት 14/2ዐ12ዓ.ም

ጎንደር

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top