ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም እና ነዋሪዎችን በማስገደድ ገንዘብ ማሰባሰብ መቀጠሉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ የ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ደርሶታል።
ኢዜማ የደረሰው የሰነድ ማስረጃ እንደሚያትተው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ሠራተኛና ማኅበራዊ ጽሕፈት ቤት ለነዋሪዎች በላከው ደብዳቤ ላይ የብልፅግና ፓርቲ እያከናወንኩት ላለሁት የልማት ተግባራት ነዋሪዎች የገንዘብ መዋጮ አድርጉ ሲል አዟል። ድጋፍ የሚደረገው የገንዘብ መጠንም ከ1000ሺህ ብር በላይ መሆን እንዳለበትና ገንዘቡንም እስከ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ገቢ መደረግ እንዳለበት በማሳሰቢያነት ተጠቅሷል።
በደብዳቤው ላይ ገንዘቡ ገቢ የሚደረግበት የፓርቲው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር የተጠቀሰ ሲሆን ገንዘቡ ገቢ ከተደረገ በኋላም የባንክ ደረሰኝ ለወረዳው ማኅበራዊ ጽሕፈት ቤት ገቢ እንዲያደርጉ ጽሕፈት ቤቱ አዟል።
ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ሠራተኛና ማኅበራዊ ጽሕፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ ላይ ለመረጃ የተጠቀሰው ስልክ ቁጥር ላይ በመደወል ደብዳቤው ከነሱ የተላከ መሆኑን ማረጋገጥም ተችሏል። ያነጋገርናቸው ግለሰብም ደብዳቤው የእነሱ መሆኑንና ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ለማድረግ በማንኛውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ ወደተጠቀሰው የሂሳብ ቁጥር ገንዘብ ማስገባት እንደሚቻል እና ገንዘቡን ያስገባንበትን ደረሰኝ ጽሕፈት ቤት በመምጣት ማስረከብ እንደሚገባን ገልፀውልናል።
ኢዜማ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት፣ የቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፋይዳ እና የተደቀኑ አደጋዎች በሚል ርእስ በመሪው በኩል ባስተላለፈው መልዕክት «ከምርጫው ጋር በተያያዘ ለገዢው ፓርቲ ማስመረጫ ገንዘብ ማሰባሰብ በሚል እየተሄደበት ያለው መንገድ የምርጫውን የመወዳደሪያ ሜዳ እጅጉን ሚዛናዊነት (Fairness) የጎደለው እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ከምርጫው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን የሙስና አካሄድ የሚያሳይ ነውና ካሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። በዚህ ሂደት የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነቶችን የሚያደበላልቁ እርምጃዎች ማየታችን እጅግ አሳሳቢ ነው።» የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚታወስ ነው።
ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2019 አንቀፅ 135 ንዑስ አንቀፅ 1 ሀ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ያለውን የሥልጣን ኃላፊነት እና የተለየ ዕድል ወይንም ተፅዕኖ የማሳደር ችሎታ ለፖለቲካ ፍላጎቱ ለመጠቀም መደለያ ማቅረብን፣ ቅጣትን ወይንም ማንኛውንም ሕገወጥ ተግባር መፈፀም እንደማይችል ይደነግጋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የደረሰውን የሰነድ ማስረጃ ከሌሎች ተመሳሳይ ማስረጃዎች ጋር በማድረግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያመለክታል።