የጋራ ራዕይና ግብ ለአማራ ሕዝብ ዘለቄታዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕርዳር ጉባኤ መካሄድ ጀመረ
“የጋራ ራዕይና ግብ ለአማራ ሕዝብ ዘለቄታዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ሐሳብ ጉባኤ አማራ በባሕር ዳር መካሄድ ጀምሯል፡፡
ከከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆዬው ጉባኤ በአማራ ሕዝብ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡
ጉባኤውን ያስተባበሩት የአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ፣ የአማራ ክልል መንግሥት፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የአማራ ማኅበራዊ ራዕይ (አማራ) ግንባር እና የማኅበረሰብ ተወካዮች ናቸው፡፡
በጉባኤው ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተጋበዙ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡
ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ለሀገር ሠላምና ዘላቂ ልማት ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
ጠንካራና የታፈረች ሀገር መመሥረት የሚቻለው በትንንሽ አጀንዳዎች ላይ ጊዜን በማጥፋት ሳይሆን ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ሲቻል አንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
‘ጉባኤ አማራ’ በባሕር ዳር መካሄድ ጀምሯል፤ ሌሎች ባዘጋጁት አጀንዳ ከመጠላለፍ በመውጣት በአንድነትና በአብሮነት በሀገራዊ ግንባታ ላይ መጓዝ እንደሚገባ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አቶ ደመቀ አሳስበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ መሪዎችም ለራስ ክብር ከመጨነቅ ወጥተው ለክልሉ ሕዝብ ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን አንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ አሳስበዋል፡፡
ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ለሀገር ሠላምና ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማትን እና ሠላምን ለማረጋገጥ እንዲቻል ፖለቲከኞች ራሳቸውን ሆነው መገኘት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
የማኅበረሰብ አንቂዎችም በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ትንተና ለማኅበረሰቡ በማቅረብ በሀገራዊ ግንባታው ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል፡፡ የሚዲያ አካላትም ሚዛናዊ፣ ተዓማኒነት ያለው፣ ዴሞክራሲን የሚያጎለብት ዘገባ ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
ምሁራንም ከዳር ተመልካችነት ወጥተው ምክንያታዊና ሳይንሳዊ ትንተና በማቅረብ ምሁራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እንደገለጹት ደግሞ ጉባኤው በክልሉ ያጋጠሙትን ችግሮች በማረም ወደ ቀደመው ሠላምና ፍቅር ለመጓዝ ያስችላል፡፡
ውይይቱም ያሉትን ልዩነቶች በማስወገድ ወደ አንድነት ሊወስድ የሚችል እንደሆነ ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የገለጹት፡፡
ጉባኤው “የጋራ ራዕይና ግብ ለአማራ ሕዝብ ዘለቄታዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል፡፡
ምንጭ – አብመድ