Connect with us

ዞዝ አምባ ውዬ መጣሁ

ዞዝ አምባ ውዬ መጣሁ

ባህልና ታሪክ

ዞዝ አምባ ውዬ መጣሁ

ዞዝ አምባ ውዬ መጣሁ፤  የልማት ያለኽ የሚለውን ቅርስ አለሁ የሚለው ማን ነው?
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኘውን ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ፍለጋ ወደ ምስራቅ በለሳ ተጉዟል፡፡ የልማት ያለህ የሚለው ቅርስ ሲል ታሪካዊው ስፍራ ሲደርስ የተሰማውን እንዲህ ያካፍለናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

እነኚህ ተራሮች ቋንቋ አላቸው፡፡ ከተራራ እያወራሁ መጣሁ፡፡ በለሳ ነኝ፡፡ ምስራቅ በለሳ ይለዋል መዋቅሩ፤ ለእኔ በለሳ በለሳ ነው፡፡ የጀግኖቹ ምድር፤ የምድሩን ጀብድ አንድ ቀን አወጋችኋለሁ፤ ዛሬ እድሜ ጠገቡን የሀገሬን ቅርስ ፍለጋ ነው የመጣሁት፤ ጎሃላ ደረስኩና ወደ ዞዝ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡

ዞዝ የቀበሌው ስም ነው፡፡ ግዙፉ ተራራም በዚሁ ስም ይጠራል፡፡ የአቡነ አብሳዲ አሻራ የታተመበት አምባ፡፡ ደረስን፡፡ ከሩቅ አየሁት፤ ለደህንነቱ ከተጋረደው የበረንዳ ጣሪያ ሾልኮ የሚመለከተኝ መለሰኝ፡፡ ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ፤ ዳገቷ ትንሽ ናት፡፡ ሊፍት የሌለው ሆቴል ያክል አትፈትንም፤ ስፍራው ድረስ መኪና ይገባል፡፡ ማዶ እብናት ነው፡፡ ታጋዮ ተፈራ የተዋጋበት የዋልዋ ተራራ ጉብ ብላለች፡፡ ዞዝ ድንቅ አምባዎች የከበቡት የውቅር አምባ ነው፡፡

ስደርስ ማመን አቃተኝ፡፡ መንገዱ ደስ አይልም፤ በደንብ አልተሰራም፡፡ ገደሉ ለመደልደል እንኳን በር ተፈልጎ ችግር መሆኑን ነግረውኛል፡፡ እዚህ ስድርስ ያየሁት ግን ተአምር ነው፡፡ ላስታ ያለሁ መሰለኝ፡፡ ግን በለሳ ነኝ፡፡

ዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ውቅር ነው፡፡ ምድሩና ጣሪያው ከዐለት ተጣብቋል፡፡ ሌላው አካሉ ንጥል ነው፡፡ ድንቅ ሆኖ የተሰራ፤ ብዙ ነገሩ ቤተ ጊዮርጊስን ይመስላል፡፡ ከመስቀለኛው ጣሪያው ውጪ፤ በርና መስኮቶቹ፣ ልቅም ብሎ መሰራቱ፤ የተጎሳቆሉ መነኮሳት አየሁ፡፡

ወርቅ የሆነውን ቅርስ እየጠበቁ አፈር መስለዋል፡፡ ይሄ ከላስታ የቅዱስ ላሊበላ ውቅሮች አስቀድሞ ቅዱሱና ንጉሡ ላሊበላ ያሰራው ውቅር ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ተደብቆ ኖሮ በአቡነ አብሳዲ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን ከተደበቀበት ወጣ፡፡

ምኑን ልንገራችሁ፤ ከሳምንት በኋላ በምስል ታዮታላችሁ፡፡ ግን አዘንኩ፤ እንዲህ ያለ ድንቅ ቅርስ ደንቀዝን አቋርጦ ጎንድን ተከትሎ በደጎማ እዚህ የሚደርስ ልዩ መስመር ያለ ቅርስ የሰው ያለህ ይላል፣ የልማት ያለህ ይላል፤ ከቤተልሔሙ የሚወጣው ጢስ ያጠቆረውን ውቅር መፍትሔው ምንድን ነው? ብዬ ብጠይቃቸው ቤተልሔሙን አውጥቶ ለመስራት አቅም አጣን አሉኝ፤
ስፍራውን ለማልማት፣ ቅርሱን ለመጠበቅ የት መሄድ እንዳለባቸው ግራ የገባቸው አባቶች ባለቤት የሆነ ሀገሬ ነው የሚል ዜጋ እስኪመጣ እየጠበቁ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቅርስ ይዞ እንዲህ ያለ መንደር መኖር ያስቆጫል፤ እንዲህ ያለ ሰው ውሎ ማደር ያንገበግባል፤ እንዲህ ልማት መራብ ያሳዝናል፤ ቅርብ ነው፤ ሊያውም ሀገራችሁ ውስጥ ሂዱና ዞዝ አምባን እዩት፤ ከመቆጨት ያለፈ ተአምር እንስራ፤

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top