Connect with us

ቆጮን በአጭር ቀናት ለምግብነት ማዋል የሚያስችል ምርምር ይፋ ሆነ

ቆጮን በአጭር ቀናት ለምግብነት ማዋል የሚያስችል ምርምር ይፋ ሆነ
Photo: Facebook

ጤና

ቆጮን በአጭር ቀናት ለምግብነት ማዋል የሚያስችል ምርምር ይፋ ሆነ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆጮን በዘመናዊ መንገድ ጥራቱን ጠብቆ አዘጋጅቶ ከ10 ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ለማዋል የሚያስችል የምርምር ውጤት ይፋ አደረገ።

ምርምሩ በባህላዊ መንገድ ቆጮ ሲዘጋጅ እስከ 45 በመቶ የሚደርሰውን ብክነት ሙሉ ለሙሉ ያስቀራል ተብሏል።

በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አዲሱ ፍቃዱ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከቤልጂየም መንግሥት ጋር በመተባበር ቆጮን በባህላዊ መንገድ ሲዘጋጅ የሚወስደውን ረዘም ያለ ጊዜ ለማሳጠርና ብክነትን ለመከላከል በተደረገው ምርምር ቆጮው ጥራቱን ጠበቆ ያለምንም ብክነት ከ10 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ለማዋል የሚያስችል ውጤት መገኘቱንና ወደ ህብረተሰቡ እየተስፋፋ ነው።

እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ፤ ቆጮ በባህላዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ለምግብነት የሚውለው ዕንሰቱ ተፍቆና ጉድጓድ ተቆፍሮ ከሁለት እስከ ስድስት ወር ቀብሮ በማቆየት ነው። በዚህን ጊዜ ከአፈር ጋር ንክኪ ስለሚኖረው ይጠቁራል እንዲሁም በተለያዩ ባክቴሪያዎች ስለሚጠቃ መጥፎ ጠረን ያመጣል። በዚህም ምግቡ ተፈጥሯዊ ጣሙን እንደሚያጣና ጥራቱም ዝቅተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በሌላ በኩልም ቆጮውን ለምግብነት ለማዋል ሲፈለግ የጠቆረውንና መጥፎ ጠረን ያመጣውን ክፍል ስለሚጣል ከአንድ ኩንታል በትንሹ ከ 25 እስከ 45 በመቶው ይባክናል። ምርቱንም አርሶ አደሮች ለገበያ ሲያወጡ ጥራቱ ስለሚቀንስ ዋጋው ይቀንሳል። ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የአውሮፓ አገሮችና ቻይና ጥቅል ጎመንን ለማብላላት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር ለቆጮ ማብላያና ማስቀመጫነት በማዋል በዘመናዊ መንገድ ቆጮን ለማምረት የተደረገው ምርምር ውጤታማ ለመሆን መቻሉን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ፤ በዘመናዊ መንገድ የተፈቀፈቀውን ቆጮ በእንስራ ውስጥ በማድረግ እርሾ ጨምሮ በሚብላለበት ወቅት፤ ከአፈር ጋር ንክኪ ስለማይኖረው አይጠቁርም፤ እንዲሁም ለተለያዩ ባክቴሪያዎች ተጋላጭ አይሆንም በዚህም መጥፎ ጠረን አይኖረውም። ቴክኖሎጂው ብክነትን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል። በባህላዊ መንገድ ቆጮን አዘጋጅቶ ለምግብነት ለማዋል ከሁለት እስከ ስድስት ወር ይወስድ የነበረውን ጊዜ ወደ 10 ቀናት ያሳጠረ ነው።

ዶክተር አዲሱ ባህላዊ የቆጮ መፋቂያና መጭመቂያ መሳሪያዎችን በዘመናዊ መሳሪያ ለመቀየር የተለያዩ ማሽኖችን ዲዛይን መደረጉንና እንደ ዳቦ እርሾ ሁሉ ለቆጮ ማብላያነት የሚውል ደረጃውን የጠበቀ እርሾ መገኝቱን ጠቁመው፤ ምርምሩን በማስፋት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ወደ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት መገኘቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች ቆጮን ለቤት ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለገበያ አውጥተው ገቢ አግኝተው ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ተክሉ እየተመናመነ መምጣቱና በአሁኑ ስዓት የዕንሰት ምርት እየቀነሰ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አዲሱ፤ ቴክኖሎጂው ወደ አርሶ አደሩ ሲሰፋ ምርትን ቶሎ ቶሎ በማምረት ከዕለት ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ለማሳደግ ያስችላል።

ዶክተር አዲሱ እየተመናመነ የመጣውን የእንሰት ተክል ዳግም እንዲያንሰራራና የቆጮ ምርት እንዲጨምር ያድርጋል። በዚህም ለሕፃናትና በተለይ ለሚያጠቡ እናቶች ተጨማሪ ምግቦችን ከቆጮ በማዘጋጀት አርሶ አደሩ በምግብ እራሱን እንዲችል ያደርጋል ብለዋል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 2/2012

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top