Connect with us

በኮንትሮባንድ ወደአገር ሊገባ የነበረ የጦር መሣሪያ ተያዘ

በኮንትሮባንድ ወደአገር ሊገባ የነበረ የጦር መሣሪያ ተያዘ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

በኮንትሮባንድ ወደአገር ሊገባ የነበረ የጦር መሣሪያ ተያዘ

አለም አቀፍ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ቡድን በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ያስገባው ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

መነሻውን ከቱርክ ሜርሲን ወደብ ያደረገው ህገወጥ የጦር መሳሪያው፤ በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ገብቶ በቁጥጥር ስር የዋለው፤ በወደቡ ለአምስት ወራት ያህል በድብቅ ተቀመጦ፤ በረቀቀ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከገበ በኋላ መሆኑን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ግምታቸው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ 501 እሽግ ካርቶኖች፤ ከ18 ሺህ በላይ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ጋር መያዛቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ ለሽፋን እንዲያገለግሉ ታስቦ የተዘጋጁና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በውስጣቸው የያዙ 229 እሽግ ካርቶኖችም ጭምር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ህገወጥ የጦር መሳሪያውን በተመለከተ የመረጃ ጥቆማ ካገኘበት ጊዜ አንስቶ፤ለረጅም ግዜ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ህገወጥ የጦር መሳሪያው በምን መልኩ፤ እንዴትና በማን ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችል በመለየት ልዩ የኦፕሬሽን ስራ ሲያካሂድ መቆየቱን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ይህ ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ቢሰራጭ ኖሮ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋና ስጋት ይደቅን እንደነበር የገለፀው መግለጫው፤የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር የማዋል ኦፕሬሽኑ በስኬት በመጠናቀቁ ምክንያት ሀገርና ህዝብን ከተደቀነበት ጥፋት የመታደግ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣት ተችሏል፡፡

አገሪቷንና ህዝቦቿን ወደ ትርምስ ለማስገባት የተወጠነውን ሴራ ለማክሸፍ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ ከኢትዮጵያ ውጪ በሌሎች ሀገራት የተዘረጉ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን መረብ በማሰስ ለመበጣጠስ የሚያስችሉ ኦፕሬሽኖችን በብቃት ለመወጣት መቻሉን መግለጫው ጠቁሟል ፡፡

በአገር ውስጥ በተካሄደው ኦፕሬሽንም ወደ አገሪቱ የገባውን የጦር መሳሪያ ተቀብለው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለማሰራጨት የተዘጋጁ 24 ተጠርጣሪዎችን የጦር መሣሪያውን ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ፤ምርምረው በሚመለከተው አካል መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል ፡፡

ብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ድንበር ተሸጋሪ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን እና የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር እንዲውል ከማድረጉም በተጨማሪ ከጅቡቲ፤ ከሱዳን፤ ከሊቢያ፤ ከቱርክ እና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡ እና ያልተያዙ አለምአቀፍ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የቁጥጥር ስራው መጠናከሩን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም 7 የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያላቸው የውጭ ተጠርጣሪዎች ሲኖሩ ከእንዚህ ውስጥም፤ 2 የሱዳን ዜግነት ያለቸው ተጠርጣሪዎች ከሱዳን የመረጃ ተቋም ጋር መረጃ በመለዋወጥ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ሌሎች በቁጥጥር ስር ያለውሉ ተጠርጣሪዎችን ከሊቢያ፤ ከጁቡቲ፤ ከሱዳን ፤ከቱርክና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሰር ለማዋል የትብብር ስራ መጀመሩንም አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በከፍተኛ ክትትል እና የተቀናጀ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር የዋለው የጦር መሳሪያ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በማባባስ እና ከፍተኛ እልቂት ለመፍጠር ሲባል የተዘጋጀ መሆኑን የገለፀው ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት መግለጫ፤ ይህን እኩይ ተልእኮ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ቀን ከሌሊት ክትትልና ቁርጥኝነት ማክሸፉ መቻሉን አመልክቷል፡፡

ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል በወሰዳቸው እርምጃዎች የጉምሩክ ኮሚሽን፤ የፌደራል፤ የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ ምሰጋና አቅርቧል፡፡ የህብረተሰቡም የተለመደ ትብብርና ድጋፍ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ከፍተኛ ሚና እንደነበርውም አክሎ ገልጿል፡፡

በቀጣይም ህብረሰተሰቡ እየረቀቀ እና አየተባባሰ የመጣውን አገርና ህዝብን ሰላም የሚያናጋውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወንጀል ለመካለካል በሚደረገው ጥረት ወስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡(ፋና)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top