Connect with us

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም – ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም – ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ

‹‹ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ ነው እንጂ የግዴታ አይደለም።›› ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለፁ።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ ሰሞነኛና ወቅታዊ አጀንዳ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልትጠቅም የምትችለውን ያህል ኢትዮጵያም ለአሜሪካ ልትጠቀም ትችላለች። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የወዳጅነትና የመፈቃቀድ እንጂ የግዴታ አይደለም።

‹‹ አሜሪካ የራሷን የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲሁም ነፃነቷን ትወዳለች፤ የዚያኑ ያህል ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ነፃነቷን የምትወድና ተከብራ የኖረችም አገር ጭምር መሆኗን አሜሪካ ማወቅ አለባት።›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በቅርቡ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደራደሩ በታዛቢነት የተሰየመችው አሜሪካ ባሳለፈችው ለግብጽ የወገነ ውሳኔ የአሜሪካ ታዋቂ ግለሰቦችና ይህን ሐሳብ የማይደግፉ ወገኖች ጭምር አሜሪካንን በመተቸት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰሩ፣ አሜሪካ በታዛቢነት ጀምራ ወደ አደራዳሪነት ብሎም ሰነድ በማዘጋጀት ወደ አስፈራሚነት የመምጣቷ አካሄድ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት ማጣቱ ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል። በጉዳዩ ዙሪያ በአሁኑ ወቅት ያለው የአሜሪካ አስተዳደር የተሳሳተ እንደሚመስላቸውም ገልፀዋል። የአሜሪካ የፖለቲካ ተቋማት የሚደግፉት አይነት አሠራር ጭምር አለመሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ለወደፊት ስህተቱ ተስተካክሎ በሁለቱ አገራት መካከል የተሻለ ግንኙነት ይፈጠራል ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ገለፃ፤ አሜሪካ በወሰደችው አቋም ምክንያት ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም የዚያን ያህል የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይጎዳዋል ተብሎ አይታሰብም። ይሁንና ጉዳት ሊኖረው ቢችል እንኳ ኢትዮጵያ ጥርሷን ነክሳ መቻል ይኖርባታል። ባስ የሚል ከሆነ ደግሞ የራሷን አማራጭ ትፈልጋለች እንጂ ለልጅ ልጆቿ የሚተርፍ ዕዳ ተሸክማ አትዘልቅም። ይህን ማንም ኢትዮጵያዊ አይፈቅድም።

‹‹አሜሪካ አልፋ ጫና ማሳደሩን የምትገፋበት ከሆነ ግን ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ጣልቃ ገብነት በፍፁም የማትቀበል አገር ናት፤ ይህም በዓለም ዘንድ የታወቀ ነው። ምክንያቱም አንድን ጉዳይ አገራት በስምምነትና በመነጋገር እንዲሁም በወዳጅነት መንፈስ የመፈፀምን መንገድ የሚያበላሽ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ የምትኖረው በአሜሪካ በጎ ፈቃድ ሳይሆን በራሷ ጥንካሬ ነው።›› ሲሉ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ህዝቡ የአገሪቱን ልማት፣ ዕድገትና ብልጽግና ወደፊት ለማስቀጠል ጠንክረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ በሩቅ ካሉ አገሮች ጋር በስምምነትና በወዳጅነት መንፈስ እንዲሁም በመተጋገዝና በመተባበር የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል።

ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በሦስቱ አገሮች መካከል ስምምነት ሳይፈረም በፊት በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊትና መሰል ሥራዎች ማከናወን እንደሌለባት መግለፁ ይታወቃል። ይህ መግለጫ በኢትዮጵያ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘም ይታወሳል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top