Connect with us

ምርጫ ቦርድ የቅንጅት መስራች አባላት ስም ዝርዝርን እንዲያጣራ ለፖሊስ ጥያቄ አቀረበ

ምርጫ ቦርድ የቅንጅት መስራች አባላት ስም ዝርዝርን እንዲያጣራ ለፖሊስ ጥያቄ አቀረበ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ምርጫ ቦርድ የቅንጅት መስራች አባላት ስም ዝርዝርን እንዲያጣራ ለፖሊስ ጥያቄ አቀረበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀድሞ አዋጅ ተመዝግበው የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ ላይ ተቀመጡትን መስፈርቶች እንዲያሟሉ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በአዲሱ አዋጅ በተደነገገው መሰረት 7,214 ( ሰባት ሺህ ሁለት መቶ አስራ አራት) ተጨማሪ መስራች የፓርቲ አባላትን አስፈርሞ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንዲያቀርብ ተገልጾለት ነበር፡፡

ፓርቲው ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ከ8 ክልሎች የተሰበሰበ የመስራች አባላት ፊርማ የያዘ ሰነድ ለቦርዱ አቀርቧል፡፡ በመሆኑም የቀረበው ሰነድ ላይ የሚከተሉትን ቦርዱ አስተውሏል፡፡

-ቦርዱ ከእያንዳንዱ ገጽ ላይ በተወሰደ እና ወካይ ሊሆን የሚችል ናሙና ባደረገው ማጣራት፣ ጥሪ ካደረገባላቸው 50 ፈራሚዎች መካከል፣ አንዱ ብቻ ፈርሞ ሲገኝ 49ኙ ግን በተለያየ ምክንያት ፊርማቸውን አለማኖራቸውን አረጋግጧል።( አብዛኛው የተሳሳተ ስልክ ነው፣ አልፈረምኩም የሚሉ ምላሾችና የማይሰራ መስመር ሆነው ተገኝተዋል)
-የፓርቲው ማመልከቻ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ቢፈርሙም፣ የተሰበሰበው ፊርማ ቃለ መሃላ ላይ የፈረመው ሌላ ግለሰብ መሆኑን፣ ሃላፊነቱም አለመገለጹን
-የአያት ስም ያላስመዘገቡ፣ ስለአባልነታቸው በፊርማቸው ያላረጋገጡ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ የምዝገባ ቀናቸው የማይታወቅ ፈራሚ ስሞችም በጉልህ ተገኝተዋል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው አዋጅ መሰረት በአባልነት ያልተመዘገበን ሰው የተመዘገበ በማስመሰል የሌለን ሰው እንዳለ ማስመሰል ሃሰተኛ ስምና ፊርማ ማዘጋጀት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ በአዋጁ መሰረት ቦርዱ ሊወስድ ከሚችላቸው ምዝገባን ከመከልከልና ከማገድ በተጨማሪ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ መሰረትም ሊጠየቅ እንደሚችል የህጉ ድንጋጌዎች ያዛሉ፡፡

ቦርዱ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በመነሳት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ( ቅንጅት) ያቀረባቸው የመስራች አባላት ፊርማ ስም ትክክለኛ ለመሆናቸው ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ ስለዚህም የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን ተመልክቶ ህጋዊ ማጣራት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው እለት የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም አስተላልፏል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top