የካቲት ታላቁ የታላቅነታችን ወር፤
ከጥንት እስከ ዛሬ ከአድዋ እስከ ካራ ማራ
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የየካቲት ወር የድል ታሪካችንን ከትናንት እስከ ዛሬ ብሎ በወፍ በረር ዳስሶታል፡፡ ከአድዋ እስከ ካራ ማራ ያለውን እንዲህ ተርኮታል፡፡ የካቲትን የታላቅነታችን ወር ይለዋል በተከታዩ ጽሑፉ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
የካቲት የብቻችን አይደለም፤ በአባቶቻችን ብርታት የአፍሪቃውያን ለመሆን የበቃ ወር ነው፡፡ በየካቲት ደግም ክፉም አልፈናል፡፡ የካቲት አድዋን ያተምንበት ነው፡፡ አድዋ የወደቅንበት ነው፤ ከአድዋ በኋላ መወረር የሚለውን ያበጠ ልብ ያስተነፈስንበት ነው፡፡ እንዲሁ የካቲት የዚያድ ባሬን ጦር ድል ያደርግነበት ነው፡፡ ከየካቲት በኋላ ሀገሬ ጠበበኝ ማለት እንጂ ኢትዮጵያን አጥብቦ ምድር መውሰድ እንደማይቻል ያሳየንበት ነው፡፡
ዛሬ የካራ ማራ ድል መታሰቢያ ቀን ነው፡፡ በአድዋ ጣዕም፣ በድሉ ትዝታ ውስጥ ሆኖ ሌላ ትውልድ ሌላ ድል ያስመዘገበበት የኩራት ቀን ነው፡፡ ለነጻነት የተከፈለ ዋጋ በየዘመኑ የሚታደስ መስዋዕትነት መሆኑን ያሳየንበት ወር ነው፡፡
የካቲት የድል ወር ነው፡፡ ከአድዋ አስቀድሞ የካቲት ሳይወጣ በመጨረሻው ቀን በ1868 ዓ.ም. ጉርዓ ላይ የግብጽን ጦር ለሀገሩ አንገቱን የሰጠው ዩሐንስ ደመሰሰው፡፡ ድግሞም ከአድዋ በኋላ የአባት አርበኞች ጦር በየካቲት 13ኛ ቀን በ1930 ዓ.ም. አጋምሳ ላይ ያለ ባንዲራ ያለ መሪ ተዋደቁ፡፡
በየካቲት ስለ ተወለዱልን ጀግኖች እልል ብለናል፡፡ በየካቲት በሞት ያጣናቸው ብዙ ናቸው፡፡ አድማስ ሰገድ የባሉት ዐፄ ሚናስ በ1953 የካቲት በገባ በአምስተኛው ቀን ሞቱ፤ በተመሳሳይ ሳልሳዊ ዳዊትም እንዲሁ የካቲት በተቆጠረ በአምስተኛው ቀን በ1708 ነበር የሞቱት፣ ራስ አሉላ አባነጋን ያጣነው የካቲት 9 ቀን 1896 ሲሆን ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱም እንዲሁ የካቲት በገባ በአራተኛው ቀን በ1910 ዓ.ም. አርፈዋል፡፡ ታላቁ የሀገር ሰሪ ቱርካና ባንዲራዋን ያውለበለቧት ራስና የኋላው ንጉሥ ወልደጊዮርጊስም እቴጌ በአረፉበት ዓመት በ24ኛው ቀን አረፉ፡፡
የካቲት የንግስና ወር ነው፡፡ ታላቁ ሰርጸድንግል በየካቲት ሰባተኛው ቀን በ1555 ነገሠ፡፡ የአንድነት ምልክቱ ዳግማዊ ቴዎድሮስም እንዲሁ የካቲት በሆነ በአምስተኛው ቀን በ1847 ነገሠ፡፡ እቴጌያችን ዘውዲቱም በየካቲት አራተኛ ቀን በ1909 ንግሥተ ነገሥታት ተባሉ፡፡
ዛሬ የየካቲት ውብ ታሪክ የሚናኝበት ልዩ ቀን ነው፡፡ ካራ ማራ እንደ አያቶቻችን አባቶቻችን የድል ጽዋ ለትውልድ ያስጎነጩበት ባንዲራችንን ከፍ አድርገው በምድሯ የሰቀሉበት ልዩ ቀን ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡