ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ለፍርድ ይቅረቡ!
ያሬድ ሀይለማርያም
በዛ በክፉ ዘመን የዛሬ ሦስት እና አራት አመት በፊት በህውሃት ደህንነቶች ታፍነው በማዕከላዊ እና በሌሎች እስር ቤቶች ታስረው የነበሩት ዜጎች፤ በርካታዎቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ሰቆቃ የተፈጸመባቸው መሆኑን አካላቸውን ጭምር እየገለጡ ለፍርድ ቤት ሲያሳዩ፣ በብልታቸው ላይ የውሃ ኮዳ ይንጠለጠል እንደነበር ሲናገሩ፣ ጥፍራቸው እየተነቀለና አካላቸው እየተቆራረጠ ሲሰቃዩ እንደነበር ሲያጋልጡ፣ ሕክምና እንዳያገኙ እንደሚከለከሉ በመግለጽ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ እኚህ ግለሰብ የሥርዓቱን ገበና ለመሸፈን በማሰብ ሚዲያዎችን እቢሯቸው ድረስ ጠርተው በየትኛውም እስር ቤት ማዕከላዊን ጨምሮ እስረኞች ላይ ግርፋት እንደማይፈጸም፣ ጨለማ ክፍልም እንደሌለ፣ እስረኞች ህክምና እንደማይከለከሉ በመግለጽ እስር ቤቱን ገነት አስመስለው የሃሰት መረጃ ለሕዝብ ሰጥተዋል።
ዛሬ የከሰሷቸውን አንዳንድ የህወሓት ባለሥልጣናት ገበናም በመሸፈን እና ለወንጀለኞች በመተባበር ትልቅ ጥፋት ፈጽመዋል። ይሁንና ለውጡ እሳቸው የአመራር አባል በሆኑበት ፓርቲ መዘወር ስለጀመረ ተጠያቂነቱ ይቅር እና እንደውም ተሹመው በተመሳሳይ ኃላፊነት ላይ እንዲቆዩ ተደረገ። ዛሬም እሳቸው በሚመሩት ተቋም ዜጎች በሃሰት በሽብርተኝነት ተከሰው እና ጨለማ ቤት ታስረው እንደሚማቅቁ ከእስር የተፈቱ ሰዎች እየነገሩን ነው። ለዚህም የኦነግ አመራር አባል የሆኑት ኮ/ል ገመቹ አያና በሚገርም ሁኔታ በዚህ ሳምንት ከLTV ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በራሳቸው ላይ የተፈጸመውን ግፍ ጭምር ጥሩ አድርገው ገልጸውታል።
‘ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም’ እንደሚባለው አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በቅርቡ ለውጡ ከተጀመረ በኋላ በተለይም የባህርዳሩን ግጭት ተከትሎ እነ ኤሊያስ ገብሩ፣ ክርስቲያን እና ሌሎች እስረኞች በጨለማ ቤት ውስጥ ታስረን እየተሰቃየን ነው የሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ እንደለመደባቸው ወደ አደባባይ ወጥተው በዚህ የለውጥ ዘመን ጨለማ ቤት የሚታሰር ሰው የለም ብለው ሽምጥጥ አድርገው ካዱ።
እነ ኤሊያስ ገብሩ ከእስር ከመውጣታቸው በፊት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከተሾሙ በኋላ እስር ቤቶቹን ጎብኝተው ሰዎች ጨለማ ክፍል መታሰራቸውን አረጋግጠው ለሕዝብ ገልጸዋል። ማሻሻያም እንዲደረግ ጠይቀው ነበር። ዛሬም የኦነግ አመራር አባል የሆኑት ኮ/ል ገመቹ አያና ከLTV ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማዕከላዊ ተዘጋ ቢባልም ሰዎች እሳቸውን ጨምሮ በጨለማ ክፍል ውስጥ ታስረው ሲማቅቁ ቆይተው በቅርቡ መለቀቃቸውን ገልጸዋል። ማዕከላዊን ዘግተን ሙዚየም አድርገነዋል እየተባለ በየሚዲያው እየተደሰኮረ ሰዎችን ለአንድ ወር ያህል ጨለማ ቤት ውስጥ አስሮ የማሰቃየት ሥራ የተፈጸመው በዚህ የለውጥ ዋዜማ ነው።
መንግሥት ከልቡ የእስረኞች አያያዝን ማሻሻል ከፈለገ፣ የፍትህ አካላት ነጻ እንዲሆኑ ከተፈለገ ተቋሙን፤ ቢያንስ በአመራር ደረጃ እንደ አቶ ብርሃኑ ካሉ የፓርቲ ተሿሚዎች እና ከዚህ ቀደም በመብት ጥሰት ቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ከነበራቸው ሰዎች ማጽዳት የግድ ይላል። ያ ብቻ ሳይሆን አቶ ብርሃኑ በሕግም ሊጠየቁ ይገባል።
ፍትህ ለሥቃይ ሰለባዎች!
ፍትህ ለፍትህ ተቋማት!
(የአዘጋጁ ማሽታወሻ፡- ይህጹሑፍ የጸሐፊውን እጂ ድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም፡፡ ጹሑፉ ቀደም ሲል የቀረበ ሲሆን የአቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነት ወደ አምባሳደርነት የሹመት ዝውውር መደረግን ተከትሎ በድጋሚ የቀረበ ነው፡፡)