አባቶቻችንን ብንክዳቸው እንኳን እነሱ አፍሪካውያንን በነጻነት ወልደዋል፤ ጥቁር ሁሉ አባቴ የሚልዎት ንጉሠ ነገሥቴ ምኒልክ፤
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የአድዋን በዓል ምክንያት በማድረግ የአድዋ ማስታወሻዎችን ሊያጋራን ነው፡፡ አባቶቻችን ያደረጉት ድል ለምናምን የንጉሠ ነገሥቱን ታላቅነት አንክድም ይለናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
እቀናለሁ፤ በመንፈሳቸው እቀናለሁ፤ አንኮበር ባልተገደበ፣ አንጎለላ ባልታጠረ አፍሪቃዊ መንፈሳቸው እኮራለሁ፡፡ የድልላቸው ምስጢር አጥር አልባው እሳቤያቸው ነው፡፡ እርሳቸው ከጮማና ጠጅ አምሮት ያለፈ የመሰልጠን ረሃብ የጎዳቸው ምልክት ናቸው፤ እርሳቸው ገዢ ነኝ ብሎ ከመኮፈስ በተሻገረ በቀለም መገዛት የለም የሚል ክብርን ያሳዩ መሪ ናቸው፤ አድዋን ያለ ዳግማዊ ምኒልክ አላስበውም፡፡
አድዋ ዝም ብሎ ጦርነት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ድልም አይደለም፡፡ የትውልድ ቅርስ ነው፡፡ ዘለዓለም ተቆፍሮ የሚወጣ ነዳጅ፣ ዘለዓለም ተዝቆ የሚጌጥበት ወርቅ፣ ዘለዓለም ተነገሮ የሚያጠግብ እውነት፡፡
ከእኔም ትውልድ የሚኮራበት እልፍ ነው፡፡ እርግጥ ነው እልፍ ክብር ለድላቸው፣ ለንጉሠ ነገሥቱና ለአባቶቻችን ሲያንሳቸው ነው፡፡ ያ የእምዬነታቸው ልብ ከጋሞ ደጋ ምድር ጀግናን አንደርድሮ አድዋ ለነጻነት አዋድቋል፤ ከጋርዱላ ምድር አብርሮ አምጥቶ ስሜን ጫፍ የድል ጽዋን አስነስቷል፡፡ ከጉባ ሀገሬን ያስባለ፣ ከዳሞት አናት ስለ ኢትዮጵያ ያከነፈ፣ ከውርጪ ደጋ ስለ ሀገር ክብር ያስመጣ፣ ከምስራቅ እልፍ ሆኖ ያስገሰገሰ፣ ከዴዴሳ ማዶ ቁጥር አልባ ዘራፍ ያስባለ የአንድነታችን ድል የአድዋ ምልክት ናቸው፤
አድዋን መካድ አይቻልም፤ ከአድዋ ክብር ድርሻን አለመውሰድ ግን መብት ነው፡፡ እኛ ግን አባቶቻችን ከግንደ በረት ጋልበው፣ ከጉና ተራራ ወርደው፣ ራስ ደጀንን አቋርጠው፣ ካራ ማራን ሰንጥቀው፣ ጉጌን አልፈው፣ ዳቲን ተሻግረው፣ ዳንጉርን ገስግሰው፣ ጮቄን ተደንደርድረው፣ አምባላጌን የድል ጽዋ ጠጥተው ሞትን እንደ ክብር በማየት ያስከበሩንን እናከብራለን፡፡
እኛ በአባቶቻችን ክብር ባንኮራ የሚዋረድ አባት የለንም፤ ክብር በስራ ነው፡፡ ይልቁንስ ንጉሠ ነገሥታችን ይልቁንስ ታላላቆቻችን ይልቁንስ ፈጣሪ ብቻ ስምና አድራሻቸውን የሚያውቃቸውን ዜጎቻችን ባናከብር ምን ሊቀርባቸው፤ እነሱን ብንክድ እነሱ አንዳች አይጎድልባቸውም፤ እነሱ አፍሪካውያንን በነጻነት ወልደዋል፡፡ እነሱ መከበር የሚሻ ውርደት የሚጸየፍ የነጻነትን ዋጋ የሚያውቅ ዘር በመላው ዓለም ተክተዋል፡፡
ጥቁር ሁሉ አባቴ የሚልዎት ንጉሠ ነገሥቴ ምኒልክ የድል ምልክቴ ነዎትና አድዋን እዘክር ዘንድ ስምዎን ከፍ አድርጌ እጀምራለሁ፤ ደግሞም የአባቶቻችን ገድል እንዲህ እቀጥለዋለሁ፡፡