“በተሠራ ማግስት የሚፈርስ መንገድ የለንም”- ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ
“መንገዱ ሰኞ አልቆ ማክሰኞ ጥገና የሚያስፈልገው ከሆነ ኪሳራ ነው”ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ
‹‹መንገዶቹ ሰኞ ተሠርተው ማክሰኞ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ኪሳራ ነው›› ሲሉ የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ‹‹በተሠራ ማግስት የሚፈርስ መንገድ የለንም›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከተለያዩ የሥራ ተቋራጮች ጋር ሰሞኑን የስምምነት ውል በተፈራረመበት ወቅት የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እንደተናገሩት፤ የሚሠሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሰኞ ተጠናቅቀው ማክሰኞ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ኪሳራ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሥራ ጥራት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ማስቀመጥ አለባቸው።
በአንዳንድ ሥፍራዎች የፕሮጀክቱ ሥራ ሳያልቅ አስቀድሞ ለብልሽት የሚዳረግ መንገድ ይታያል ያሉት አቡነ አትናቴዎስ፤ ይህ ዓይነቱ ሥራ ከትርፉ ኪሳራው ስለሚያመዝን ግንባታውን የሚያከናውነው አካል በጥራት በመሥራት ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ማስቀመጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ብጹእነታቸው የአንድ አገር ብልጽግና መለኪያ የመሰረተ ልማቶች መሟላት መሆናቸውን ጠቁመው፤ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ የሥራ ተቋራጮች የሚያስቀምጡት ታሪክ መሆኑን አውቀው ሙያዊ ስነምግባርን ተላብሰው በጥራት ሠርተው እንዲያጠናቅቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
“በተሠራ ማግስት የሚፈርስ መንገድ የለንም” ያሉት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፤ በጅምላ ሁሉንም መንገዶች ችግር አለባቸው ብሎ መናገር ተገቢ እንዳልሆነ፣ ለ20 ዓመታት ጥገና ሳይደረግላቸው ያገለገሉ መንገዶች መኖራቸውን፣ ተቋሙ ብዙ ፕሮጀክቶችን ስለሚያስተዳድር አልፎ አልፎ ጉድለት ሊታይ እንደሚችልና ፕሮጀክቶች ጥራት እንዲኖራቸው ተጋግዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ በጥራት እንዲሠሩ ከተፈለገ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ዳይሬክተሩ አሳስበው፤ ባለስልጣኑ መንገዶች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሰፊው እየሠራ በመሆኑ በቀጣይ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የህዝብን አመኔታና ድጋፍ ከሚሸረሽሩ ጉዳዮች አንዱ የፕሮጀክቶች የጥራት መጓደል መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራትም ላይ መሥራት ስለሚያስፈልግ፤ በዘርፉ የተሰማራ ሁሉም ሰው በተለይ ጥራት ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡት አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች የቆሼ – ሚጦ – ወራቤ፣ ጋምቤላ – አቦቦ – ጎግ – ዲማ፣ የግሸን – መገንጠያና የጎንጂ – ቆለላ መሆናቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2012