Connect with us

የመንግሥት ሠራተኞች ውሎ አበል ለአካባቢዎች በተተመነ ምጣኔ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመርያ ወጣ

የመንግሥት ሠራተኞች ውሎ አበል ለአካባቢዎች በተተመነ ምጣኔ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመርያ ወጣ
Photo: Facebook

ኢኮኖሚ

የመንግሥት ሠራተኞች ውሎ አበል ለአካባቢዎች በተተመነ ምጣኔ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመርያ ወጣ

የመንግሥት ሠራተኞች የቀን የውሎ አበል የደመወዝ ደረጃን መሠረት አድርጎ ለመስክ ሥራ መዳረሻ አካባቢዎች በተተመነ የክፍያ ሰንጠረዥ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመርያ ወጣ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ያወጣው መመርያ የመንግሥት ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራ ቦታ ክልል ውጪ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ የሚከፈላቸው የቀን ውሎ አበል፣ መመርያው ለመስክ ሥራ መዳረሻ አካባቢዎች ባስቀመጠው የተመን ሰንጠረዥና የሠራተኞች የደመወዝ ደረጃ መሠረት እንዲከፈል ይደነግጋል።

‹‹የቀን ውሎ አበል›› ማለት አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በአገር ውስጥ ከመደበኛ የሥራ ቦታ ውጪ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ለሥራ ጉዳይ ሄዶ በዕለቱ ለመመለስ ሳይችል ሲቀር፣ ለአንድ ቀን ለሚያስፈልገው የምግብና የመኝታ ወጪ የሚከፈል እንደሆነ የሚደነግገው መመርያው ከክልል እስከ ከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የሚከፈለውን የቀን አበል የሚወስን ሰንጠረዥም አባሪ አድርጓል።

ለአብነት ለመቀሌ ከተማ የተተመነው ዝቅተኛው የቀን አበል 348 ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 468 ብር ነው። ይህም ማለት የሠራተኛው ወርኃዊ ደመወዝ ከ1,100 ብር እስከ 3,933 ብር ከሆነ ለመቀሌ ከተማ የተተመነውን ዝቅተኛ የቀን አበል የሚያዝ ሲሆን፣ ወርኃዊ ደመወዙ ከ9,056 ብር በላይ የሆነ ሠራተኛ ደግሞ ከፍተኛውን የቀን አበል ማለትም 468 ብር እንደሚያገኝ በመመርያው ተደንግጓል።

ለአዲስ አበባ ከተማ የተተመነው የቀን አበል ከሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ለመስክ ሥራ የተመደበ የመንግሥት ሠራተኛ ከላይ በተገለጸው ወርኃዊ የደመወዝ መጠን መሠረት የሚያገኘው ዝቅተኛ የቀን አበል 468 ብር ሲሆን፣ መካከለኛው 549 ብር ነው፡፡ ወርኃዊ ደመወዛቸው ከ9,056 ብር በላይ የሆኑት ደግሞ 724 ብር በቀን እንዲያገኙ ወስኗል። ከክልል ከተሞች ዝቅተኛ የቀን አበል የተተመነው ለጅግጅጋ ከተማ ሲሆን፣ ከላይ በተገለጸው ወርኃዊ የደመወዝ ደረጃ መሠረት ለጅግጅጋ የተተመነው መነሻ የቀን አበል 314 ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ 404 ብር ነው።

በየክልሉ ሥር ለሚገኙ የዞን ዋና ከተሞች የቀን ውሎ አበል መጠንም በመመርያው ተተምኖ የቀረበ ሲሆን፣ ከላይ በተገለጸው የደመወዝ ምጣኔ መሠረት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የዞን ከተሞች የሚከፈለው ዝቅተኛ ወይም መነሻና ከፍተኛ የቀን አበል እንደ ቅደም ተከተላቸው 279 ብርና 417 ብር እንደሚሆን ተተምኗል። በተመሳሳይ በአማራ ክልል ለሚገኙ የዞን ከተሞች የተተመነው መነሻና ከፍተኛ የቀን አበል እንደ ቅደም ተከተላቸው 277 ብርና 409 ብር እንደሆነ በተመን ሰንጠረዡ ተገልጿል።

በመንግሥት ሠራተኞች የቀን ውሎ አበል ተመንና አከፋፈል ሥርዓት ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 07 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔና ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የወጣው መመርያ፣ ከመንግሥት ተሿሚዎች በስተቀር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ አስተዳደር እርከን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚ እንደሚሆን ደንግጓል።

በተጨማሪም በዜግነት ኢትዮጵያዊ በሆኑ ቋሚ፣ ጊዜያዊ ወይም በኮንትራት ተቀጥረው በሚያገለግሉ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ደንግጓል። ከቀን ውሎ አበል በተጨማሪ ‹‹የውሎ ገባ አበል›› እና ‹‹የአየር ፀባይ አበል›› የክፍያ ተመንና የአከፋፈል ሥርዓትንም መመርያው ይደነግጋል። አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ከመደበኛ የሥራ ቦታ ውጪ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ ሄዶ ዕለቱን የሚመለስ ከሆነ ለምግብ ለሚያወጣው ወጪ የውሎ ገባ አበል እንደሚከፈለውና ይኼውም ለክልል ከተሞች፣ ለከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም ለዞኖችና ለወረዳዎች ከተተመነው የቀን ውሎ አበል ተመን ውስጥ አሥር በመቶ ለቁርስ፣ 25 በመቶ ለምሳ፣ እንዲሁም 25 በመቶ ለእራት እንደሚከፈል ይደነግጋል።

አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ለመስክ ሥራ የአየር ፀባዩ አስቸጋሪ ወደሆነበት ቦታ ሲንቀሳቀስ የአየር ፀባይ አበል እንደሚከፈለው፣ ይኸውም በአንደኛ ደረጃ አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ባላቸው አካባቢዎች የተመደበ ሠራተኛ በአካባቢው ለቀን ውሎ አበል የተተመነውን ክፍያ 40 በመቶ በተጨማሪነት እንደሚከፈለው ይደነግጋል። የመንግሥት ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀምና ይህንንም ለመቆጣጠር የተለያዩ ድንጋጌዎችን መመርያው አካቷል። ከእነዚህም መካከል ተቋማት ሁሉም ክልሎች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችና የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለመስክ ሥራ የሚያሰማሯቸውን ሠራተኞች ብዛት የተወሰኑ እንዲሆን ያስቀመጠው ድንጋጌ አንዱ ነው።

በዚህ ድንጋጌ መሠረት ተቋማት በዓመት ከአጠቃላይ ሠራተኞቻቸው ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚመድቡት ሁለት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንድ በመቶ፣ በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሦስት በመቶ፣ በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች 15 በመቶና በሌሎች ክልሎች ከ15 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ወስኗል። ከዚህ በፊት ሲሠራበት የነበረው የቀን ውሎ አበል ተመን ከወቅቱ የገበያ ዋጋ ጋር የተመጣጠነና ለአከፋፈል ምቹ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ የነበረው የቀን ውሎ አበል ተመን ከወቅቱ የገበያ ዋጋና እያደገ ከሄደው የምግብና የመኝታ ዋጋ ጋር ባለመመጣጠኑ፣ በሠራተኞችና በመንግሥት ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ይህ መመርያ እንዲወጣ መወሰኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገልጿል።(ዮሐንስ አንበርብር – ሪፖርተር)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top