Connect with us

ቅዱስ ሲኖዶስ: ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት በተጠመዱ የብዙኀን መገናኛዎች እና ፓርቲዎች ጉዳይ እየተወያየ ነው

ቅዱስ ሲኖዶስ: ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት በተጠመዱ የብዙኀን መገናኛዎች እና ፓርቲዎች ጉዳይ እየተወያየ ነው
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ቅዱስ ሲኖዶስ: ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት በተጠመዱ የብዙኀን መገናኛዎች እና ፓርቲዎች ጉዳይ እየተወያየ ነው

ቅዱስ ሲኖዶስ: ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት በተጠመዱ የብዙኀን መገናኛዎች እና ፓርቲዎች ጉዳይ እየተወያየ ነው

• በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ አፈጻጸም ገመገመ፤
• “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት” በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው፣ በሕግ እንዲጠየቅ ቢወስንም፣ አፈጻጸሙን በዕርቅ ስም ያሰናከሉ አባቶችንና አካላትን በድክመት ገሠጸ፤
• ሕገ ወጥ እንቅስቃሴውን ከሚደግፉ አባቶች ውስጥ፣ “ብፁዕ ወቅዱስ” እየተባሉ በጸሎት መጠራት የጀመሩ እንዳሉ በማስረጃ ቀርቧል፤
• “ሊፈጸም በማይችል የዕርቅ ሙከራ አዘናግታችኋል፤ የሰጣችኹትም የመምሪያ ዋና ሓላፊነት ሹመት አግባብ አይደለም፤”/ቅዱስ ሲኖዶስ/
***

በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች፣ ሰኞ፣ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ የምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ከቀትር በኋላ ውሎው፣ ቤተ ክርስቲያንን በማጠልሸት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችንና ፕሮግራሞችን በሚያሰራጩ የብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ተወያይቷል፡፡

ኦኤምኤን፣ ኦቢኤን እና ኤልቴቪ በተባሉ ሚዲያዎች፣ በሐሰት ትርክት እና መረጃ ላይ ተመሥርተው የተሰራጩ ፕሮግራሞች ይዘት፣ በስላይድ እና በጽሑፍ ቀርበው ለምልአተ ጉባኤው ገለጻ ተደርጓል፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አራት አህጉረ ስብከትም፣ ከዚኹ ጋራ በተያያዘ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለምልአተ ጉባኤው አስረድተዋል፡፡

“ውሳኔ ላይ አልደረስንም፤ኾኖም፣ ሰፊ ውይይት ነው ያደረግነው፤” ያሉ የስብሰባው ተሳታፊ ብፁዕ አባት፣ ነገም በሚቀጥለው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጠንካራ የጋራ አቋም እንደሚወስድበት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው፣ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቋቁማለኹ፤” ባዮቹ እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ደንብ በመጣስ ማንነቷን ለማጥፋት እና አንድነቷን ለመናድ በሚያደርጉት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴያቸው፣ በሕግ እንዲጠየቁ፣ በጥቅምቱ መደበኛ ስብሰባው አሳልፎት የነበረውን ውሳኔ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ከማስፈጸም ይልቅ፣ ችግሩን በ“ዕርቅ እንፍታው” በማለት ግፊት ያደረጉ ብፁዓን አባቶች እንደነበሩና አንድ ብፁዕ አባትም ራሳቸውን ገልጸውና ስሕተታቸውን ለምልአተ ጉባኤው አምነው እንደተናገሩ በመረጃው ተገልጿል፡፡

ይህም፣ የውሳኔውን አፈጻጸም ከማዘግየቱም ባሻገር፣ የሕገ ወጡ እንቅስቃሴ አውራ የኾነው ቀሲስ በላይ መኰንን፣ በእነዚኹ አባቶች ግፊት፣ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተመልሶ፣ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊነት እንዲመደብ ተደርጎ እንደነበር ታውቋል፡፡

አጠቃላይ አካሔዱ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን እንደሚጋፋ ምልአተ ጉባኤው ጠቅሶ፣ ችግሩን በሌላ መልክ ማየት ካስፈለገ፣ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ይገባ እንደነበር ገልጿል፡፡ የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ ማስፈጸም ያለባቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ አካላት የኾኑት ጽ/ቤቱ እና ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በተወሰኑ አባቶች ግፊት የውሳኔውን አፈጻጸም ከማዘግየት አልፎ ግለሰቡን በሓላፊነት የመደቡበትን ውሳኔ ተችቷል፡፡

ቀሲስ በላይ መኰንን፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ በሕግ እንዲጠየቅ ቀደም ሲል አሳልፎት የነበረው ውሳኔ፣ ግለሰቡ ይቅርታ ለመጠየቅ እምቢተኛ በመኾኑ የተወሰነ እንደነበር ምልአተ ጉባኤው አውስቷል፡፡

“በዕርቅ ለመፍታት ያደረጋችኹት ሙከራ ቢፈጸም ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ተፈጻሚነት በሌለው ዕርቅ፣ የጥፋት እንቅስቃሴው እንዲቀጥልና የምልአተ ጉባኤው ውሳኔ እንዳይፈጸም አዘናግታችኋል፤” በማለት በቋሚ ሲኖዶሱ ላይ ጫና በመፍጠር የተሳተፉ አባቶችን ገሥጿል፡፡

በነገው ውሎው፣ ሕገ ወጡን እንቅስቃሴ በኅቡእ የሚደግፉ አባቶችን ጨምሮ(ብፁዕ ወቅዱስ ተብለው መጠራት የጀመሩም እንዳሉበት በስላይድ በቀረበው ማስረጃ ተመልክቷል)፣ የቀደመ ውሳኔውን የሚያጠናክር የጋራ አቋም እና የእርምት ርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል፡፡(ሐራ ተዋህዶ)

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top