ዛሬም ከዱባይ መልስ ለልጆቹ ቡትቶ ሳይሆን የሰው ልጆች ህይወት ይዞ የመጣው ጠቅላይ፤
(ከስናፍቅሽ አዲስ)
በሚሆነውማ እናመስግነው እንጂ፡፡ ትናንት ተማሪ ታግቷል ስንል እኮ ወቅሰነው ነበር፤ የሰው ህይወት ችላ አለ ብለን መንግስት በሞተውም በወደቀውም ኮንነንው ነበር፡፡ እንዲህ ሰው ሲታደግ እንዲህ በርታልን እንበለው፡፡
በእነኚህ የዱባይ ነዋሪ ዜጎቻችን ቦታ ራሳችንን እንክተት፣ በሰው ሀገር የሰው ሀገር ህግ የሚፈልገውን ሰነድ ሳናሟላ የምንኖረውን የሰቀቀን ኑሮ እናስበው፡፡ ከዛሬ ነገ እስር ብቻ ተስፋችን ሆኖ ተስፋ ቆርጠን እዚህ መቼ ትመጣለህ ለሚል ቤተሰብ ዛሬ ነገ እያልን አስሩን አመት በዓል ዘርዝረን አንዱንም ሳንመጣ፣ እንዴት ያለ የሰቀቀን ኑሮ ነው፡፡ እንዴት ያለ የመከራ ሕይወት ነው፡፡ ጠቅላዩ እንዲህ ያለውን አበሳ አስወገደው፡፡ እንዲህ ላለችዋ ጭቁን ነፍስ ከፈጣሪ የተላከ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያውያን ነጻ ወጡ፡፡
የሚሰቃየውን እየቆጠርን መንግስት አልባ ነን ስንል ኖረናል፡፡ የሚሰቃየው ከስቃዩ ሲፈታ፣ የሚሰቃየው ሀገሩ ሲገባ ግን ምሬት ማጣታችን ያከሰረን ይመስል ምላሻችን ቧልት ይሆናል፡፡
እስቲ በእነኚህ ተስፋ የቆረጡ ዜጎቻችን ቤተሰቦች ራሳችንን ቀይረን እናስብ፤ የሌላው ልጅ ይመጣል፤ የእኛ ልጅ ግን አይመጣም፡፡
የሌላው ልጅ እንደ አሻው ይደውላል፤ የእኛ ግን ከፖሊስ ጋር አይጥና ድመት ነው፡፡ የሌላው ልጅ የቤተሰቡን ኑሮ ይቀይራል የእኛው ግን ሩጦ ለማደር እንዳይችል ህግ የሚጠይቀውን አላሟላም፡፡ ወይ ትተህው ና እንለዋለን፤ እሺ ይላል አይመጣም፡፡ ጠቅላዩ እንዲህ ዓይነቱን ነው ይዞ የመጣው፡፡
ብዙ ሹመኛ ዱባይ ሲደርስ ስለ ልጆቹ ቡትቶ ያስብ እንደሁ እንጂ የታሰረ ዜጋ የተዋረደች ሀገር ምን ይሻላታል ብሎ አይጠይቅም፡፡
ሌላው ቢቀር እንዲህ ያሉ ዜጎችን ሰብስቦ አይዟችሁ አይልም፡፡ ሌላው ቢቀር መጥቶ በዚያ ሀገር መከራቸውን ስለሚበሉ ዜጎቻችን አይነግረንም፡፡
ጠቅላያችንም ልጆች ነበራቸው፡፡ ጊዜና ጉልበታቸውን ለልጆቻቸው ቁሳቁስ መግዣ ማዋል ይችሉ ነበር፡፡ ለልጆቼ ብትቶ ይዤ አልገባም ብሎ የሰው ልጅ በስስት የሚጠብቃቸውን ልጆቹን ይዞ መግባት የተባረከ ስራ ነው፡፡
ከሰው አበባ በለጠበት ብለነው ነበር፡፡ ሊቀጠፍ የተቆረጠ አበባን ይዞ ተመለሰ፡፡ እነኚህ ወጣቶች የኢትዮጵያ አበቦች ናቸው፡፡
ከመጠውለግ ታደጋቸው፤ ከመድረቅ ታደጋቸው፡፡ እንዲህ ያለ የሀገርን አበባ ማስመለስ ክብር የሚቸረው ተግባር ነው፡፡ እናም በሚያስመሰግነው ማመስገንን ካልለመድን መሪዎች ልክና ስህተትን ሳያውቁት ይኖራሉ፡፡