Connect with us

“ባለፉት ሁለት ዓመታት…አገራችን ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች”

"ባለፉት ሁለት ዓመታት...አገራችን ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች"

ፓለቲካ

“ባለፉት ሁለት ዓመታት…አገራችን ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች”

“ባለፉት ሁለት ዓመታት…አገራችን ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች”

የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል የጀመረበት የየካቲት 11 ቀን 45ኛ ዓመት በአል ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ
~~~
በዚች አገር የነበረውን ጭቆና፣ ተፅእኖና ቁጥር ስፈር የሌለው ግፍ ”እምቢ አንቀበልም፣ በፍፁም ኣንገዛም፣ እምቢ ለባርነት!” በማለት የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት እየተመራ የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 45ኛ ዓመት እያከበርን እንገኛለን። የካቲት 11 የትግራይን ህዝብ ፅናትና ድል ወደኋላ መለስ ብለን የምናስታውስበት፣ የዛሬንና የነገ ጉዟችን ከፍተኛ ወኔና ፅናት ተላብሰን በከፍተኛ የትግል መንፈስ ወደፊት የምንገሰግስበት ዕለት ናት። የትግራይ ህዝብ ጠብመንጃ አንስቶ ትግል ሲጀምር በጦርነት ወቅት የሚያጋጥመውን ሁለገብ ኪሳራ መገመት አቅቶት ሳይሆን ያነገበውን ቅዱስ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ተገዶ የገባበት ብቸኛ ኣማራጭ ስለነበረ ነው። የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ያካሄደው በኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረውን የኣገዛዝ ቀንበር በመደምሰስ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ስርኣት ለመትከልና ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተከባብረው በእኩልነትና በወንድማማችነት የሚኖሩበት፣ በራሳቸው ጉዳይ ላይ ራሳቸው የሚወስኑበት አገር በመፍጠር የጨፍላቂዎች ህልም ለዘለዓለም የሚቀበርበት ስርኣት በመፍጠር ከድህነትና ድንቁርና በመላቀቅ በሰላም፣ በልማት ዲሞክራሲ ጎዳና ለመገስገስ የሚያስችል መንገድ ለመጥረግ ሲል ነው።

የትግራይ ህዝብ ይህንን ከባድና የተወሳሰበ ትግል ተሸክሞ፣ ለአፍታ እንኳ አጋዥ ሳይጠይቅና ሳይለግም አኩሪ ታሪክ በመስራት ለማመን የሚያደግት ከባድ መስዋእትነት ከፍሎ፣ ፍፁም ፀረ-ዲሞክራሲ፣ ግፈኛና የድህነትና ድንቁርና ዘበኛ የነበረውን ፋሽስታዊ የደርግ ኢሰፓ ስርኣት በመደምሰስ በዚች አገር አዲስ ምዕራፍ እንዲፈጠር አድርጓል። የደርግ ስርኣት ከተደመሰሰ በኋላም አገሪቱ ደርሳበት ከነበረው የመበታተን ጫፍ በማዳን፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያሳተፈ ህገ-መንግስታዊ ስርኣት እንዲመሰረት ተኪ የሌለው ሚና ተጫውቷል። ህገ መንግስቱ ከፀደቀ በኋላም በዚህች አገር ለአለም ተምሳሌት የሚሆን ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርኣት እንዲገነባና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች አዲስ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን አስችሏል።

ለዘመናት በማንነታቸው ምክንያት ይፈሩና ይሸማቀቁ የነበሩ ህዝቦች በማንነታቸው ኮርተው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትና በፌደራል መንግስት ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የሚያገኙበት ስርኣት እውን ሆኗል። ለዘመናት ምላሽ ያላገኙ የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቂዎች ፣የብሄርና የማንትነት ጥያቄ ፣ የመሬት ባለቤትነትና የስልጣን ጥያቄ፣ ሁሉም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ምላሽ አግኝተዋል።

በዚህ አዲስ የትግል ምዕራፍ የሃገራችንን የቀልቁለት ጉዞ በመግታት ወደ ዕድገት ጎዳና የሚያሸጋግር ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር ተቀይሷል። ሃገራችን በጨበጥነው የጠራ ልማታዊ መስመር እየተመራች ለመገመት የሚያደግቱ አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግባለች። በተመፅዋችነት ትታወቅ የነበረችው ሃገር ፈጣንና ተከታታይ ልማት ከሚያረጋግጡ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ችላለች። በዚች አገር ታይተውና ተሰምተው የማያውቁ ዓበይት የልማት ፕሮጀክቶች እውን ሆናዋል። ባረጋገጥነው ፍትሃዊና ፈጣን ልማት በየዓመቱ በሚሊዮች የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት መስመር ተሻግረዋል። ሰላምና የህግ የበላይነት ተረጋግጦ፣ የሃገራችን ላዕላዊነት ተከብሮ እና ተሰሚነታችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። በማህበራዊ መስክም በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ደማቅ ድሎች ተመዝግበዋል። ሰለሆነም ያለፍት 27 ዓመታት ጠላቶች እንደሚሉት “የጨለማ ዘመን¡” ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ከጭቆናና ከባርነት ቀንበር ተላቀው የሰላም፣ የልማትና ዲሞክራሲ ትሩፋትን የሚያጣጥሙበት የለውጥ የህዳሴ ዘመን ነበር።

የተከበርከው የትግራይ ህዝብ!
የተከበራችሁ የህወሓት አባላት!
አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ የመጣው የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመር ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት በኢህአዲግ ውስጥ ባጋጠመ የጥገኛ መበስበስ አደጋ በሃገሪቱ ስፍኖ የነበረው ሰላም ደፍርሶ፣ ተጀምሮ የነበረው ልማት ተስተጓጉሎ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል። ህወሓት ያጋጠመውን ይህንን የመበስበስ አደጋ በፅናት በመታገል ዳግም ታድሶ ስርኣቱን ለማዳን ከባድ ጥረት ቢያደርግም እንኳ የኢህአዲግ አባል የነበሩ እህት ድርጅቶች ራሳቸውን ሳያጠሩና ሳያድሱ በመቅረታቸው በኢህአዴግ ውስጥ የተደረገው የአመራር ሽግሽግ በጥገኛው ሃይል የበላይነት ሊጠቃለል ችሏል። በጥገኛ መንገድ የመጣው የኢህኣዴግ ኣመራር የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመርን በመተው ጠቅልሎ ወደ ጥገኛ መበስበስና ፍፁም ግለሰባዊ አምባገነናዊነት መንገድ በመግባት በጥልቅ ተሃድሷችን ወቅት “መደገም የለባቸውም!” ብለን ያወገዝናቸውን ጉድለቶች አሁን በከፋ ደረጃ በመፈፀም ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚች አገር ከባድ ጥፋቶችና ቀውሶች ተፈጥረው ዛሬ አገራችን ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች።

የተገነቡትን ተቋማት በማፍረስ፣ አገሪቱን ወደሃላ የመመለስ ጥፋቶችና ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የአገራችን መድህን የሆነው ህገ-መንግስት ተጥሶ፣ የህግ የበላይነት ተረግጦ፣ ህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርኣቱ በጠራራ ፀሃይ እየተሸረሸረ፣ ተጠብቆ የነበረው ሰላም ደፍርሶ፣ የህዝባችን አንድነት ተበትኖ፣ ልማት ተኮላሽቶ፣ የዚች አገር ክብርና ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተደፍሮ አገራችን የትናንሽና የትላልቅ የውጪ ሃይሎች መፈንጫ ሆናለች። በዚህ ምክንያት የዚች አገር ህልውና ከማንኛውም ጊዜ በከፋ ደረጃ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል። በዚህ ሳቢያ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ህይወታቸውንና ንብረታቸውን ሲያጡ፣ አስከፊ ቅራኔና መፈናቀል ሲደርስ ፣ የአገር ዘብ ሆነው ዕድሜ ልካቸውን የታገሉ ጀነራሎች ሲቀጠፋ፣ ዮኒቨርስቲዎች ከጥናትና ምርምር ማእድ ወጥተው ወደ ሁከትና ግርግር ሲገቡ፣ ተማሪዎች ህይወታቸውን ሲያጡና በወጡበት ሲታገቱ ማየት ዕለታዊ ተግባር ሆኗል።

ከዚህም አልፎ በህጋዊ መንገድ ስልጣን ይዞ በዚች አገር ሁለገብ ዕድገት፣ ሰላምና የህግ የበላይነት አረጋግጦ ይመራ የነበረው ኢህአዴግ በፍፁም ፀረ- ዲሞክራሲ፣ በህገወጥ አካሄድና በእህት ድርጅቶች ክህደት እንዲፈርስ ተደርጓል፤ አዲስ ብልፅግና የተባለ ድርጅትም ተመስርቷል። ኢህአዴግ በምርጫ ተወዳድሮ የያዘውን ስልጣን ጊዜው ደርሶ ለህዝብ ሳያስረክብ በመጥለፍ በፌደራልና በአዲስ አበባ አስተዳደር ህወሓት ከሃላፊነት እንዲነሳ እየተደረገ ነው። በዚች አገር ፍፁም ፀረ-ዲሞክራሲና አፈና ነግሷዋል። ፖለቲካዊ ምህዳሩ ጠቧል፣ የተለየ ሃሣብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፣ይታፈናሉ።

የተከበርከው የትግራይ ህዝብ!
የተከበራችሁ የህወሓት አባላት!

በዚች አገር የተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ፈታኝ ቢሆንም እንኳ ድርጅታችን ህወሓት ገና በጥዋቱ ያነገበውን ህዝባዊ ዓለማ ታጥቆ አሁንም በብርታት፣ በፅናትና በብስለት በመመከት ላይ ይገኛል። ከትምክህትና ከአድሃሪያን ሃይሎች ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ በአጠቃላይ በአገሪቱ የህግ የበላይነትና ስርኣት እንዲከበር፣ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት በየትኛውም ቦታና ጊዜ እንዲከበር ዛሬም እንደወትሮው በፅናት በመታገል ላይ ይገኛል። ህብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርኣቱ እንዳይፈርስ፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ በዜጎች በተለይም በህዝባችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የሚያደርጉትን ያለሰለሰ ትግል ለማደናቀፍ ከዚህም ከዚያ የተሰባሰቡ የትምክህት ሃይሎች ግንባር ፈጥረው ዘምተዋል። የትግራይ ህዝብንና መሪ ድርጅቱ ህወሓትን አንገት ለማስደፋትና ለማንበርከክ ያላቸውን ሃይል ሁሉ አሟጠው እየተረባረቡ ይገኛሉ። ተሸናፊ የትምክህት ሃይሎች ያገኙዋትን ዕድል ተጠቀመው የትግራይን ህዝብ ዳግም ለመጨፍለቅ ቀን ከሌት የተደራጀና የተቀናጀ ጥቃት እየፈፀመሙ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ምኞታችንና ፍላጎታችን ብትር በነቀነቀ ላይ ብትር መነቅነቅ አይደለም ። ዓላማችን ለረጅም ጊዜ በድህነት፣ በድንቁርናና በጦርነት የተጠቃውን ህዝባችንን በልማት መካስ ነው። የትግራይ ህዝብ ህልውናና ድህንነት የሚከበረውም በልማት መስክ በምናስመዝግባቸው ሁለገብ ድሎች፣ በመልካም አሰተዳደር መስክ በምናረጋግጠው እመርታ፣ በክልላችን በምናረጋግጠው ዋስትና ያለው ሰላምና ፀጥታ ነው። ኣጀንዳችን ሰላም፣ ልማት፣ ዲሞክራሲና በሁሉም ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ ለሁሉም ህዝቦች እኩል ዕድል የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ ፌደራላዊ ስርኣት እንዳይፈርስ መታገል ነው።
ስለሆነም የትግራይን ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓትን ከዚህ መሰረታዊ አጀንዳው አውጥቶ በውጥረት ውስጥ በማስገባት አንገቱን እንዲደፋና እንዲንበረከክ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከንቱ ድካም መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። የትግራይ ህዝብ እንኳንና ዛሬ ቀድሞም ቢሆን በጭፍጨፋና በረሃብ አልተንበረከከም። ከወጣንበት ከፍታ እየጨመርን እንሄዳለን እንጂ በፍፁም አንወርድም፤ ፍትሃዊ ትግል እስካካሄድን ድረስም ድላችን አያጠራጥርም።

የተከበርከው የትግራይ ህዝብ!

ጠንካራው ታጋይ ህዝባችን ዛሬም እንደወትሮህ በማንኛውም አይነት ግርግር ሳትደናገር መስመርህን በፅናት ኣንግበህ ከድርጅትህ ጎን ተሰልፈህ በመታገል ላይ ትገኛለህ። ድርጅትህን እያጠራህና እያጎለበትክ ከመንገድህ ዝንፍ ሳትል በመራመድ ላይ ትገኛለህ። በትክክለኛ ዓላማ ላይ የተመሰረተ ትጥቅህን ሳታላላ፣ የፅናት አብነት ሆነህ፣ ፈተናዎችን በትእግስት እየተሻገርክ ወደፊት በመገሰገስ ላይ ትገኛለህ። እስካሁን ላደርገከው ትግልና ምከታ ድርጅትህ ህወሓት ከፍተኛ አክብሮቱን ይገልፃል። ዛሬም ነገም መልካቸው እየተቀያየረ የተለያዩ ፈተናዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። እንደ ብረት በጠነከረ የአላማ ፅናትህና አንድነትህ እንቀልፍ ያጡት የትምክህት ሃይሎችና ተባባሪዎቻቸው በውስጥህ ክፍተት ለመፍጠር ብዙ ሃብት በማፍሰስና በስልጣን በመደለል ቅጥረኞችን መልምለው አንዳንዴ አከባቢያዊ ኋላቀር አስተሳሰቦችን በማርገብገብ፣ ሃይማኖታዊ ፅንፍ በመያዝና ፀረ- ህዝብ ጥያቄዎችን በማንሳት ሌላ ጊዜ ደግሞ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎችህን መልካቸውን በመቀየር እንደብረት የጠነከረ አንድነትህን ለማደፍረስ ይንቀሳቀሳሉ። ወደፊትም እንዲህ አይነት ሴራዎችን ማጠንጠናቸው ኣይቀርም። አንተም እንደወትሮህ በብቃትህ እንክርዳዱን ከስንዴው በመለየት አንገዋላቸው። ደህንነትህንና ህልውናህን አደጋ ላይ የሚጥሉ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በፅናት ታገላቸው።

ደህንነትህና ህልውናህ የሚጠበቀው በምታደርገው ሁሉገብ ትግል መሆኑን ተረድተህ ልማትህን አጠናክረህ ቀጥል፤ ፀረ-ልማት አስተሳሰቦችንና ተግባራትን ታገል፤ ሃብትህን በስርኣት አስተዳድር፤ ቆጥብ፤ ጥሪትህንና ሃብትህን አታባክን፤ ሰላምህን ጠብቅ፤ አከባቢህን ባንዳ እንደይረግጠው እንደወትሮህ በንቃት ተከታተል፤ ተደራጅተህ ሁሉ ዓይነት ትግልህን አጠናክር፤ በምታደርገው የትግል አይነት ሁሉ ድርጅትህ ህወሓት ከጎንህ ነው። ለሁለገብ ትግልህና ፅናትህ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያለውን የላቀ ክብርና አድናቆት በመግለፅ፣ ለላቀ ትግልና ድል እንድትዘጋጅ ጥሪውን ያቀርብልሃል።

የተከበራችሁ የህወሓት አባላት!

የገባንበት የምከታ ምዕራፍ ካለፉት ወቅቶች በአይነቱም በይዘቱም በጣም የተለየ ነው። በአንድ በኩል ከኛ ጋር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ እህት ድርጅቶች በፈፀሙት ታሪካዊ ክህደት የጋራ አደረጃጀታችን የነበረው ኢህአዴግ በፀረ-ዲሞክራሲያዊና በህገ-ወጥ መንገድ በመፍረሱ ምክንያት ህወሓት በልማታዊና በዴሞክራሲያዊ መስመሩ ላይ የቆመበት ሁኔታ በመፈጠሩ፣ በዚህ መስመር ላይ የሚቃጣ የውስጥና የውጭ ፈተና ሁሉ በኛ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተገንዝባችሁ ለመመከት እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ ወደፊትም በፅናት ታገሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በክልላችን የጀመርናችው የሰላም፣ የልማት የዲሞክራሲ፣ ፍትህና መልካም ኣስተዳደርን የማረጋገጥ አጀንዳዎች ከግብ ለማድረስ በጊዜ የለንም መንፈስና የነበሩብንን ጉድለቶች በሚያካክስ ሁኔታ ሁለገብ ርብርብ እንድታደርጉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርብላቸኋል።

የተከበራችሁ የስማዕታት ቤተሰቦች፣ የጦር ኣካል ጉዳተኞች፣ ታጋየችና የትግላችን ነባር ዓቅሞች!
በከፈላችሁት ከባድ መስዋእትነት የተረጋገጠው ሰላም በመደፍረሱ፣ ልማት በመደናቀፉና የዲሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታ አደጋ ላይ በመውደቁ ከፍተኛ ቁጣ እንደተሰማችሁ ድርጀታችን ህወሓት ያምናል። ይህ በመሆኑም በቀረቻችሁ አካልና ዕድሚያችሁ መስመሩንና ስርኣቱን ለመጠበቅ ያለባችሁን ችግሮች ወደጎን በመተው ያለምንም እረፍት በመታጋል ላይ ትገኛላችሁ። ወደፊትም እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ ተደራጅታችሁ ከመመከት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። ስለሆነም ያጋጠመንንና ሊያጋጥመን የሚችለውን ፈተና ልክ እንደትናንቱ የታመቀ ዓቅማችሁንና ልምዳችሁን በመጠቀም ከድርጅታችሁና ከህዝባችሁ ጎን በመቆም ዳግም ታሪክ እንድትሰሩ ድርጅታችሁ ህወሓት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
የተከበራችሁ የትግራይ ወጣቶች!

“ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የታላቆቻችሁን አደራ እንዳትበሉ!” የሚለውን ከባድ የአደራ ቃል ጨብጣችሁ ምክንያታዊ ትግል በማካሄዳችሁ የትግራይን ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱን የፖለቲካ ሚዛን ለመለወጥ የሚያኮራ ትግል በማካሄድ ላይ ትገኛላችሁ። ያሉባችሁን ችግሮች ወደጎን በማቆየት በትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት ላይ አትኩራችሁ ጠንካራ ትግል በማካሄድ ላይ ትገኛላችሁ። በታላቆቻችሁ ታሪክ ላይ አዲስ ወርቃዊ ታሪክ በማስመዝገብ ላይ ትገኛላችሁ። እስካሁን ላካሄዳችሁት ስኬታማ ትግል ድርጅታችሁ ህወሓት ከፍተኛ አድናቆት አለው። ወደፊትም የትግራይን ህዝብ አንድነት ለማደፍረስ የሚወጠኑ ሴራዎችን በንቃትና በጠንካራ አደራጃጀት እንደምታከሽፉት አንጠራጠርም። ከህዝባችሁ ጎን ቆማችሁ ለመመከት በምታደርጉት ትግልና ሁለገብ ችግራችሁን ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ድርጅታችሁ ህወሓት ከጎናችሁ እንደሚቆም ሊያረግጥላችሁ ይወዳል።

የተከበራችሁ የትግራይ ሴቶች!

በትጥቅ ትግሉ ወቅት ድርብ ሸክም ተሸክማችሁ ታሪክ የማይረሳው ፅናት ኣሳይታችሁ ለድል በቅታችኋል። በዲሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታና በልማትም ተደጋጋሚ የሚያኮራ ታሪክ አስመዝግባችኋል። አሁን በሚካሄደው ምከታም በከፍተኛ ወኔና ቆራጥነት አራስ ነብር ሆናችሁ በመመከት ላይ ትገኛላችሁ። እስካሁን ላደረጋችሁት ትግል ድርጅታችሁ ህወሓት የላቀ አድናቆቱን ያቀርብላችኋል። ወደፊት በሚካሄደው ሁለገብ የመመከት እንቅስቃሴም ዳግም ታሪክ እንደምትሰሩ አንጠራጠርም። ያለባችሁን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እንደምንፈታችው ድርጅታችሁ ህወሓት ያረጋግጥላችኋል።
የተከበራችሁ የትግራይ ምሁራንና ባለሃብቶች!

በተካሄደው ፀረ-ድህነትና ኋላቀርነት ትግል ድርሻችሁ ከፍተኛ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። አሁን ያጋጠመውን ፈተና በመመከት ረገድም ሙሉ ሃላፊነት ወስዳችሁ በእውቀታችሁና በሃብታችሁ ከህዝባችሁና ድርጅታችሁ ጎን በመቆም ለምታደርጉት ምከተ ያለንን አክብሮትና ኣድናቆት እየገለፅን፣ ወደፊትም ያሉትን እድሎች ኣሟጣችሁ ወደ ትግራይ ህዝብ ጥቅም ለመለወጥና፣ የሚጋጥሙ ፈተናዎችን በመመከት በከፍተኛ ደረጃ ለህዝባችሁ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

የተከበራችሁ በውጭ አገር የምትኖሩ የትግራይ ተወላጆች!

በመራራው የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ወቅት ከህዝባችሁና ከድርጅታችሁ ህወሓት ጎን በመሰለፍ በእውቀታችሁ፣ በገንዘባችሁና ሙሉ ህይወታችሁን በማበርከት የማይረሳ ገድል ፈፅማችኋል። የትጥቅ ትግሉ ከተጠቃለለ በኋላም በትግራይ ዘርፈ ብዙ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ ከናንተ የሚጠበቀውን ሁሉ እያበረከታችሁ ቆይታችኋል። ባለፈው እንደፈፀማችሁት ታሪክ ሁሉ አሁንም የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት የገጠማቸውን ፈተና በፅናት ለመሻገር ያለምንም ልዩነት በፅናት በመታገል ላይ ትገኛላችሁ። እስካሁን ለአደረጋችሁት ሁለገብ ፅናትና ምከታ ድርጅታችሁ ህወሓት ምስጋናውን እየገለፀ ወደፊትም የጀመራችሁትን ትግል ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ከህዝባችሁ ጎን ተሰልፋችሁ እንድትመክቱ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

የተከበራችሁ የክልላችን ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት!

የክልላችን ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት የየካቲት 11 ውጤት መሆናችሁን የምትረዱት ሃቅ ነው። በክልላችን ለሚረጋገጠው ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የምታበረክቱት አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ እንገናዘባለን። በተለይም በትግራይ ህዝብ ላይ ያጋጠመውን ፈተና በፅናት ለመሻገርና የትግራይ ህዝብን ህልውናና ደህንነት ለማረጋገጥ ለምትታገሉ ድርጅቶችና ማህበራት ህወሓት ያለው አድናቆት ከፍተኛ ነው። ወደፊትም በሚደረገው የመመከተ እንቅስቃሴም በማንኛውም አይነት ቅጥፈትና ድለላ ሳትንበረከኩ ከህዝባችሁ ጎን በመቆም ሃላፊነታችሁን በተግባር እንድታረጋግጡ ጥሪያችንን በማቅረብ፣ የምታደርጉትን ትግል ህወሓት እንደሚደግፍ ልንገልፅላችሁ እንወዳለን።

የተከበራችሁ ህገ-መንግስታዊና ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊስት ሃይሎች!

የበለፀገች፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላሟ የተጠበቀ፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረና የህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ሃገር ለመመስረት የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት የከፈሉትን መስዋእትነት የምትረዱትና ታሪክ የማይረሳው ነው። በከባድ መስዋእትነት የተረጋገጠው የህግ የበላይነት፣ ሰላምና ፌደራል ስርኣት ተጥሶ አገራችን በመበታተን አደጋ ላይ ወድቃለች። የአገራችንና የህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርአታችን ቀጣይነት የሚረጋገጠው ህገ-መንግስታዊ ስርኣት ሲከበር ብቻ ነው። ስለሆነም ህገ-መንግስትንና ህብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርአትን ከአደጋ ለማዳን የጀመራችሁትን ትግል በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ትግል በጋራ እንደምንሰራ ህወሓት በድጋሜ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።

የተከበራችሁ የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች!
በጋራ ባደረግነው ትግልና በተከፈለው መስዋእትነት መላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአገራችን ጉዳይ በእኩልነት የመሳተፍና የመጠቀም ዕድል አረጋግጠናል። ይሁን እንጂ በትግላችሁ የተረጋገጠው ህገ-መንግስታዊ ስርኣት በትምክህት ሃይሎች አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል። የህገ-መንግስቱና የህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርኣት መፍረስ ወደ ሃገር መበታተንና እልቂት እያመራ መሆኑን በተግባር እያየነው እንገኛለን። ስለሆነም ህገ-መንግስቱንና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርኣቱን ለማዳን እንደቀድሞው በጋራ እንድንታገል ህወሓት ጥሪውን ያቀርባል።

የተከበርከው የኤርትራ ህዝብ!
የትግራይ ህዝብና ህወሓት በኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ላይ ተደራድረውም ሆነ ተሳስተው እንደማያውቁ ትገነዘባለህ። በጋራ በከፈልነው መስዋእትነት ጨቋኙ የደርግ ስርዓት ደምስሰን የጋራ ድል ጨብጠናል። የትግልህ መንስኤ የሆነውን የራስህን ዕድል በራስህ የመወሰን መብት አረጋግጠሃል፤ በዚህም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ይኮራሉ። ይሁን እንጂ ባለፉት 20 ዓመታት አሰፈላጊ ባልሆነ ጦርነትና ግጭት ውስጥ ገብተን ሁላችንም አስፈላጊ ያልሆነ ዋጋ ከፍለናል። ይህ የፈጠረው ጠባሳ ቀላል እንደማይሆን ሁላችንም የምንገነዘበው ሃቅ ነው። አሁን ግን የጋራ ጥቅማችንንና ታሪካዊ ዝምድናችንን በማደስ የጋራ እድገት ለማረጋጥ ወደሚያስችል ደረጃ እንድናሸጋግረው ህወሓት በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።

መስመራችንን አንግበን ለምከታ!
ዘላለማዊ ክብር ለሰማእታት!
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ
የካቲት 2012 ዓ.ም
መቐለ፤

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top